ፈልግ

የቤተሰቦች ተሞክሮችና ተግዳሮቶች  የቤተሰቦች ተሞክሮችና ተግዳሮቶች  

የቤተሰቦች ተሞክሮችና ተግዳሮቶች

የቤተሰብ ደህንነት ለዓለምም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕድል ወሳኝ ነው፡፡ ስለ ጋብቻና ቤተሰብ፣ እንዲሁም ጋብቻና ቤተሰብ አሁን ስላሉባቸው ችግሮችና ተግዳሮቶች አያሌ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ‹‹ የመንፈስ ቅዱስ ጥሪና ፍላጎት በታሪክ ክስተቶች ውስጥ እያስተጋባ ስለ ሆነ›› እኛም በተጨባጭ እውነታዎች ላይ ማተኮር ይኖርብናል፤ በእነዚህም ክስተቶች አማካይነት ‹‹ቤተክርስቲያንም የጋብቻንና የቤተሰብን ጥልቅ ምስጢር ይበልጥ ወደ ማወቅ ልትደርስ ትችላለች››፡፡ እዚህ ላይ ዛሬ ስለቤተሰብ የሚነገረውን ነገር ሁሉ ለማቅረብ አልሞክርም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የሲኖዶስ አባቶች በመላው ዓለም ያለውን የቤተ ሰቦች ሁኔታ የመረመሩ ስለ ሆነ፣ ከእነርሱ ሐዋርያዊ ምልከታዎች አንዳንዶቹንና ከራሴም ተሞክሮ ያገኘሁአቸውን አንዳንድ ሥጋቶች ማቅረብ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

አሁን ያለው ቤተሰብ እውነታ

 ‹‹ለክርስቶስ ትምህርት ታማኝ ሆነን፣ ዛሬ ቤተ ሰብ የሚገኝበትን እውነታ ከነውስብስብነቱ፣ ከብርሃናዊና ከጨለማ ጎኖቹ ጭምር እናያለን … የዘመናችን የሥነ ሰውና  የባህል ለውጦች የሕይወትን ገጽታዎች ሁሉ ስለሚነኩ፣ ትንተናና ዘርፈ ብዙ አቀራረብን ይሻሉ››፡፡ ከብዙ አሥርት ዓመታት በፊት፣ የስፔን ጳጳሳት እንዳመለከቱት፣ ቤተሰቦች ‹‹ተግባራትን፣ ኃላፊነትንና ሥራን በእኩልነት በማከፋፈል›› ሻል ያለ ነጻነት ለመቀዳጀት ችለዋል፡፡ በእርግጥም፣ ‹‹በባልና ሚስት መካከል ላለው ግላዊ ግንኙነት ትልቅ ትኩረት መስጠቱ የቤተ ሰብን ሕይወት ይበልጥ ሰብአዊ ያደርገዋል››፡፡ ከዚህ ሌላ  ‹‹የዛሬ ኅብረተሰብም ሆነ መጪው ኅብረተሰብ አሮጌዎቹን ቅርጾችና ምሳሌዎች ያለ ነቀፋ እንዲቀጥሉ አይፈቅድም››፡፡ እንዲሁም ‹‹ግለሰቦች፣ በግላዊም ሆነ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ፣ ከማኅበራዊ መዋቅሮች የሚያገኙት ድጋፍ ካለፈው ጊዜ እያነሰ መምጣቱን  ከሥነ ሰውና ከባህል ለውጦች መሠረታዊ አቅጣጫዎች››  በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል፣ ‹‹የቤተሰብን ትስስር የሚያላላውና እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል ነጥሎ የሚያየው፣  በአንዳንድ ሁኔታዎችም የአንድ ሰው ኃላፊነት ፍጹም ተብለው በሚገመቱ የግል ምኞቶች ልክ ይወሰናል ወደሚል አስተሳሰብ የሚመራው ከልክ ያለፈ ግለኝነት ለሚያስከትለው ከፍተኛ አደጋ እኩል ግምት መስጠት ያስፈልጋል››፡፡   ‹‹ከመጠን ባለፈ የግለኝነት ባህል የተፈጠሩ ውጥረቶች፣ ከሀብትና ከምቾት ጋር ተዳምሮ፣ በቤተሰብ ውስጥ መቻቻል እንዳይኖርና ጥላቻ እንዲነግሥ ያደርጋሉ››፡፡ እዚህ ላይ የዛሬ ዘመን ፈጣን የሕይወት ለውጦችን፣ ጭንቀትንና የኅብረተሰብና የሥራ አደረጃጀትን ለማካተት እወዳለሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ kሚ ውሳኔዎችን የሚከለክሉ ባህላዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሰፊ የሆነ ጥርጣሬና አሻሚ ሁኔታ ያጋጥመናል፡፡ ለምሳሌ፣ ከተራ መመሳሰል ይልቅ  ወደ እርግጠኝነት ለሚያዘነብል ግለኝነት ዋጋ እንሰጣለን፡፡ ይህ ሁኔታ  ግብታዊነትንና የሰዎችን ክህሎት በተሻለ መልኩ መጠቀምን የሚያበረታታ ቢሆንም፣ አቅጣጫውን ከሳተ ግን የማያቋርጥ ጥርጣሬ፣ የቁርጠኝነት ፍርሃት፣ የራስ ወዳድነትና የእብሪት አስተሳሰብን ሊያስፋፋ ይችላል፡፡ የመምረጥ ነጻነት ሕይወታችንን ለማቀድና ራሳችንን ለማብቃት ያስችለናል፡፡ ሆኖም፣ ይህ ነጻነት ክቡር ዓላማ ያለው ወይም ግላዊ ሥነ ምግባርን የተላበሰ ካልሆነ፣ ራስን ለሌሎች አሳልፎ የመስጠት ፍላጎትን ይሸረሽረዋል፡፡  በእርግጥ፣ ጋብቻዎች እየቀነሱ በመጡባቸው በርካታ አገሮች  ለብቻ መኖርን የሚመርጡ ወይም በደባልነት  ሳይኖሩ ጊዜአቸውን አብረው ለማሳለፍ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥራቸው  እያደገ መጥቶአል፡፡ ከዚህ ሌላ፣ ፍትሕን በተመለከተ አሳሳቢ ሁኔታዎች መኖራቸውን ልብ እንበል፡፡ መግባባት ከሌለ፣ ይህ ሁኔታ ዜጎችን በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብቻ ያተኮሩ ደንበኞች ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡

እነዚህ ምክንያቶች ስለ ቤተሰብ ያለንን ግንዛቤ በሚነኩበት ጊዜ፣ እንደ አመቺነቱ የሚጠቅም መገናኛ ጣቢያ፣ ወይም መብቶች  በግል ምኞትና ሁኔታ በሚዋዥቁ ግንኙነቶች ውስጥ የሚከበሩበት ድባብ ይፈጠራል፡፡ በመጨረሻም፣ ባሁኑ ጊዜ  አቅጣጫ የሚያሳዩ እውነቶች፣ እሴቶችና መርሆች የሌሉና ሁሉም ነገር የሚቻልና የተፈቀደ  ይመስል፣ እውነተኛ ነጻነትንና እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ፈለገ መሆን ይችላል ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ማምታታት  ቀላል ነገር ሆኖአል፡፡ የማይመች ወይም አድካሚ መስሎ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ ለግላዊና መረጋጋት ለሰፈነበት የጋብቻ ዓላማ ዝግጁ የመሆን ሁኔታ ወደ ጎን ገሸሽ ይደረጋል፡፡ የብቸኝነት ፍርሃትና የመረጋጋትና የታማኝነት ፍላጎት፣ እያደገ ከመጣውና ግላዊ ግቦች እንዳይሳኩ በሚያደርግ የግንኙነት ወጥመድ ላለመያዝ ካለው ፍርሃት ጋር አብሮ  ይኖራል፡፡

እንደ ክርስቲያን፣ የዘመኑን ስሜቶች ለመሸሽ ወይም ዘመናዊ ለመምሰል ፣ ወይም በሰብአዊና ግብረ ገባዊ ጉድለቶች ምክንያት በሚደርስ ተስፋ መቁረጥ ብቻ ጋብቻን መደገፋችንን ማቆም አንችልም፡፡ ያለበለዚያ ለዓለም መስጠት ያለብንንና የምንችለውን እሴት ሳንሰጥ እንቀራለን፡፡ ነገሮች ይለውጣሉ በሚል እሳቤ ብቻ ባሁኑ ጊዜ የሚታዩ ክፉ ነገሮችን ማውገዝ ብቻ ትርጉም እንደማይኖረው ግልጽ ነው፡፡ ሥልጣን አለኝ ብሎ ብቻ ሕጎችን በጉልበት ለመጫን መሞከርም አይጠቅምም፡፡ ለእኛ የሚያስፈልገን ጋብቻንና ቤተሰብን የመረጥንባቸውን ምክንያቶችና ዓላማዎች ለማስረዳት፣ ከዚህም በመነሣት እግዚአብሔር ለሚሰጣቸው ጸጋ በተሻለ መልኩ ምላሽ እንዲሰጡ ወንዶችና ሴቶችን ለመርዳት ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማውና ለጋስ ጥረት ማድረግ ነው፡፡

 ከዚህ ሌላ፣ ትሁታንና ሐቀኞች መሆንና ፣ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያናዊ እምነታችንን የምናሳይበትና ሌሎች ሰዎችን የምንይዝበት መንገድ ለዛሬው አስቸጋሪ ሁኔታ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ በቂና ጤናማ ግለ ሂስ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ፣ ለሥነ ተዋልዶ ተግባሩ  ብቻ ልዩ ትኩረት ስለምንሰጥ፣   ብዙውን ጊዜ  የጋብቻ  ትርጉም፣ እርሱም የሚያቀርበው በፍቅር የማደግ ጥሪና እርስ በርስ የመረዳዳት ዓላማ ተድበስብሶ ሊቀር ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ለወጣት ተጋቢዎች የራሳቸውን የጊዜ ሁኔታ፣ አስተሳሰባቸውንና ተጨባጭ ፍላጎቶቻቸውን ያገናዘበ  ጠንከር ያለ ምክር ሁልጊዜ አልሰጠናቸውም፡፡ አልፎ አልፎ ስለ ጋብቻ እጅግ ረቂቅና ልባዊ ያልሆነ፣ ከእውነተኛ የቤተሰቦች ተጨባጭ ሁኔታዎችና ተግባራዊ ችሎታዎች የራቀ ነገረ መለኮታዊ ሐሳብ አቅርበን ይሆናል፡፡ ይህ ከልክ ያለፈ ሐሳባዊነት፣ በተለይ በእግዚአብሔር ጸጋ መተማመንን ለመቀስቀስ ባልቻልንበት ሁኔታ፣ ጋብቻን ይበልጥ አጓጊና ማራኪ በማድረግ ፈንታ ተቃራኒውን መልክ እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡

ለረጅም ጊዜ ለጸጋ ክፍት መሆንን ሳናበረታታ በትምህርታዊ፣ ሥነ ሕይወታዊና ግብረ ገባዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር ለቤተሰቦች በቂ ድጋፍ እየሰጠን ነው፣የጋብቻን ትስስር እያጠናከርን ነው፣ ለጋብቻ ሕይወት ትርጉም እየሰጠን ነው ስንል ቆይተናል፡፡ ጋብቻ የዕድሜ ልክ ሸክም ሳይሆን፣ወደ ግላዊ ዕድገትና ሙላት የሚያደርስ መንገድ መሆኑን የማስረዳት ችግር አለብን፡፡ እንደዚሁም፣ ውስንነቶች ቢኖሩባቸውም ለወንጌል ጥሪ የተቻላቸውን ያህል ምላሽ ለሚሰጡና በውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ የራሳቸውን ፍላጎት መርምረው ማወቅ ለሚችሉ ምእመናን ኅሊና በቂ ቦታ መስጠት ይከብደናል፡፡ የተጠራነው ኅሊናን ለማነጽ እንጂ ለመተካት አይደለም፡፡

አብዛኞቹ ሰዎች kሚ ለሆኑና የእርስ በርስ መከባበር ለሚታይባቸው የቤተሰብ ግንኙነቶች ዋጋ ስለሚሰጡ ልናመሰግናቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤተክርስቲያን በፍቅር ማደግን፣ ግጭት ማስወገድንና ልጆች ማሳደግን በሚመለከቱ መስኮች አመራርና ምክር ለመስጠት የምታደርገውን ጥረት ያደንቃሉ፡፡ ብዙዎቹም የጋብቻንና የቤተሰብን ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ የሚረዳቸውን በምሥጢረ ንስሐና በምሥጢረ ቁርባን የሚገኘውን  የጸጋ ኃይል አውቀዋል፡፡ በአንዳንድ አገሮች፣ በተለይም በተለያዩ የአፍሪካ አካባቢዎች፣ ዓለማዊነት አንዳንድ ባህላዊ እሴቶችን  ስላላዳከመ፣ ጋብቻዎች በሁለት ትላልቅ/ሰፊ ቤተሰቦች መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠርና ችግሮችንና ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ግልጽ መዋቅሮች እንዲኖሩ አስችለዋል፡፡ ባሁኑ ጊዜ፣ ዘላቂ ብቻ ሳይሆኑ ፍሬያማና በፍቅር የተሞሉ ጋብቻዎች ስላላቸው ምሥክርነት ምሥጋና እናቀርባለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ጥንዶች የወንጌልን ፍላጎት በማወቅ እንዲያድጉ የሚረዳ አዎንታዊና ምቹ ሐዋርያዊ አቀራረብ እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም፣ ብዙውን ጊዜ እውነተኛ ደስታ የሚገኝባቸውን መንገዶች በመጠቆም ረገድ የቅድሚያ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የአስተሳሰብ ዝቅጠት የሚታይበትን ዓለም በማውገዝ ሐዋርያዊ ጉልበታችንን ስለምናጠፋ ተከላካዮች ሆነናል፡፡ ብዙ ሰዎች ስለ ጋብቻና ቤተሰብ ያለው የቤተክርስቲያን መልእክት ትልቅ ምሳሌ ያስቀመጠውን፣ ነገር ግን፣ ሳምራዊት ሴትን ወይም በምንዝር የተያዘችውን ሴት ለመሰሉ ግለሰቦች ደካማነት ክብካቤና ቅርበት ከማሳየት ያልተቆጠበውን የኢየሱስን ትምህርትና አስተሳሰብ በግልጽ እንደማያንጸባርቅ ያስባሉ፡፡

ፍቅርን ወይም ራስን አሳልፎ መስጠትን የማይደግፍ ባህላዊ ዝቅጠትን ከማውገዝ ወደ ኋላ እንላለን ማለት ዘበት ነው፡፡ ከሁለቱ ሲኖዶሶች በፊት የተደረገው  ምክክር የተለያዩ ‹‹የጠፊ ባህልን›› ምልክቶች አሳይቶአል፡፡ እዚህ ላይ፣ ለምሳሌ፣ ሰዎች ከአንድ ስሜታዊ ግንኙነት ወደ ሌላው በምን ያህል ፍጥነት እንደሚዞሩ ሳስብ ይገርመኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች ፍቅር  በሸማቹ ፍላጎት፣ ከማኅበራዊ መረቦች መስመር ጋር  ሊገናኝ ወይም ሊላቀቅ ይችላል፣ ግንኙነቱም በፍጥነት ‹‹ሊታገድ›› ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡ እንደዚሁም ከkሚ ግዴታ፣ በነጻ ጊዜ ከመመሰጥ፣ ብቸኝነትን ለመሸሽ፣ ጥበቃ ወይም አንዳንድ አገልግሎቶችን ለመስጠት  ሲባል ጥቅምና ጉዳቱን ከሚያመዛዝኑ ግንኙነቶች ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ፍርሃት አስባለሁ፡፡ ውጤታማ ግንኙነቶችን የምንመለከተው ቁሳዊ ነገሮችንና አካባቢን በምንመለከትበት አኳኋን ነው፤ ሁሉም ነገር ቀሪ ነው፤ ማንም ሰው ተጠቅሞ የተረፈውን ይጥላል፣ ይወስዳል፣ ይሰብራል፣ ይበዘብዛል፣ እስከ መጨረሻ ጠብታ ድረስ ይጨምቃል፣ ከዚያ በኋላ ደህና ሁን ይላል፡፡ ራስን ማምለክ ሰዎችን ከራሳቸው ምኞትና ፍላጎት ባሻገር እንዳያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሆኖም፣ ፈጠነም ዘገየም፣ ሌሎች ሰዎችን እንደ ዕቃ የሚጠቀሙ ሰዎች ራሳቸው በዚያው አስተሳሰብ መሠረት የሌሎች መጠቀሚያ ሆነው እንደ አሮጌ ዕቃ ይጣላሉ፡፡ ፍቺ ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ‹‹ነጻነትን›› በሚሹና እርስ በርስ በመደጋገፍና በመንከባከብ አብሮ የማርጀት ሐሳብን በሚቃወሙ ዕድሜአቸው በገፋ ጎልማሶች መካከል መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡

‹‹የወደፊት ዕድል ስለሌላቸው ወጣቶችን ቤተሰብ እንዳይመሠርቱ በሚያስገድዳቸው ባህል ውስጥ እንኖራለን ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል፡፡ ይኸው ባህል ብዙ አማራጮች ያሉአቸው ወጣቶችም ቤተሰብ እንዳይመሠርቱ ይገፋፋቸዋል››፡፡ በአንዳንድ አገሮች፣ ብዙ ወጣቶች ‹‹በኢኮኖሚአዊ፣ በሥራ ወይም በትምህርት ምክንያት ጋብቻን ያዘገያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ይህን የሚያደርጉት ጋብቻንና ቤተሰብን ዋጋ በሚያሳጡ ርእዮተ ዓለሞች፣ እጅግ ከባድና የተቀደሰ ነገር ነው ብሎ ከመገመት በሚመጣ ፍርሃት፣ አብሮ ከመኖር ጋር በተያያዙ ማኅበራዊ ዕድሎችና ኢኮኖሚአዊ ጥቅሞች፣ ፍቅርን የስሜትና የደግነት ሐሳብ ብቻ ነው በሚል ግምት፣ ነጻነታቸውን እንዳያጡ በመፍራት፣ እና ተቋማዊ ቢሮክራሲያዊ መስሎ የሚታየውን ነገር በመጥላት ነው››፡፡ ስለዚህ፣ የወጣቶችን ልብ ለመማረክና ለልግስና፣ ለዝግጁነት፣ ለፍቅርና ለጀግንነት ጭምር ያላቸውን ችሎታ ለማነሣሣት፣ እንዲሁም የጋብቻን ተግዳሮት በንቃትና በድፍረት እንዲቀበሉ ለማድረግ የሚረዳ ትክክለኛ kንk፣ የክርክርና የምስክርነት ዐይነቶችን ማግኘት ያስፈልገናል፡፡

የሲኖዶሱ አባቶች እንዳመለከቱት፣ በዛሬው ዓለም የሚታዩ ባህላዊ ዝንባሌዎች፣ በሰው ስሜት ላይ ምንም ገደብ ያላቸው አይመስልም፤ እንዲያውም፣ ‹‹ራስን የሚያመልክ፣ ያልተረጋጋ ወይም ተለዋዋጭ ስሜት አንድን ሰው ሁልጊዜ ወደ ብስለት አያደርሰውም››፡፡ እንዲሁም ባሁኑ ጊዜ ‹‹ ኢንተርኔትን ያለ አግባብ በመጠቀም ጭምር እየተስፋፉ የመጡ አስነዋሪ ፊልሞችና ገላን ለገንዘብ የመሸጥና  ሰዎችን ወደ ዝሙት አዳሪነት እንዲገቡ የሚያስገድዱዋቸው አስነዋሪ ሁኔታዎች›› መኖር እንዳሳሰባቸው የሲኖዶሱ አባቶች  ገልጸዋል፡፡ በዚህ አገባብ ‹‹ጥንዶች ብዙውን ጊዜ ስለ ዕድገት አማራጮች  እርግጠኞች አይደሉም፣ ያወላውላሉ፣ ይታገላሉ፡፡ ብዙዎቹ በዕድገታቸውና በወሲባዊ ሕይወታቸው ገና በእንጭጭነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ የጥንዶች የግንኙነት ቀውስ ቤተሰብን ያናጋል፣ በመለያየትና በፍቺ ምክንያት እንዲሁም ግላዊና ማህበራዊ ትስስሮችን በማላለት ወጣቶችን፣ ሕጻናትንና መላውን ኅብረተሰብ ወደ ከባድ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል››፡፡  የጋብቻ ችግሮች ‹‹ብዙውን ጊዜ ከጥድፊያና ለማሰላሰልና ለትእግሥት፣ መሥዋዕትነት ለመክፈልና እርስ በርስ ይቅር ለመባባል  ድፍረቱ ካለመኖር ጋር ይያያዛሉ፡፡  ውድቀት ለአዲስ ግንኙነቶች፣ ለአዲስ ጥንዶች፣ ለአዲስ ጥምረቶችና ለአዲስ ጋብቻዎች መነሻ ይሆናል፣ ለክርስትና ሕይወት ውስብስብና አስቸጋሪ የሆኑ የቤተ ሰብ  ሁኔታዎችንም ይፈጥራል››፡፡        

ከዚህ በተጨማሪ፣ ‹‹ልጆች መውለድን በመጥላትና በዓለም የሥነ ተዋልዶ ጤና ፖሊቲካ በመበረታታት የተከሰተው የሕዝብ ብዛት መቀነስ በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት ከእንግዲህ ወዲያ አስተማማኝ የማይሆንበትን ሁኔታ ይፈጥራል፤ በጊዜ ሂደት ደግሞ ይህ የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ወደ ኢኮኖሚአዊ ድህነትና ተስፋ ማጣት ያመራል፡፡ የሥነ ሕይወት ቴክኖሎጅም በልደት ምጣኔ ላይ ትልቅ አንደምታ ነበረው››፡፡ ከዚህ ሌላ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ፤ እነርሱም ‹‹የኢንዱስትሪ ዕድገት፣ የሥነ ተዋልዶ አብዮት፣ የሕዝብ ብዛት ፍርሃትና የኢኮኖሚ ችግሮች ናቸው፡፡ …የፍጆታ ባህልም  ሰዎችን ነጻነታቸውንና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ልጆችን እንዳይወልዱ ሊከለክላቸው ይችላል››፡፡ ሕይወትን የማስተላለፍ በጎ ኅሊና ያላቸው ጥንዶች፣ በበቂ ምክንያቶች፣ የልጆቻቸውን ቁጥር እንዲገድቡ ያደርጋቸዋል፣ ‹‹ ለኅሊናቸውም ክብር ስትል ቤተክርስቲያን ፅንስ ለመከላከል፣ ለማምከንና ፅንሰ ለማስወረድ ጭምር የሚደረገውን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በጥብቅ ትቃወማለች››፡፡  እነዚህን የመሰሉ እርምጃዎች፣ ከፍተኛ የውልደት መጣኔ ባለባቸው ስፍራዎች ጭምር ተቀባይነት የላቸውም፤ በአንዳንድ አሳሳቢ የሆነ ዝቅተኛ የልደት ምጣኔ ባላቸው አገሮችም ቢሆን ፖለቲከኞች እነዚህን እርምጃዎች ሲያበረታቱ እናያለን፡፡ የኮሪያ ጳጳሳት እንደተናገሩት፣ ይህ እርምጃ ‹‹እርስ በርሱ የሚቃረንና የራስን ግዴታ ችላ የማለት አካሄድ ነው››፡፡

በአንዳንድ ኅብረተሰቦች ዘንድ የእምነትና ሃይማኖታዊ ልምዶች መዳከም ቤተሰቦች ይበልጥ እንዲነጠሉና ከችግራቸው እንዳይላቀቁ ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል፡፡ የሲኖዶስ አባቶች እንዳስገነዘቡት፣ ‹‹ከዘመኑ ባህል ትልቁ የድህነት ምልክቶች አንዱ በሰው ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር ባለመኖሩና በግንኙነቶች ደካማነት ምክንያት የሚፈጠር ብቸኝነት ነው፡፡ እንደዚሁም፣ በማኅበራዊና ባህላዊ እውነታዎች ፊት የተጋረጠና ብዙውን ጊዜ ቤተሰቦችን የሚጨፈልቅ አጠቃላይ የሆነ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አለ…፡፡ ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ በተkማት በኩል ፍላጎትና ትኩረት በማጣት የተተው ይመስላቸዋል፡፡ የሕዝብ ብዛት ቀውስ፣ ልጆችን የማሳደግ ችግር፣ አዲስ ሕይወትን ለማስተናገድ ያለው ማወላወል፣ አረጋውያንን እንደ ሸክም የማየት ዝንባሌና የአእምሮ መረበሽ እንዲሁም የረብሻና የሁከት መጨመር በማኅበራዊ ሥርዓት ላይ የደረሰው አሉታዊ አንደምታ ከፍተኛ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ ስለዚህ፣ መንግሥት የወጣቶችን ተስፋ ለማለምለምና ቤተሰብ ለመመሥረት ያላቸውን ዕቅድ እንዲያሳኩ ለመርዳት ተገቢ ሕጎችን የማውጣትና ሥራ የመፍጠር ኃላፊነት አለበት››፡፡

ምቹ ወይም በቀላል ዋጋ የሚገኝ መኖሪያ ቤት እጦት ይፋ የጋብቻ ግንኙነቶች እንዲዘገዩ ያደርጋል፡፡ ‹‹ቤተሰብ ሁነኛ፣ ለቤተሰብ ኑሮ የሚስማማና ከአባላት ቁጥር ጋር የሚመጣጠን፣ ለቤተሰብና ለማኅበረሰብ ሕይወት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ያሉበትን አካባቢ የማግኘት መብት እንዳለው›› ልብ ይሏል፡፡  ቤተሰቦችና መኖሪያ ቤቶች አብረው ይሄዳሉ፡፡  ይህም በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ መብቶች ላይ ማተኮር ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ ያስገነዝበናል፡፡ ቤተሰብ ለኅብረተሰብ አስፈላጊ መሣሪያ ስለ ሆነ በሚገባ ሊጠበቅ ይገባል፡፡  ‹‹ቤተክርስቲያን፣ በተለይም ዛሬ በፖለቲካ አጀንዳዎች ውስጥ እምብዛም ትኩረት የተነፈገውን ጋብቻንና ቤተሰብን መንከባከብና ከጥቃት መከላከል የተልእኮዋ አንዱ አካል እንደ ሆነ  ትገነዘባለች››፡፡(25)  ቤተሰቦች ‹‹በሕጋዊ፣ ኢኮኖሚአዊ፣ ማኅበራዊና በመንግሥታዊ በጀት አደላደል ረገድ ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት በቂ የቤተሰብ ፖሊሲ የማግኘት›› (መብት አላቸው፡፡ አልፎ አልፎ ቤተሰቦች የሚወዱት ሰው ሲታመምባቸው፣ በቂ የጤና እንክብካቤ በማጣት ይሠቃያሉ፣ ወይም ሁነኛ ሥራ ለማግኘት ይፍጨረጨራሉ፡፡

‹ኢኮኖሚአዊ እንቅፋቶች ቤተሰብ የትምህርት፣ በባህላዊ ተግባራትና በኅብረተሰብ ሕይወት ውስጥ ተሳትፎና ተደራሽነት እንዳይኖረው ያደርጉታል፡፡ የአሁኑ ጊዜ ኢኮኖሚአዊ ሁኔታ ሰዎችን፣ በብዙ መንገዶች በኅብረተሰብ ውስጥ እንዳይሳተፉ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ  ቤተሰቦች ከሥራ ጋር በተያያዘ ችግሮች ያጋጥሙአቸዋል፣ ወጣቶች ያላቸው ችሎታ አነስተኛና ሥራ የማግኘት ዕድላቸውም ጠባብና አስተማማኝ አይደለም፡፡ የሥራ ቀናት ረጅምና ብዙውን ጊዜ ከቤት ካለው ርቀት አኴያ ይበልጥ አድካሚ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ የቤተሰብ አባላት በአንድነት እንዳይሰበሰቡ ወይም ወላጆች በየቀኑ ግንኙነታቸውን በሚያድሱበት መንገድ ከልጆቻቸው ጋር እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል››፡፡

‹‹ በርካታ ልጆች ከጋብቻ ውጭ ይወለዳሉ፣ ብዙዎቹም በአንድ ወላጅ እጅ ብቻ ወይም በቅልቅል ወይም አዲስ በተመሠረተ ቤተሰብ ውስጥ ያድጋሉ፡፡ … በልጆች ላይ የሚፈጸም የጾታ ብዝበዛ በአሁኑ ኅብረተሰብ ውስጥ ሌላው አሳፋሪና ጠማማ እውነታ ነው፡፡ በጦርነት፣ በአሸባሪነት ወይም በተደራጀ ወንጀል ምክንያት ሁከት የሚደርስባቸው ኅብረተሰቦች፣ በተለይ በትላልቅ ከተሞች፣ የቤተሰብ ዝቅጠት ይታያል፣ በከተሞች ዳርቻ ደግሞ ‹‹የጎዳና ልጆች›› የሚባለው ክስተት እየጨመረ መጥቶአል››፡፡ በልጆች ላይ የሚደርስ የጾታ ጥቃት እጅግ ሰላማዊ በሚባሉ ሥፍራዎች፣ በተለይም በቤተሰቦች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በማኅበራትና በክርስቲያናዊ ተkማት ውስጥ ጭምር መከሰቱ እጅግ አሳፋሪ ጉዳይ ነው፡፡

‹‹ስደት በቤተሰብ ሕይወት ላይ ካለው አሉታዊ አንደምታ አንጻር ሊጋፈጡትና ሊረዱት የሚገባ ሌላው የጊዜው ምልክት ነው››፡፡ በቅርቡ የተካሄደው ሲኖዶስ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ እንዳስገነዘበው፣ ‹‹በተለያዩ መንገዶች፣ ስደት በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች መላ ሕዝቦችን እየነካካ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም በዚህ መስክ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ ይህን የወንጌል ምስክርነት መጠበቅና ማስፋፋት (ንጽ. ማቴ. 25፡ 35) ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖአል፡፡… ከሕዝቦች ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ እንቅስቃሴ ጋር የሚጣጣም የሰዎች ዝውውር ለሚሰደዱ ቤተሰቦችም ሆነ ስደተኞችን ለሚቀበሉ አገሮች እውነተኛ ብልጽግናን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ በጦርነት፣ በብጥብጥ፣ በድህነትና ፍትህ በማጣት ምክንያት በቤተሰቦች ላይ የሚደርስ፣ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ሕይወትን አደጋ ላይ በሚጥል የጉዞ ውጣ ውረድ የታጀበ የግዴታ ስደት፣ ሰዎችን ያስጨንቃል፣ ቤተሰቦችንም ያናጋል፡፡ ቤተሰብ ከቤተሰቦች ጎን በመቆም፣ ለሚሰደዱ ቤተ ሰቦች ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ኋላ ለሚቀሩ የቤተሰብ አባላት ጭምር የሚሆን ልዩ ሐዋርያዊ ፕሮግራም መንደፍ ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ሐዋርያዊ ተግባር ለባህላቸው፣ ለመጡበት ሰብአዊና ሃይማኖታዊ ሕንጸት እንዲሁም ለአምልኮ ሥርዓቶቻቸውና ትውፊቶቻቸው መንፈሳዊ ቅርስ ክብር በሚሰጥ መልኩና በልዩ ሐዋርያዊ እንክብካቤ ጭምር መፈጸም አለበት፡፡ … ስደት በተለይ ለቤተሰቦችና ለግለሰቦች አስደንጋጭና አጥፊ የሚሆነው፣ ከሕጋዊ አግባብ ውጭ ሲፈጸምና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ መረብ ሲደገፍ ነው፡፡ ይህም ይበልጥ የሚጎላው፣ በጊዜያዊ መጠለያዎችና የስደተኛ ካምፖች ለረጅም ጊዜያት ለመቆየት የሚገደዱ ሴቶችን ወይም ብቸኛ ሕጻናትን ሲያካትትና የውሕደት ሂደት መጀመር የማይቻል ሲሆን ነው፡፡ ከልክ ያለፈ ድህነትና ሌሎች የቤተሰብ ሁኔታዎች አንዳንድ ጊዜ መሪ ቤተሰቦችን እንኳ ልጆቻቸውን ለዝሙት አዳሪነት ወይም ለሕገ ወጥ የሰው አካል ዝውውር እስከ መሸጥ ድረስ ያንኮታኩቷቸዋል››፡፡ ‹‹ በብዙ የዓለም ክፍሎች በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ በክርስቲያኖች፣ በጎሳዎችና በአናሳ የሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ስደትና እንግልት ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ማኅበረሰብ ትልቅ ፈተና ሆኖአል፡፡ ስለዚህ፣ በተጨባጭ መንገድ ጭምር፣ ቤተሰቦችንና ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን በየትውልድ አገራቸው እንዲቆዩ ማናቸውንም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል››፡፡

የሲኖዶሱ አባቶች ‹‹የአካል ጉዳተኝነት ያልተጠበቀ ተግዳሮት የቤተሰብ ሚዛንን፣ ምኞትና ተስፋን ሊያናጋ ስለሚችል ልዩ እንክብካቤ የሚያሻቸው ሰዎች ስላሉባቸው ቤተሰቦች…›› ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ልዩ ድጋፍ የሚፈልግ ልጅ የማሳደግ አስቸጋሪ ፈተናን በጸጋ የሚቀበሉ ቤተ ሰቦች ሊደነቁ ይገባል፡፡ እነዚህ ቤተሰቦች ለቤተክርስቲያንም ሆነ  ለኅብረተሰብ እንዲሁም ለሕይወት ስጦታ ታማኝ ስለ መሆን  የማይተካ ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ያለ ቤተሰብ ከክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር በመተባበርና የሰውን ሕይወት  ደካማነት ምሥጢር በደስታ ተቀብሎ በመንከባከብ፣ አዲስ የአቀራረብ ስልቶችንና  የድርጊት ዘዴዎችን ሊቀይስና ከሌሎች ጋር የመቀራረብና የመመሳሰል መንገዶችን ሊያገኝ ይችላል፡፡ አካል ጉዳተኞች ለቤተ ሰብ ስጦታና በፍቅር፣ እርስ በርስ በመረዳዳትና በአንድነት ለማደግ መልካም ዕድል የሚያጎናጽፉ ናቸው፡፡… ቤተሰብ በእምነት ብርሃን ተመርቶ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በደስታ መቀበሉ የእያንዳንዱን ሰብአዊ ሕይወት ጥራትና ዋጋ ከነተገቢ ፍላጎቶቹ፣ መብቶቹና ዕድሎቹ ለማወቅና ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡ ይህ የአቀራረብ ዘዴ ለእነዚህ የአካል ጉዳተኞች እንክብካቤና አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል፣ ሰዎችም አካል ጉዳተኞችን እንዲቀርቡአቸውና በእያንዳንዱ የሕይወታቸው ደረጃ ፍቅር እንዲሰጡአቸው ያበረታታቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ለስደተኞችና ልዩ እንክብካቤ ለሚያሻቸው ሰዎች ጭምር የሚሰጥ ፍቅርና እንክብካቤ የመንፈስ ቅዱስ ምልክት መሆኑን በአጽንኦት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ሁለቱም ሁኔታዎች መሠረታዊ ሌሎችን በምሕረት ለመቀበልና ደካሞችን በማኅበረሰባችን ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲታቀፉ ለመርዳት ያለንን ቁርጠኝነት ለማወቅ የሚረዱ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡

አብዛኞቹ ቤተሰቦች ለአረጋውያን ትልቅ አክብሮት አላቸው፤ እንደ በረከትም ስለሚቆጥሩአቸው በፍቅር ይንከባከቡአቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላ፣ አረጋውያንን በመንፈስም ሆነ በማህበራዊ ኑሮ ረገድ ለማገልገል ቄርጠኝነት ላላቸው ተkማትና የቤተሰብ እንቅስቃሴዎች ልዩ ምሥጋና ያስፈልጋቸዋል፡፡… የወሊድ ምጣኔ እየቀነሰ ቢሆንም፣ የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረ ባለባቸው በኢንዱስትሪ በገፉ ኅብረተሰቦች ዘንድ አረጋውያን እንደ ሸክም ይቆጠራሉ፡፡ በሌላ በኩል፣ አረጋውያን የሚፈልጉት እንክብካቤ ብዙውን ጊዜ በዘመድ አዘማድ ላይ ውጥረት ይፈጥራል››፡፡ ‹‹በመጨረሻው የዕድሜ ደረጃ ላይ እንክብካቤና ፍቅር መስጠት፣ የዘመኑ ኅብረተሰብ የሞትንና የሞትን ዱካ ሁሉ ለማጥፋት ጥረት በሚያደርግበት በዛሬ ጊዜ፣ አስፈላጊነቱ ይበልጥ የጎላ ነው፡፡ ደካማና ጥገኛ የሆኑ አረጋውያን አልፎ አልፎ ለኢኮኖሚአዊ ጠቀሜታ ሲባል ያለ አግባብ ይበዘበዛሉ፡፡ ብዙ ቤተሰቦች የአንድን ሰው በጌታ የፋሲካ ምስጢር የመርካትና የመሳተፍ ስሜትን አስፈላጊነት በማጉላት ወደ ሕይወት ፍጻሜ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል እያሳዩን ነው፡፡ እጅግ በርካታ አረጋውያንም፣ በቁሳቁስም ሆነ በመንፈሳዊ ረገድ፣ በሰላማዊ የቤተሰብ ካባቢ መኖር እንዲችሉ በቤተክርስቲያን ተkማት ውስጥ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ የመዳን ዕድል የሌላቸው በሽተኞችን እንዲሞቱና ራሳቸውን እንዲያጠፉ መርዳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቤተሰቦች ሥጋት ሆኖአል፡፡ በብዙ አገሮች እነዚህ ድርጊቶች ሕጋዊ ሆነዋል፡፡ ቤተክርስቲያን፣ እነዚህን ልማዶች በጽኑ ከመቃወም ባሻገር፣ አረጋውያንንና አካል ጉዳተኛ አባሎቻቸውን ለሚንከባከቡ ቤተሰቦች እርዳታ ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ ይሰማታል››፡፡

እዚህ ላይ፣ በከፋ ድህነትና በትልቅ እጥረት ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ሁኔታ ለመጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ድሃ ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙአቸው ችግሮች እጅግ ፈታኝ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ አንዲት እናት ብቻዋን ልጅ ማሳደግና ወደ ሥራ ስትሄድ ልጅዋን ብቻውን መተው ካለባት፣ ልጁ ለማናቸውም ዐይነት ስጋትና ለሰብአዊ ዕድገት መሰናክል የተጋለጠ ሆኖ ያድጋል፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች፣ ቤተክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ምሕረት ማሳየት የሚገባት እናት ኮንናለች፣ ለብቻችን ትታናለች ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉአቸውን ሕጎችና ደንቦች ከማስቀመጥ ይልቅ መረዳትን፣ መጽናናትንና ተቀባይነት ማግኘትን በመስጠት ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ የጸጋን ፈዋሽ ኃይልና የወንጌል መልእክትን ብርሃን በመስጠት ፈንታ አንዳንዶች ያንን መልእክት ‹‹በማስረጽ›› ‹‹በሌሎች ላይ ወደሚወረወሩ ግዑዝ ድንጋዮች›› ይለውጡታል፡፡

ምንጭ፡ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይፋ ካደረጉት ጳጳሳዊ መልእክት፣ ከምዕራፍ ሁለት ከአንቀጽ 30-48 ላይ የተወሰደ።

14 July 2021, 09:46