ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገሩ ሕዝብ መልካም ዜና ነው
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስታኒስላቭ ከዚህ በፊት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስሎቫኪያን ከሰኔ 23–26/1987 ዓ. ም. መጎብኘታቸውን አስታውሰው፣ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም በስሎቫኪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ የሚመጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስታኒስላቭ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የእምነት አብሳሪ ከሆኑት ሁለት የአገራቸው ቅዱሳን፣ ከቅዱስ ክሪል እና ከቅዱስ ሜቶዴዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ጋር የተገናኘ መሆኑን በመልዕክታቸው አስረድተው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ማክበር ያስተማሩትም እነዚሁ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም አገራቸው የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በክብር ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጅት ላይ መሆኗን አስታውቀዋል። ከዚህም ጋር አያያዘው ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት እያንዳንዱ ዜጋ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ መልዕክት በሚገባ ማዳመጥ የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስታኒስላቭ አክለውም የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት በመከራ ውስጥ የሚገኙት፣ ከማኅበረሰቡ መካከል የተገለሉት፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ድጋፍን የሚሹትን በማስታወስ የሚቻለውን ዕርዳታ እንዲደረግላቸው የሚያሳስብ መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቤተሰብ ሕይወት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስታኒስላቭ፣ ቅዱስነታቸው ለወጣት ትውልድ ሕይወትም የሚጨነቁ መሆኑን ተናግረዋል።
የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስታኒስላቭ ስቮሌንስኪ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት እነዚህን ርዕሠ ጉዳዮች አስመልክተው መልዕክት እንደሚያስተላልፉ አስረድተው፣ ከሐዋርያዊ መልዕክታቸው ከፍተኛ መንፈሳዊ ብርታትን እንደሚያገኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።