ፈልግ

ጽንስ የማስወረድ ተግባር ከፍተኛ ጉዳት ጽንስ የማስወረድ ተግባር ከፍተኛ ጉዳት  

ጽንስ የማስወረድ ተግባር ከፍተኛ አደጋን እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ

በእንግሊዝ ውስጥ በግል የሚፈጸም ጽንስ የማስወረድ ተግባር በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ አደጋን እያስከተለ መሆኑን የእንግሊዝ ብጹዓን ጳጳሳት አስታወቁ። የእንግሊዝ መንግሥት በግል የሚፈጸም ጽንስ የማስወረድ ተግባርን ሕጋዊ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል። “የእንግሊዝ መንግሥት ጽንስ ማስወረድን ለማበረታታት የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች የተሳሳቱ ናቸው” ያሉት ብጹዕ አቡነ ጆን ሼሪንግተን ፣ መድኃኒቶችን በመቀበል በቤት ውስጥ በግል ደረጃ የሚፈጸሙ ጽንጽ የማስወረድ ተግባር በሴቶች አካል እና ስነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእንግሊዝ መንግሥት ያለፈው አውሮፓዊያኑ ዓመት 2020 ዓ. ም. ጽንስን ማስወረድ በማስመልከት ያወጣቸው ጊዜያዊ ደንቦች፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በቤታቸው ሆነው መድኃኒቶችን በግል በመውሰድ ጽንጽን እንዲያስወርዱ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል። እርምጃው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን መንግሥት አስታውቋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ጥሪ

ጽንስ ማስወረድ የሚፈልጉ ነፍሰ-ጡር ሴቶች ከሐኪሞቻቸው ጋር በሚለዋወጡት የስልክ መልዕክት በመታገዝ በፖስታ የሚላክላቸውን መድኃኒት ለአሥር ሳምንታት ከወሰዱ በኋላ የጽንስ ዕድገት ማጨናገፍ መቻላቸው ታውቋል። የአገሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተጠሪ እና የሕይወት መምሪያ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆን ሼሪንግተን በሰጡት ፈጣን ምላሽ በተግባሩ እጅግ መደንገጣቸውን ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ጆን በመልዕክታቸው “ምንም እንኳን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ብንገኝም፣ በመንግሥት በኩል የተወሰዱ ውሳኔዎች ሴቶችን ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጡ፣ የአካል እና የስነ-ልቦና ጉዳትን የሚያስከትሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አደገኛ ሕግ

ጽንስ የማስወረድ ተግባር አስመልክቶ የእንግሊዝ መንግሥት ያወጣቸው ደንቦች በአገሪቱ ውስጥ አነጋጋሪ በመሆን፣ ብሔራዊ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአገሪቱ ማኅበራዊ ደህንነት ክፍሉ አማካይነት የተለያዩ ጥናቶችን ማድረግ መጀመሩ ታውቋል። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ ጥናቶችን ካካሄደ በኋላ የሚያወጣቸው ደንቦች ሴቶች መድኃኒትን በግል በመውሰድ ጽንጽ ለማስወረድ የሚያደርጉት ተግባር ሕጋዊ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። የእንግሊዝ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተጠሪ እና የሕይወት መምሪያ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆን ሼሪንግተን የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተቃውሞ በመብለጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መንግሥት ጽንስ የማስወረድ ሕጋዊነት አስመልክቶ ያሚያወጣው ደንብ ቋሚ እንዲሆን የሚደረግ ከሆነ ውሳኔው በሴቶች ላይ ከፍተኛ የአካል እና የስነ-ልቦና ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን የማይቀበሉት መሆኑን አስገንዝበዋል። አክለውም በሺህዎች የሚቆጠሩ እና ገና ያልተወለዱ ነፍሳትን ለሞት በመዳረግ፣ አሰቃቂ እና አላስፈላጊ ኪሳራን የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል።

ከባድ የጤና እና የስነልቦና አንድምታዎች

ብጹዕ አቡነ ጆን ሼሪንግተን በመልዕክታቸው፣ ጽንስን ማስወረድ በማስመልከት መንግሥት የሚያወጣቸው ጊዜያዊ ደንቦች፣ በሴቶች አካል እና ስነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን የፓርላማ አባል የሆኑት ካርላ ሎካርት መሞገታቸውን ገልጸው፣ ምዕመናንም ድጋፍ እንዲሆኑ አሳስበዋል። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጭካኔያዊ ተግባር እንዲገታ፣ በሕይወት የመኖር መብትን እንዲከበር ካቶሊካዊ ምዕመናን በአንድነት ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።                               

07 June 2021, 15:07