ፈልግ

በቡቴምቦ-ቤኒ ወረዳ ጥቃት የደረሰባት ካቶሊካዊ ቁምስና በቡቴምቦ-ቤኒ ወረዳ ጥቃት የደረሰባት ካቶሊካዊ ቁምስና  

በዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ውስጥ በቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት መድረሱ ተነገረ

በዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፓብሊክ ቤኒ በተባለ አካባቢ በሚገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና እሑድ ሰኔ 20/2013 ዓ. ም የጦር መሣሪያ ጥቃት መድረሱ ታውቋል። በጥቃቱ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ከሥፍራው የወጣ ዘገባ አመልክቷል። የአገሪቱ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጥቃቱን አውግዘው “በዚያ አካባቢ አንድም ቀን የሰው ሕይወት ሳይጠፋ የሚያልፍበት ቀን የለም” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአካባቢው የተሰራጨው ዘገባ እንዳመለከተው እሑድ ሰኔ 20/2013 ዓ. ም በቡቴምቦ-ቤኒ ወረዳ በሚገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና ላይ የተፈጸመው የከባድ ጦር መሣሪያ ጥቃት ከደረሰው በላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበር ተገልጿል። እሑድ ማለዳ ላይ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በመንበረ ታቦት አካባቢ የተጠመደው ቦምብ ፈንድቶ በሁለት ሰዎች ላይ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋን ማድረሱ ታውቋል። ፍንዳታው እሁድ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለሚሰጥ የቅዱስ ሜሮን ምስጢር ሥፍራን በማዘጋጀት ላይ በነበሩ ሁለት ሴቶች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋን ያደረሰ መሆኑ ታውቋል። አደጋው የደረሰባቸው ሴቶች በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና የተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል።

በሰሜን ምሥራቅ ዴሞክራሲዊት ኮንጎ ሪፓብሊክ የምትገኝ ቡቴምቦ-ቤኒ ቁምስና ከረጅም ዓመታት ወዲህ ጥቃት ሲደርስባት በነበረው በሰሜን ኪቩ ክፍለ ሀገር የምትገኝ ወረዳ መሆኗ ታውቋል። በቤተክርስቲያኗ ላይ ጥቃት ያደረሱት መሣሪያ ታጣቂዎች ከእስላማዊ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከ ጼደቅ ሲኩሊ ገልጸዋል። አቡነ መልከ ጼደቅ ያለፈው ወር በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መሣሪያ ታጣቂዎች ተከታታይ ጥቃት ሲፈጸሙ መቆየታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። መሣሪያ ታጣቂዎቹ ቤተክርስቲያንን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን የጥቃት ዒላማ አድርገው መቆየታቸውን አስረድተዋል። አክለውም ታጣቂዎቹ በአካባቢ አንድም ቀን የሰው ሕይወት ሳይገድሉ የሚውሉበት ቀን አስታውቀው ሆስፒታል ውስጥ ታመው የተኙትንም ጭምር የሚገድሉ መሆኑን ገልጸዋል።  

በሰሜን ምሥራቅ ዴሞክራሲያዊት ኮንጎ በምትገኝ ቤኒ ወረዳ እ. አ. አ ከ2013-2020 ዓ. ም በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ 7,500 ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸው፣ መንደሮች በእሳት መጋየታቸው፣ መሥሪያ ቤቶ መዘረፋቸው፣ እንስሳት እና የእርሻ ሰብሎች እንደዚሁ መዘረፋቸው ታውቋል። ባለፈው መጋቢት ወር የአገሪቱ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባስተላለፈው መልዕክት፣ መሣሪያ ታጣቂ አማጺያን በወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ላይ የሚያደርሱትን የሞት አደጋ እንዲያቆሙ አሳስቦ፣ የንጹሃን ደም በምድር ላይ እየጮኸ እንደሚገኝ ገልጿል።

የዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ መንግሥት በአካባቢው የሚገኝ ጸጥታ አስከባሪ ኃይል ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተባብሮ የአካባቢውን ጸጥታ ለማስከበር ትክክለኛ ትዕዛዝ እንዲሰጥ አሳስቧል። የጳጳሳቱ ጉባኤ በማከልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታ አስከባሪ ኃይልም በበኩሉ የአገልግሎት ቀጣናውን በማስፋት የጦር መሣሪያ ትጥቅን በማስፈታት በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ሕዝቦች በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ እንዲያመቻች፣ በአካባቢው የሚገኙ ሕዝባዊ መሪዎችን የሚያሳትፍ የሰላም ጥረቶችን ለማኅበረሰቡ ማስተማር እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የዴሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አክሎም፣ በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ ወገኖችን የሚያሳትፍ፣ የዜጎችን ማኅበራዊ እሴቶች የሚያሳድግ የጋራ ውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ አሳስቧል። “ጦርነት የመከራ ሁሉ ምንጭ ነው” ያለው የጳጳሳቱ ጉባኤ፣ ጦርነት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚጎዳ፣ የመጭውን ትውልድ የወደፊት ተስፋ የሚያጨልም መሆኑን ገልጾ፣ ልዩነት እና መከፋፈል የሚታይባቸው ወገኖች በፍቅር እና በአንድነት ዓላማ ተነሳስተው የአመጽ ምንጭ የሆነውን ክፋት ማሸነፍ የሚችሉ መሆኑን አስታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በመጨረሻም በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚደርሰው መከራ በመላው አገሪቱ ላይ የሚደርስ መከራ በመሆኑ፣ በአካባቢው ሰላም እንዲወርድ የጋራ ጸሎት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አደራ ብሏል።         

30 June 2021, 13:17