ፈልግ

በዓለማችን በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን በዓለማችን በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን  

በዓለማችን በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ለማቋቋም 123 ሚሊዮን ዩሮ ያስፈልጋል ተባለ።

በዓለማችን በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን እና ድሃ ማኅበረሰብን በመርዳት ወደ መደበኛ ኑሮአቸው እንዲመለሱ የሚያስችል የ123 ሚሊዮን ዩሮ እገዛ የሚያስፈልግ መሆኑ ታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚታዩ ማኅበራዊ ችግሮችን ማቃለል እንዲቻል ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ሲነገር ከፕሮጀክቶቹ ማካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙና ይበልጥም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት ነው ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለማችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ ከለጋሽ አገሮች እና ግለሰቦች የሚሰጥ የዕርዳታ መጠን ከጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ጥሩ ተስፋ መሆኑን በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ዕርዳታን የሚያደርግ ጳጳስዊ ፋውንዴሽን እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም ባቀረበው ዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት በበርካታ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን እና ድሃ ማኅበረሰብ ለከፈተኛ ችግር መዳረጉን፣ ብዙዎችን ያለ ሥራ እና ዕለታዊ ቀለብ ማስቀረቱን፣ በቁጥር በርካታ የሆኑ ካህናትን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያትን ለችግር የዳረጋቸው መሆኑን ዓለም አቀፍ ጳጳስዊ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቶማስ ሄይን ጀልደርን አስረድተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ፍርሃት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው ቢሆንም ፍርሃቱ መሠረተ ቢስ መሆኑ ተረጋግጦ የበጎ አድራጊዎች ልገሳ ብዙም ሳይቆይ መድረሱን በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ዕርዳታን የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ጳጳስዊ ፋውንዴሽን የጣሊያን ቅርንጫፍ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አልፍሬዶ ማንቶቫኖ አስታውቀዋል። 

ስደት እና መከራ የደረሰባቸውን የዓለማችን ክርስቲያኖችን እና ድሃ ማኅበረሰብን መርዳት እንዲቻል በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ጽሕፈት ቤቶች በኩል የተሰበሰበው የዕርዳታ መጠን 122.7 ሚሊዮን መድረሱ ታውቋል። በዕርዳታ የተገኘው ገንዘብ እ. አ. አ በ2019 ዓ. ም ከተሰበሰበው የገንዘብ መጠን ጋር ሲወዳደር በ16.4 ሚሊዮን መጨመሩ እና ይህም 15.4 ከመቶ መሆኑ ታውቋል። በማከልም ከጣሊያን የተሰበሰበው የዕርዳታ መጠን 20 ከመቶ ጨምሮ መገኘቱን የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ጽሕፈት ሪፖርት ገልጾ፣ በዓለማችን ውስጥ ከተለያዩ አገራት የተሰበሰበው የገንዘብ ዕርዳታ ከመቶ በላይ በሚሆኑ ፕሮጄክቶች በኩል በስደት ለሚገኙ ቤተክርስቲያናት እና ድሃ ማኅበረሰቦች እንዲደርስ መደረጉን ዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል።      

ዕርዳታው የሚደርሳቸው አህጉራት

በዕርዳታ የተሰበሰበው ገንዘብ ከጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አስተዳደር እና ከለጋሽ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የተገኘ ሲሆን በተለያዩ አገሮች ውስጥ ተዘርግተው በሚንቀሳቀሱ ፕሮጄክቶች አማካይነት የሚደርስ፣ ከፕሮጀችቶቹ በተጨማሪ የጸሎት ዝግጅቶችን ለማስፈጸም የተዋቀሩ 4,758 ፕሮጄክቶች በ138 አገሮች ውስጥ መኖራቸው ታውቋል። ከለጋሽ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከተገኙት ዕርዳታዎች መካከል አንድ ሦስተኛው ወደ አፍሪካ አህጉር የተላከ መሆኑን የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ዓመታዊ ሪፖርት አመልክቷል። ከሌሎች ዓመታት በተለየ መልኩ ቅድሚያን በመስጠት ዕርዳታው ለሶርያ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና የሽብር ተግባርን በመዋጋት ላይ ለሚገኙ የሰሃል አገራት እንዲደርስ መደረጉን ሪፖርቱ አክሎ አስታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተፈናቃዮችን ሕይወት የበለጠ አስቸጋሪ እንዳደረገው ሪፖርቱ አስታውቆ እነዚህን ተፈናቃዮች ተቀብሎ ዕርዳታን በማድረስ ላይ የሚገኝ ብቸኛው የቤተክርስቲያን ተቋም መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል። ልዩ ዕቅድ ተይዞለት አራት ሚሊዮን ዩሮ በመካከለኛው ምስራቅ በቁጥር ከፍተኛ ክርስቲያኖች ወደሚገኝባት ሊባኖስ መላኩን ሪፖርቱ አስታውቆ እ. አ. አ ነሐሴ 4/2020 ዓ. ም በቤሩት ከተማ የተነሳው ፍንዳታ ያስከተለውን ማኅበራዊ ቀውስ ሪፖርቱ አስታውሷል።

የመልሶ ግንባታ ፕሮጄክቶች

የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ጽሕፈት ሪፖርት አክሎም በተለያዩ አገራት በተፈጸሙ የአሸባሪዎች ጥቃት የተጎዱ ወይም የወደሙ ቤተክርስቲያናት፣ ቁምስናዎች፣ ገዳማት እና የዘርዕ ክህነት ትምህርት ቤቶች ቁጥር 744 መሆኑን ገልጾ ዕርዳታው እነዚህን ተቋማት መልሶ ለመገንባት የዋለ መሆኑን አስታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ በዓለማችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቤተክህነት ወገኖችን የጎዳው መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቆ፣ በስደት ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ዕርዳታን የሚያደርግ ጳጳስዊ ፋውንዴሽን እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም ለዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቶችን እና በቁጥር ከ18,000 በላይ የሚሆኑ የቤተክህነት አባላትን የረዳ መሆኑን አስታውቋል። ዕርዳታው የዋለበት ሌላው ዘርፍ የሐዋርያዊ አገልጋዮች የመጓጓዣ አገልግሎት መሆኑን ሪፖርቱ ገልጾ፣ ይህን ለማሟላት 783 ብስክሌቶችን፣ 280 መኪኖችን፣ 166 ሞተር ብስክሌቶችን፣ 11 ጀልባዎችን፣ ሁለት መለስተኛ አውቶቡሶችን እና አንድ ትልቅ አውቶቡስን በግዥ ያቀረበ መሆኑን አስታውቋል። 

21 June 2021, 16:45