ፈልግ

“Oasis” የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ፋውንዴሽን “Oasis” የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ፋውንዴሽን  

በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠና የጋራ ውይይት መድረክ

በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት፣ ከሁለቱም የእምነቱ ተከታዮች በኩል የታዩ ፍላጎቶችን እና የሚቀርቡ ጥያቄዎችን መሠረት ያደረገ የቪዲዮ ቅንብር መዘጋጀቱ ታውቋል። የቪዲዮ ቅንብሩ የቀረበው “ዩቲዩብ” በተባለ የማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ሲሆን፣ ውይይቱ የተዘጋጀው “Oasis” በመባል የሚታወቅ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ የእስልምና እና የክርስትና እምነቶች የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ፋውንዴሽን መሆኑ ታውቋል። የፋውንዴሽኑ ዋና መስራችም ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ስኮላ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለእስልምና እምነት ተከታዮች የክርስትናን እምነት መሠረቶች በማብራራት በሃይማኖቶች መካከል የሚከሰቱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስወገድ የሚያስችል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ የቪዲዮ ቅንብር በዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል መቅረቡ ታውቋል። የቪዲዮ ቅንብሩ በሁለቱ እምነቶች መካከል ያሉትን ልዩነቶች እና የጋራ እሴቶችን ለይቶ በማውጣት ለእምነቶቹ ተከታዮች አብራርቷል። “ምክንያት እና ተስፋ” በሚል ርዕሥ የቀረበውን ዝግጅት ያስተባበረው “Oasis” በመባል የሚታወቅ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ የእስልምና እና የክርስትና እምነቶች የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ፋውንዴሽን መሆኑ ተገልጿል።

የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስወገድ

ካለፉት ዓመታት ወዲህ በቁጥር በርካታ የሚባሉ ሙስሊሞች የክርስትናን እምነት መሠረቶች ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸው ለመገንዘብ ችለናል ያሉት “Oasis” በተባለ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የእስልምና እና የክርስትና እምነቶች የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ፋውንዴሽን ሳይናሳዊ ጥናቶች መሪ እና በካቶሊካዊ ተቋም የአረብኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር ማርቲኖ ዴዝ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ከእስልምና እምነት መምህራን የቀረቡ እና የክርስትና እምነትን የሚመለከቱ አነጋጋሪ ትምህርቶች፣ አንድ ወገን ብቻ ያገናዘቡ አስተያየቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መቅረባቸውን ፕሮፌሰር ማርቲኖ ዴዝ ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ወደ ኢራቅ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የተመለከቱ በርካታ ሙስሊሞች አድናቆታቸውን መግለጻቸውን ፕሮፌሰር ማርቲኖ አስታውሰዋል። በመሆኑም ባሁኑ ወቅት በበርካታ ሙስሊሞች ልብ ውስጥ የተፈጠረው እርስ በእርስ የመተዋወቅ ፍላጎት፣ በተለይም ከካቶሊክ እምነት በኩል የታየው የወንድማማችነት መንፈስ መሠረቱ ከወዴት እንደሆነ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት የቀሰቀሰ መሆኑን ፕሮፌሰር ማርቲኖ ገልጸዋል።     

በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች መካከል ያሉትን ግንኙነቶችን እና ልይነቶችን የሚገልጹ፣ በዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የቀረቡት ትምህርቶች እስካሁን ሦስት መሆናቸውን ፕሮፌሰር ማርቲኖ ገልጸው፣ ቅንብሮቹ ለጊዜው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ መሆናቸውን እና በሌሎችም ቋንቋዎች ማለትም በጣሊያንኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ መሆኑን አስረድተዋል። የቅንብሮቹ ርዕሦችም “ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በቁርዓን” ፣ “ብዙ ነቢያት ነገር ግን አንድ መልዕክት” ፣ “የኢየሱስ ሚና በቁርዓን” ፣ “የአዳኙ ኢየሱስ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ” የሚሉ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ማርቲኖ ገልጸዋል። የእስልምና እና የክርስትና እምነቶች ያሏቸው ግንዛቤዎች በሁለቱ የእምነት ሕግጋት የሚመሩ ሁለት አስተሳሰቦች መኖራቸውን አስረድተው፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት የተዘጋጁ ሦስቱ የቪዲዮ ትምህርቶች በሁለቱ እምነቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እና ልዩነት የሚገልጹ መሆኑን አስረድተዋል። ሁለተኛው የቪዲዮ ቅንብር፣ እንደ እስልምና እምነት ከሆነ፣ ኢየሱስ ነቢይ እና መልዕክተኛ እንደሆነ የሚገልጽ እና ይህም በእግዚአብሔር እና በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መካከል ያለውን መሠረታዊ ግንኙነት የሚገልጽ መሆኑን ፕሮፌሰር ማርቲኖ  ገልጸው፣ ሦስተኛው የቪዲዮ ቅንብር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሚያወሳ መሆኑን አስረድተዋል።

የእምነት ብልህነት እንዲሠራ ማድረግ

በሁለቱ እምነቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እና ልዩነት በትክክል በማወቅ “ምክንያት እና ተስፋ” በሚል ርዕሥ የቀረበው ዝግጅት ዓላማ የክርስትና እምነት መሠረቶችን ለሌሎች ለማሳወቅ እና “ክርስቲያኖች ማን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሆኑን ፕሮፌሰር ማርቲኖ  ገልጸዋል። ይህ ጥያቄ የእስልምና እምነት ተከታዮች ጥያቄን ለመመለስ ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ወገኖችም የእመነታቸውን እውነት ለማወቅ የሚረዳ መሆኑን አስረድተው፣ ዋናው ነጥብ ከእስልምና እምነት ተከታዮች በኩል የሚመጡ ጥያቄዎች ምክንያታዊ እና በሰላማዊ መንገድ የሚቀርቡ ከሆነ የእምነት ብልህነት ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን አስረድተዋል።

ለክርስቲያኖች የቀረበ ተጨማሪ እሴት

አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ “እግዚአብሔር አንዱ ልጁን፣ ነብዩ ኢየሱስ ክርስቶስን ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ግልጽ አልሆነልኝም” በማለት ጥያቄ ማቅረቡን ፕሮፌሰር ማርቲኖ አስታውሰው፣ ይህ ጥያቄ አንዱን ከሌላው ለማበላለጥ ወይም ለማሳነስ የቀረበ አለመሆኑ አስረድተው፣ በእርግጥም በጥያቄው ላይ ይበልጥ እንድናስብበት የሚጋብዝ ሰላማዊ ጥያቄ መሆኑን በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የእስልምና እና የክርስትና እምነቶች የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ፋውንዴሽን ሳይናሳዊ ጥናቶች መሪ እና በካቶሊካዊ ተቋም የአረብኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር ማርቲኖ ዴዝ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አስረድተዋል።    

03 June 2021, 16:21