ፈልግ

በሚያንማር ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ካቶሊካዊ ቁምስና በሚያንማር ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ካቶሊካዊ ቁምስና 

በሚያንማር ውስጥ በቤተክርስቲያን ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ

በሚያንማር ውስጥ በምትገኝ የሰላም ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊካዊ ቁምስና ቤተክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተነገረ። ፊደስ የተሰኘ የቤተክርስቲያን ዜና ማዕከል እንዳስታወቀው ከሁለት ሳምንታት ወዲህ ካቶሊካዊ ተቋማትን ያነጣጠር ጥቃት ሲፈጸም መቆየቱን አረጋግጧል። ጥቃቱን ፈጻሚዎቹ ቤተክርስቲያኗን የሚቃወሙ የመንግሥ ወታደሮች መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዜና ማዕከሉ በጽሑፉ እንዳረጋገጠው፣ በሚያንማር፣ ካያክ ግዛት ውስጥ በምትገኝ የሰላም ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመው ጥቃት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ መሆኑ ታውቋል። በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ የሞት እና የመቁሰል አደጋ ባይኖርም በአካባቢው በሚገኙት መኖሪያ ቤቶች ላይም ጉዳት መድረሱ ታውቋል። ውድመት ደርሶባታል በተባለችው ቤተክርስቲያን ጎን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ደናግል የሚመራ አንድ የአረጋዊያን ማረፊያ ማዕከል የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ማዕከል ጥቃቱን የሸሹ 150 ሰዎች ዕርዳታ እያገኙ መሆናቸው ሲነግር፣ ከተረጅዎች መካከል ሴቶች፣ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞች ያሉበት መሆኑ ታውቋል። በመንግስት ታጣቂዎች የሚፈጸመውን ጥቃት ለማምለጥ በርካታ ሰዎች የመኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ የተገደዱ ሲሆን በካያ ግዛት ሎይካው ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ ሰባት ቁምስናዎች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸው ታውቋል።

የሰላም ጥሪ

ጥቃት ደርሶባታል በተባለች የሰላም ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስና ዙሪያ በቁጥር 812 ካቶሊካዊ ምዕመናን የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ምዕመናን ከካህናት፣ ከደናግል እና ከትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በኩል የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲያገኙ መቆየታቸው ታውቋል። በካባቢው በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት  የኢየሱሳዊያን ማኅበር አባል፣ ክቡር አባ ዊልቤርት ሚሬ ለመንግሥት ወታደሮች የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸው፣ በቤተክርስቲያን ላይ የሚፈጸም ጥቃት እንዲቆም በተለይም አቅመ ደካማ እና ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ እና ጥገኝነትን እና ከለላን ጠይቀው በየቁምስናዎች ውስጥ በሚገኙት ሰዎች  ላይ የሚደርስ አደጋ እንዲቆም መጠየቃቸው ታውቋል። ነገር ግን ክቡር አባ ዊልቤርት ላቀረቡት የሰላም ጥሪ መልስ አለማግኘቱ ታውቋል። ክቡር አባ ዊልቤርት ስለ ሁኔታው ሲገልጹ ጥቃቱን በማድረስ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ወታደሮች በሕዝቡ ላይ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ርኅራሄ የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ከአካባቢው የሚወጡት የቤተክርስቲያኒቱ ዜናዎች እንዳመለከቱት፣ ወታደሮቹ በቤተክርስቲያኗ ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በማሳደግ በደቡብ ካያንታር በሚገኝ በቅዱስ ልበ ኢየሱስ ካቶሊካዊ ካቴድራል ላይ በፈጸሙት ጥቃት የአራት ሰዎች ሕይወት መጥፋትቱን ገልጸዋል። የወታደሮቹ ጥቃት ከዚህም በተጨማሪ በፌኮን ሀገረ ስብከት በሚገኝ በቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል፣ በመታነጽ ላይ በምትገኝ የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ ጉዳት ማድረሱ ሲነገር፣ በቁጥር 1,300 ሰዎች በሚገኙበት ከፍተኛ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ላይ በተከፈተው ጥቃት አንድ በጎ ፈቃደኛ መገደሉ ታውቋል።                           

08 June 2021, 16:26