ፈልግ

ስደተኞች፣ ከጥገኝነት ጠያቂዎች እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ስደተኞች፣ ከጥገኝነት ጠያቂዎች እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች 

ካርዲናል ታግለ፣ መንግሥታት ለስደተኞች የሚሰጡትን ዕርዳት ማቋረጥ የለባቸውም አሉ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የስደተኞችን ሰብዓዊ ክብር ሳይቋረጥ እንዲከበር በማሳሰብ “አብረን እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል በመመራት ሲያካሂድ የቆየው ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ መጠናቀቁን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታወቀ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አብረን እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ መስከረም 27/217 ዓ. ም ያስጀመሩት ቅስቀሳ ዋና ዓላማ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በስደተኞች ላይ ያለውን አመለካከት ለማስቀየር እና ለመለወጥ ያቀደ መሆኑ ታውቋል። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚመራ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት ያስጀመረው ቅስቀሳ በመጭው ሰኔ 13/2013 ዓ. ም በሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰደተኞች ቀን የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል። በቅስቀሳው የእስካሁን ሂደት ላይ ለመመወያየት በቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ለመስጠት የቀረቡት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሲሆኑ ከእርሳቸውም ጋር በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚመራ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት ፕሬዚደንት መሆናቸው ታውቋል። ሁለቱ የቅስቀሳው አስተባባሪዎች በመግለጫቸው እንዳረጋገጡት በጎ አድራጊ ድርጅታቸው ባለፉት ዓመታት ውስጥ የስደተኞችን ሕይወት በቅርብ በመከታተል ድኅነታቸውን እና መከራቸውን ለመጋራት የቻለ መሆኑን አስረድተው፣ ስደተኞችን መመልከት ያለብን በቁጥራቸው ብዛት ሳይሆን በስብዕናቸው መሆን እንዳለበት ማስገንዘብ መቻላቸውን ገልጸዋል።

መንግሥታት በራስ ወዳድስነት በሽታ መጠቃት የለባቸውም

ከስደተኛ ቤተሰብ የመጡት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ የስደትን አስከፊነት የሚያውቁ ሰዎች ስሜት በማስታወስ እና ይህን ስሜት በግል ከሚያገኟቸው ስደተኞች ፊት በማንበብ የሚረዱ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥታት በራስ ወዳድነት በሽታ በመጠቃት ለስደተኞች የሚያቀርቡትን ዕርዳት ማቋረጥ እንደሌለባቸው አሳስበዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሰዎች መካከል ያለውን ወዳጅነት እና መተጋገዝ የበለጠ እንዲያድግ የሚያደርግ መሆን አለበት ብለዋል። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሚመራ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት አስተባባሪነት የተጀመረው ቅስቀሳ በአስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን ከስደተኞች ጋር ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ አሳስበው፣ ዓላማውም በስደተኞች፣ በጥገኝነት ጠያቂዎች እና በተራው ሕዝብ ጋር ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት እና ትውውቅ እንዲጎለብት ማድረግ እንደሆኑ አስረድተዋል። ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ አክለውም ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ በየአገራቱ የሚገኙ 162 ካቶሊካዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅት ያስተባበሯቸው 130 ዕቅዶች በተግባር ላይ መዋላቸውን አስረድተዋል። 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቅስቀሳው እንዲጀምር አድረገዋል

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚመራ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት ያተባበረው ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተለያዩ በጎ ተግባራትን ሲፈጽም የቆየ ሲሆን ከእነዚህም መካከል “ምግብ እንጋራ” በሚል ቅስቀሳው በየአገራቱ በሚገኙ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ማዕከላት ዕለታዊ ምግብን ያደለ ሲሆን በተጨማሪም ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ያስጀመሩትን “የአንድነት ጉዞን” በሮም በማዘጋጀት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ማኅበራት እና ግለሰቦች ከስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር በመሆን የእግር ጉዞ መከናወኑ ታውቋል።

የተስፋ ሻማዎች ይበራሉ

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት ከስደተኞች፣ ከጥገኝነት ጠያቂዎች እና ከአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጋር ሊኖር የሚገባውን አንድነት ማሳደግ እንዲቻል ዓለም አቀፍ ዘመቻን በመቀላቀል በየአገራቱ በሚዘጋጁ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ የሚቻል መሆኑን አስታውቋል። በተጨማሪም ከሰኔ 8/2013 ዓ. ም ጀምሮ “caritas.org” በተሰኘው ማኅበራዊ ድረ ገጽ በመክፈት በሚፈልጉት አገር ውስጥ መልካም ተስፋን የሚገልጽ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት መፈጸም የሚቻል መሆኑን አስታውቋል። የመልካም ምኞታቸው መልዕክት በመጽሐፍ ታትሞ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሚቀርብ መሆኑን ቅስቀሳውን አስተባባሪ የሆነው ካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት አስታውቋል።       

16 June 2021, 16:22