ፈልግ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት አርማ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት አርማ  

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ያስተላለፈው መልእክት

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ለመላው ምዕመናንና በጎ ፊቃድ ላላቸው የሀገራችን ሕዝቦች በሙሉ ያስተላለፈው የቅድመ ምርጫ መልዕክት ‹‹አቤቱ ፍርድህን ለንጉሥ ስጥ ሕዝብህንም በጽድቅ ችግረኞችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ›› (መዝ. 72. 1-2)

1.     ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደምንረዳው የእስራኤል ሕዝቦች እግዚአብሔር መልካም መሪ እንዲሰጣቸዉ በጠየቁት ጊዜ በነፃነት መሪያቸዉን እንዲመርጡ ፈቀደላቸዉ፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ምኞታችን ከዚህ የተለየ ሳይሆን የዘመናት አብሮነታችንና፣ በመከባበር፣ በመደጋገፍ መኖራችንን አስጠብቆ የሚያቆየን መልካም መሪ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህም በ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ እግዚአብሔር መልካም መሪ እንዲሰጠን እየጠየቅን፤ ለምርጫዉ ሰላማዊነትና ለሀገራችን ደኅንነት እንሻለን፣ ፀሎታችንም ነው፡፡

2.     መልካም አገልጋይ የሆነ መሪ የሚወጣዉ ከሕብረተሰባችንና ከልጆቻችን በመሆኑ፤ በሚመጣዉ 6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ እግዚአብሔር ከልጆቻችን ዉስጥ በእኩልነት፤ በፍትሃዊነት፤ እና መልካም አርአያ በመሆን የሚያገለግል መሪ እንዲሰጠን በጸሎት መበርታት አለብን፡፡ መልካም መሪ በሕዝባችን ዉስጥ እኩልነት፤ ፍትሃዊነት፤ መልካም አስተዳደርና ሰላም እንዲረጋገጥ በጥበብ ይመራል፡፡ ለእግዚአብሔር የታመነ፣ በጥበብ የሚያስተዳድርና በትክክል የሚመራ መሪ እንዲኖረንም እኛ እንደ ሕብረተሰብ በልጆቻችን ዉስጥ መልካም ዘር መዝራት አለብን፡፡ የመልካም መሪ መለያም በዋናነት በእኩልነትና በፍትሃዊነት ማገልገል ነዉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ከ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ የምንጠብቀዉ ሕዝባችንን ለማገልገል የሚወዳደሩ አገልጋዮች የመልካም መሪን መርሆዎች ለመተግበር የተዘጋጁና ብቁ የሆኑ እንዲሆኑ ነዉ፡፡ ይህም ማለት በሰዎች መሃከል ልዩነትን የሚፈጥሩ ነገሮች እንዲቀረፉና አንድነትን የሚያጎልብቱና የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቁ የሀገርን ዕድገት የሚያፋጥኑ ጉዳዮች እንዲጎለብቱ ትኩረት የሚያደርግ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ይህም ተግባር የፖለቲካ ማህበረሰቡንና ሕዝቡን የበለጠ ያቀራርባል የሚል እምነት አለን፡፡ አሁን ባለዉ ሁኔታ ደግሞ ሕዝባችን እነዚህን ተግባራት ማለትም አድሎአዊነትን፤ በዘር መከፋፈልን፤ መፈናቀልን፤ መሰደድን፤ ሙስናንና እነዚህን መሠረት ባደረጉ በተለያዩ ግጭቶች የንፁሃን ዜጎች ሕይወት መጥፋትን፤ የንብረት መዉደምን ወዘተ ደግመዉ እንዲከሰቱ አይፈልግም፡፡ በሌላ አነጋገር 6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፤ ፍትሃዊ፤ ዴሞክራሲያዊ፣ ተአማኒነት ያለዉና  ሰላማዊ እንዲሆን የሁላችንም ምኞትና ጸሎት ነው፡፡

3.     ሕዝባችን ከሚያነሳቸዉ መሠረታዊ የዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በመነሣት ከ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ሊነሱ ለሚችሉ ዉዝግቦች የፖለቲካ ማህበረሰቡ ውይይትና ድርድርን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መዉሰድ ይኖርበታል እንላለን፡፡ በተቃራኒዉ መጓዝ ግን ለማንም እንደማይጠቅም መገንዘብ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም የሕይወት መጥፋትና የንብረት መዉደም ማንንም ተጠቃሚ እንደማያደርግ እያየነዉ ያለ እዉነታ ስለሆነም ጭምር ነዉ፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ለጋራ ጥቅም መከበር የመሥራት ግዴታ አለብን፡፡ የፖለቲካ ማህበረሰብ (በሥልጣን ላይ ያለዉና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር) ይህንን የማመቻቸት ኃላፊነት አለባቸዉ፡፡ ሰለሆነም እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ሀገሪቷን ለሚያስተዳድረዉ መንግሥት፣ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሚመለከታቸዉ ሁሉ የምናሳስበዉ፡-

3.1. 6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፡ ገለልተኛ፤ ፍትሃዊ፤ ተአማኒ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

3.2.  ለሕዝባችንም እንዲሁ ምርጫዉ የምንፈልጋትን ሀገር ለመገንባት ያስችለን ዘንድ ሁላችንም በያለንበት የሕዝቦች ደህንነት እንዲረጋገጥ የየበኩላችንን ኃላፊነት እንድንወጣ አደራ እንላለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሕዝቦች መሃከል የበለጠ መቀራረብና መግባባት እንዲሰፍን ለሚነሱ ጥያቄዎችም ወቅታዊ ምላሽ በመስጠት ለምርጫዉ ፍትሃዊነትና ሰላማዊነት የበኩሉን ኃላፊነት በገለልተኝነት እንደሚወጣ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የምንመርጠውን መሪ የምንለካው ባለው አመራር ብስለት ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም የቆመ ለሀገር አንድነት የሚተጋ ፤ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚገባውን ክብርና መብት የሚሰጥ እንዲሁም ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሔረሰብ በፍትሐዊ መንገድ የሚያስተዳደር በመሆኑ እንጂ በብሔሩ ወይም በቋንቋው መሆን እንደሌለበት ህዝባችን እንዲገነዘብ እንፈልጋለን፡፡

3.3.  በሀገራችን ብሔርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉና የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች ሊሰጣቸዉ የሚችሉ ግጭቶች በኦሮሚያ ፣ በትግራይ ፣ በአማራ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ በሱማሌ ፣ በአፋር ፣ በደቡብ እና በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ብዙዎችን አፈናቅለዋል፤ የብዙ ንፁሃን ዜጎቻችንን ሕይወትም ቀጥፈዋል ፣ ሴቶች እህቶቻችን ተደፍረዋል፣ ንብረትንም ወድሟል፡፡ በአንድ ሀገር በወንድማማችነትና በእህትማማችነት፤ በመተሳሰብና በመከባበር የምንኖር ሕዝቦች ሆነን ሳለ በመሃከላችን ይህ መከሰቱ በእጅጉ ያሳዝነናል፤ ያስቆጨናል፡፡ 6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅና አብሮነታችን ተጠናክሮ የሀገራችንም ዕድገት እንዲፋጠን መንግሥት በዜጎች ላይ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት እንዳይደርስ አስፈላጊዉን ጥበቃ እንዲያደርግ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡

3.4.  የሀገራችን መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የፀጥታና ደኀንነት አካላት በሙሉ፤ አሁን ያለንበት ወቅት የምርጫ ወቅት በመሆኑ የእናንተ ከመላዉ ሕዝባችን ጎን መሆን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ይጠበቃል፡፡ ያለንበትን የምርጫ ዝግጅት ተከትሎ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሏቸው ክፍሎች በሀገራችን ላይ የተለያዩ ጫናዎችን እያደረጉ እንደሆነም እንገነዘባለን፡፡ የዚህ የ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅ  ለሀገራችን ታላቅ ተስፋ እንደሚሆን በመገንዘብ ከወትሮው በተለየ ለሀገራችንና ለሕዝቦቿ ደህንነት፤ እንዲሁም ለምርጫዉ ፍትሃዊነትና ሰላማዊነት የተለመደዉን የሕዝብ ወገንተኛነታችሁን አስጠብቃችሁ ለሰላማችን ከሀገራችን ሕዝቦች ጋራ እንድትቆሙ አደራ እንላለን፡፡

3.5. ወጣቶቻችን ደግሞ የነገ ሀገር ተረካቢዎች መሆናችሁን በመረዳት በገለልተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዉስጥ የመሳተፍ ልምዱን እንድታዳብሩና ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ለመምጣት የምርጫ ካርድ ብቻ አስፈላጊ መሆኑን ለሕብረተሰባችን በማሳወቅ የሀገራችንና የሕዝቦችዋ ደህንነት እንዲጠበቅ የበኩላችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡

3.6. በቤተሰብ ደረጃም ይሁን በሀገር ደረጃ ለሚነሱ ችግሮች/ግጭቶች መፍትሔ በማፈላለግ ሴቶች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በመሆኑምየሀገራችን ሴቶች 6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ከማንኛዉም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ ሆናችሁ የበኩላችሁን የሰላም ተልዕኮ እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡

3.7. ለሀገራችን ሕዝቦች ዕድገትና ብልጽግና መሠረት የሆነው የአባይ ግድብ ወደ መጨረሻዉ ምዕራፍ እየተጓዘ መሆኑ ግልፅ ነዉ፡፡ ይሁንና ከታችኛዉ የተፋሰስ ሀገሮች በተለይም ከግብፅና ከሱዳን ጋር ያለዉ ድርድር አለመቋጨቱ ያሳስበናል፡፡ በመሆኑም ሰላም ወዳድነታችንን በተግባር ለማረጋገጥ ከግብፅና ከሱዳን ጋር እየተካሄደ ያለዉ ድርድር ሀገራችንን በማይጎዳና በዉሃችን የመጠቀም መብታችንን ባረጋገጠ እና የሌሎችም የተፋሰስ ሀገራት ፍትሃዊ ጥቅም ባልነካ መልኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊዉን ሁሉ እንዲያደርግ አደራ እንላለን፡፡ ይህም ሂደት በጉርብትናችን ላይ ያንዣበበዉን ‹‹ጥቁር ደመና›› ይገፍፋል፣ ጉርብትናችንንም ያጠናክራል ብለን እናምናለን፡፡

3.8. ሀገራችንና ሕዝቦቿ ከወትሮው የበለጠ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተጎዱ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በመሆኑም ለመላዉ የሀገራችን ሕዝቦች የምናስተላልፈዉ መልዕክት ራሳችንን ከዚህ ወረርሽኝ ለመታደግ አስፈላጊዉን ጥንቃቄ በማድረግ ከመንግሥት የሚተላለፉ መመሪያዎችንም በጥንቃቄ እንድንተገብር አደራ በማለት ነዉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በዓለማችን እየታየ ያለዉ የሰዉ ልጅ ክብር መጓደል፤ የአረጋዉያን መጎሳቆል፤ የሰዎች የእርስ በእርስ አለመተማመን በሰዎች ሁለንተናዊ ወንድማማችነትና በእህትማማችነት ላይ ጥላን ጋርዷል፡፡ ስለዚህ ሰዉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ክቡር ፍጡር መሆኑን ሳንዘነጋ ማንም ይሁን ማን አስፈላጊዉን ክብርና እገዛ እንዲደርግለት አደራ እንላለን፡፡ በተገኘዉ ክትባትም እንድንጠቀምና ራሳችንን ከበሽታዉ እንድንከላከል አደራ እንላለን፡፡

3.9. ከ6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ በኋላ የአገልግሎት ወንበሩን የሚረከብ መሪም ሆነ መንግሥት የሚረከባት ሀገር፣ ሕዝቦቿን በአንድነት፣ በብዝኃነት የሚመራ፣ ቁስሏን የሚያክምላት፣ ለዜጎች ሁሉ በእኩልነት መብታቸዉንና ጥቅማቸዉን የሚያስከብር መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም ያለችን ሀገር አንድ መሆኗን ተገንዝበን ለመጪዉ ሀገር ግንባታ መሠረት ለመጣል ምሁራን በእዉቀታችሁ፤ ሕዝባችን ደግሞ በመልካም ፈቃዳችሁ ከመሪያችሁ ጋር እንድትቆሙና እንድትተባበሩ አደራ እንላለን፡፡

3.10. በመጨረሻም ዉድ ካቶሊካዉያን ምዕመናንና መላዉ የሀገራችን ሕዝቦች ፤ በሀገራዊ ምርጫ የመሳተፍ የዜግነት ግደታችሁ መሆኑን ተረድታችሁ በምርጫዉም በንቃት እንድትሳተፉና ምርጫዉ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለዉ እንዲሆን በጾምና በጸሎት እንድትተጉ አባታዊ ጥሪ እናቀርብላችኃለን፡፡

ፈጣሪ ሀገራችንን ይባርክ፤ ይጠብቃትም!!

አዲስ አበባ ግንቦት 2013

አባ ተሾመ ፍቅሪ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ጸሐፊ

07 June 2021, 13:29