ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ ከ “ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ጋር ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ ከ “ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ጋር 

የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተግባር የቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ አገልግሎት አካል መሆኑ ተገለጸ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያስከተለው ቀውስ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን የበለጠ በማስተባበር፣ አዳዲስ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን እንዲያቀርብ ማድረጉን “ካቶሊካዊ ተግባር” የተባለ ማኅበር ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጁሴፐ ኖታርስተፋኖ አስታወቁ። ማኅበሩን እ. አ. አ ከ2021 – 2024 ዓ. ም እንዲመሩ የተመረጡት ክቡር አቶ ጁሴፐ ኖታርስተፋኖ በማከልም የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሚያቀርበው ሐዋርያዊ ተግባር የቅዱስ ሲኖዶስ የጋራ ሐዋርያዊ ጉዞ አካል መሆኑ ገልጸው በዚህ የጋራ ጉዞ ወቅት የውይይት ልምዶችን በመጠቀም ከመንፈሳዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ ማኅበራዊ እውነታዎችንም በጋራ ለመመልከት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ያለፈው ሚያዝያ 30/2021 ዓ. ም በቫቲካን ውስጥ ለተቀበሏቸው የ “ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ማኅበሩ በ “ምስጋና፣ በትህትና እና በየዋህነት” የታገዘ እንዲሆን አሳስበዋል። በጣሊያን ካቶሊካዊ ምዕመናን የሚመራው እና በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ገደማ የተመሠረተው ማኅበሩ “ታማኝነት ፣ ለጋስነት እና ኃላፊነትን መሸከም” በሚሉ ሦስት ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ ማኅበሩ ለሰው ልጆች ሕይወት በሚያደርገው እንክብካቤ እና ድጋፍ ታማኝነቱን እንዲገልጽ አደራ ብለዋል። ማኅበሩን ለሚቀጥሉ ሦስት ዓመታት እንዲመሩ የተመረጡት ክቡር አቶ ጁሴፐ ኖታርስተፋኖ በበኩላቸው የማኅበራቸው ዓላማ ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። በደቡብ ጣሊያን ፓሌርሞ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሉምሳ በሚባል ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኤኮኖሚያዊ ስታትስቲክስ ተመራማሪ እና መምህር የሆኑት አቶ ጁሴፐ፣ ባካበቱት ረጅም የሥራ ልምድ በመታገዝ ማህበሩን እንዲመሩ የተመረጡት በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መሆኑ ታውቋል።

ክቡር አቶ ጁሴፐ ኖታርስተፋኖ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከረጅም ጊዜ አንስተው ስለ “ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር በሚያደርጉት ንግግር፣ ማኅበሩ ከጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓ ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመተባበር ሃላፊነቱን በታማኝነት በመወጣት ላይ የሚገኝ ማኅበር እንደሆነ መግለጻቸውን አስታውሰዋል። አክለውም የጳጳሳት ቅዱስ ሲኖዶስን አካሄድ በሚገባ ተረድተው አንድነትን በማሳደግ በትውልዶች ፣ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ሕይወት እና በአገራት መካከል መደማመጥ እና መግባባት እንዲኖር ማኅበራቸው በርትቶ የሚሠራ መሆኑን አስረድተዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ችግር የሰዎች ማኅበራዊ ሕይወት መቃወሱን የገለጹት ክቡር አቶ ጁሴፐ ኖታርስተፋኖ “ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ከጊዜ ወደ በማሳደግ አገልግሎቱን ለማበርከት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የሰዎች ስቃይ ከፍተኛ መሆኑን ተመልክተናል ያሉት ክቡር አቶ ጁሴፐ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ልጆች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የርቀት ትምህትን አገልግሎት በማመቻቸት፣ የትምህርት መገልገያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ እና ወደ ኋላ ለቀሩት ተማሪዎች ከመደበኛው የትምርት ጊዜ ውጭ የማካካሻ ትምህርቶችን እንዲከታተሉ በማድረግ ማኅበራቸው ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል። የ“ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላስከተለው ችግር ፈጣን ምላሾችን መስጠት እንደቻለ ገልጸው ይህን ለማድረግ የቻሉትም የሰዎችን ችግር ቶሎ መመልከት በመቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ልምድ በመታገዝ፣ ከሌሎች ማኅበራት ጋር በመተባበር እና በመደማመጥ፣ ድፍረትንም በማግኘት የሚችሉትን አገልግሎት ለማኅበረሰብ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።    

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ“ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር ከጣሊያን ብጹዓ ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመተባበር ሃላፊነቱን በታማኝነት በመወጣት ላይ እንደሚገኝ መናገራቸው ደስታን እንደጨመረላቸው የገለጹት ክቡር አቶ ጁሴፐ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ቅዱስ ሲኖዶስ አካሄድ በመረዳት እና አንድነትን በማሳደግ በትውልዶች እና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ሕይወት መካከል መደማመጥ እና መግባባት እንዲኖር ማኅበራቸው የሚሠራ መሆኑን ገልጸው ፣ በጣሊያን ውስጥ ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ጋር በመወያየት እና አብሮ በመጓዝ ብዙ መልካም ልምዶችን ያገኙ መሆኑን አስረድተዋል። በጣሊያን ውስጥ የ“ካቶሊካዊ ተግባር” ማኅበር ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አቶ ጁሴፐ ኖታርስተፋኖ በመጨረሻም ከብጹዓን ጳጳሳት ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በሕብረት የሚያደርጉትን ጉዞ በታማኝነት ለመጓዝ የሚያስችላቸውን የመንፈስ ቅዱስን መሪነት ለምነዋል።

05 June 2021, 16:11