ፈልግ

ቅዱስ መስቀል ቅዱስ መስቀል 

ጣሊያናዊት መነኩሴ ኢራንን ለቅቀው እንዲወጡ ተነገራቸው

ኢራን ለ26 ዓመታት ሕዝብን ሲያገለጉ ለቆዩት የ75 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ እህት ጁሴፒና ቤርቲ የመኖሪያ ፈቃድ ዕድሳትን በመከልከል ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች። ጣሊያናዊ ዜግነት ያላቸው እህት ጁሴፒና ቤርቲ በኢራን ውስጥ ታብሪዝ በሚባል አካባቢ በስጋ ደዌ ለሚሰቃዩ ሕሙማን ለ26 ዓመታት የሕክምና አገልግሎት ሲያበረክቱ ቆይተዋል። እህት ጁሴፒና ቤርቲ ከአገልግሎት ዓመታት በኋላ በ75 ዓመት ዕድሜአቸው በጡረታ የተገለሉ እና በኢራን ውስጥ ኢስፓን በተባለ አከባቢ በሚገኝ የማኅበራቸው የቸርነት ሥራ ልጆች ቤት የኖሩ ናቸው ። እህት ጁሴፒና ቤርቲ በአገሪቱ የመቆያ ቪዛቸው ወይም የመኖሪያ ፍቃዳቸውን ለማሳደስ ባስገቡት ጥያቄ፣ ከአገር እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። የእህት ጁሴፒና ቤርቲ ከኢራን እንዲወጡ መደረግ የተቀሩ የማኅበሩ አባላት እህቶችን አሳስቧቸዋል። በኢራን ውስጥ ድሆችን እና በስጋ ደዌ የሚሰቃዩ ሰዎችን እየረዱ ለ38 ዓመታት የኖሩት ሌላኛዋ የ77 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ፣ ኦስትሪያዊ እህት ፋቢዮላ ዌይስ፣ የመኖሪያ ፍቃድ እንዲታደስላቸው ላስገቡት ጥያቄ የአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ የተሰጣቸው መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራን ሕዝብ መካከል የሐይማኖት እና የዘር ልዩነት ሳይመለከቱ ድሆችን እና የስጋ ደዌ ሕሙማንን ሲረዱ ለበርካታ ዓመታት የኖሩት ሁለቱ ደናግል እ. አ. አ በ1937 ዓ. ም የተቆረቆረውን የማኅበራቸውን መኖሪያ ቤት ለቅቀው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መገደዳቸው ታውቋል። በኢራን ውስጥ ኢስፓን በተባለ አካባቢ የሚገኝ የቸርነት ሥራ ልጆች ደናግል ማኅበር ለአካባቢው ወጣቶች የትምህርት እና የስልጠና ዕድሎችን ሲያመቻች የቆየ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የቸርነት ሥራ ልጆች ደናግል ማኅበር እ. አ. አ በ1942 ዓ. ም በጦነት ምክንያት ወላጅ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖላንድ ስደተኛ ሕጻናትን ተቀብሎ ዕርዳታን የሰጠ መሆኑ ይታወሳል። ማኅበሩ ለአካባቢው ሕዝብ አገልግሎት ብለው የገነቡት ታዋቂ ትምህርት ቤት  እ. አ. አ በ1979 ዓ. ም በተካሄደው የኢራን አብዮት ወቅት መወረሱ ይታወሳል። ድሆችን እና የስጋ ደዌ ሕሙማንን ሲረዱ ለበርካታ ዓመታት የኖሩት ሁለቱ ደናግል በጡረታ ጊዜያቸው ሐይማኖትን ይሰብካሉ ተብለው እንዳይከሰሱ በመስጋት ቀለል ያሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው ታውቋል።

በኢራን ውስጥ ኢስፓን በተባለ አካባቢ የሚገኝ የቸርነት ሥራ ልጆች ደናግል ማኅበር ብቸኛው የላቲን አምልኮ ሥርዓትን የምትከትለ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋም መሆኑ ሲታወስ በአካባቢው የምትገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና እ. አ. አ በ1939 ዓ. ም.  የታነጸች እና አልፎ አልፎ ለጎብኚዎች ክፍት በመሆን የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸምባት መሆኑ ታውቋል።

በኢራን የምስራቅ ቤተክርስቲያን አምልኮ ሥርዓትን የሚከተሉ ሁለት ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች በአንድ ጳጳስ እና አራት ካህናት በኩል መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን እ. አ. አ ከ2019 ዓ. ም. ጀምሮ በቴራን የሚገኙ ከለዳውያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ራማዚ ጋርሙ የመኖሪያ ፈቃድ እድሳት ተከልክለው ወደ ቴራን እዳሳይመለሱ መታገዳቸው ታውቋል። ሌላው በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአርመኒያ ሥርዓተ አምልኮን የሚከተል ሀገረ ስብከት በጳጳስ ብቻ አገልግሎት የሚያገኝ ሲሆን እና የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የሚከተል ሀገረ ስብከት በቅርቡ አዲስ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ማቲው የተመደበለት መሆኑ ታውቋል። በአገሪቱ የሚገኙ ካቶሊካዊ ገዳማትን በተመለከተ በቴራን የሚገኙ ሦስት የቸርነት ሥራ ልጆች ደናግል እና ኢስፓን በተባለ አከባቢ ሁለት ደናግል መኖራቸው፣ ከእነርሱም ሁለት ገዳማዊያን እህቶች መኖራቸው ሲታወቅ የምዕመናኑ ቁጥርም ወደ 3000 የሚጠጋ መሆኑ ታውቋል።

ድሆችን እና የስጋ ደዌ ሕሙማንን ሲረዱ ለበርካታ ዓመታት የኖሩት የሁለቱ ደናግል ከኢራቅ እንዲወጡ መደረግ በኢስፓን የላቲን ሥርዓት አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እንዳትኖር የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። እ. አ. አ በ2016 ዓ. ም የልኡካን ማኅበር ወይም የላዛሪስት ማኅበር ቤት መወረሱ ይታወሳል። ሁለቱ የቸርነት ሥራ ልጆች ደናግል፣ ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ በኖሩበት አገር ለሚቀጥሉት ዓመታትም እንዲቆዩ የኢራን መንግሥት ውሳኔን እንደሚያስተላልፍ ተስፋ ተደርጎበታል።                

12 June 2021, 16:40