ፈልግ

ክርስትናና ትሕትና ክርስትናና ትሕትና 

ክርስትናና ትሕትና

ትሕትና ከራስ ይልቅ ሌላ ሰው እንደሚሻው መገመትን ራስን ዝቅ በማድረግ ከምድራዊ የበላይነት ውድድር ራስህን መቆጠብ እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያብራራል፡፡ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ነቢይ የሚባለው አጥማቂው ዮሐንስ እንደሁም ድንግል ማርያምና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትሕትና መምህራኖቻችን ናቸው፡፡ ማር. 1፡7፤ ሉቃ. 1፡38

የቤተክርስቲያን ቅዱሳን ታሪክ መለስ ብለን ስንመለከት ብዙዎች እንደ ጳውሎስና እንደ መጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ለወንጌል ተልእኮ ከሀገር ወደ ሀገር በመሄድ አገልግለዋል። አንዳንዶቹ በበረሐ በጾም ፣ በጸሎትና በተጋድሎ አሳልፈዋል። እንዳንዶቹ ደግሞ በተጋድሎና በብቸኝነት ሲያሳልፉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሰምተው በመኖር ብቻ ተቀድሰዋል። ከቅዱሳን አንዳንዶቹ በድንግልናና በክህነት የኖሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ቤተሰብ መሥርተው የኖሩ ናቸው። እንዲሁም አንዳንዶቹ ጳጳሳትና ሊቃውንት ሲሆኑ ግማሾቹ መሃይምና በሰብአዊ ዐይን ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ነበሩ።

እነዚህ ሁሉ የጽድቅ አክሊል የተካፈሉት ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው በማስገዛትና የእግዚአብሔር ፈቃድ በትሕትና በመጠበቃቸው ነበር። በመሠረቱ ሰው ሁሉ የተጠራው ለቅድስና ነው። የቅድስናን ሕይወት ለመለማመድ የክርስቶስን ሕይወት እያንዳንዱ ሰው መለማመድ የግድ ያስፈልጋል። የክርስቶስን ሕይወት ለመለማመድ ደግሞ ከክርስቶስ መማር ወሳኝ ነገር ነው። “እናንተ ደካሞች ወደ እኔ ኑ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ …. ከእኔም ተማሩ የዋህና ትሑት ነኝ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ማቴ. 11፡28-29። የነፍስ ዕረፍት ለማግኘት የክርስቶስን ትሕትና መማር አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል። የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ተልእኮአችን እንዲሰምር የትሕትና መምህር ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ መቅረብ ያስፈልጋል።

ትሑታንንና ትዕዛዝ የሚፈጽሙትን እግዚአብሔር በእውነትና በፍቅር እንደሚመራቸው ዳዊት ከራሱ የሕይወት ልምዱ በመነሣት ገልጾልናል። ትሕትና በእግዚአብሔር ፊት ጥበብ እንደሆነ በመጽሐፈ ምሳሌ እንደሚከተለው ተገልጿል። “እግዚአብሔርን ብትፈራና ትሑት ብትሆን ሃብት ፣ ክብርና ረዥም ዕድሜ ታገኛለህ” ምሳ. 22፡4

ሁሉም ሰው የሚመኘውን መንግሥተ ሰማያት የሚወርሱት “በመንፈስ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ” እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጾልናል። ማቴ. 5፡3 ይህንኑ ሐሳብ ለማጠናከር ሐዋርያት በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን እንደሆነ በጠየቁት ጊዜ አንድ ሕፃን በመካከላቸው አቁሞ “እንደዚህ ህፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይሆናል” በማለት አስተምሮአቸው ነበር። ማቴ. 18፡4 በዚህ አባባል መሠረት ትሕትና ወደ መንግስተ ሰማያት መግቢያ ወሳኝ በር እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

የሐዋርያት ጥያቄ የሁላችን ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ክርስቲያን ሆኖ በክርስቶስ ተስፋ የተሰጠውን መንግሥተ ሰማያት የማይመኝ አይኖርም። በክርስቶስ የማመንና ክትስቶስን የመከተል ትልቁ ዓላማ ለመንግሥተ ሰማያት ሕይወት ነውና።በሥጋዊ ዐይን ስንመለከት የምድራዊ ሕይወት ጉጉት ማለትም የሀብት ፣ የሥልጣን ፣ የክብርና ዝና የማትረፍ ፍላጐት በክርስቶስ መንፈስ እንዲገራ ጊዜ ይወስዳል።

እግዚአብሔር በሁሉም ነገር ፍጹምና ሙሉ በመሆኑ ካለበት ደረጃ ከፍ ለማለት አይጓጓም። ጌታችን ኢየሱሰ ክርስርቶስ የእግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ለእኛ ሊያካፍል ሲመጣ በገዛ ፈቃዱ አምላካዊነቱን ሳይተው እንደ እኛ ሰው መሆንን የመረጠው ትሕትናን ለማስተማር ነበር። ዕብ. 4፡15

ጌታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መገለጡ ትሕትና አዕምሮአዊ እውቀት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ለኛም ትሕትናን ለማስተማር ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ፍቅርና ትሕትና የማይነጣጠሉ እንደመሆናቸው መጠን እውነተኛ ትሕትና ባለበት ቦታ እውነተኛ ፍቅር አለ ፤ እውነተኛ ፍቅር ባለበት ቦታ ደግሞ እውነተኛ ትሕትና አለ። ቅዱስ አውጐስጢኖስ ስለ ትሕትና ወሳኝነት እንዲህ ሲል ይገልጻል “ያለ ትሕትና ደኅንነት የለም ፤ ያለ ትሕትና ቅድስና የለም ፤ ያለ ትሕትና የእግዚብሔርና የሰው ፍቅር የለም። ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር መድረሻ እርግጠኛ መንገድ መጀመሪያ ትሕትና ቀጥሎ ትሕትና በመጨረሻም ትሕትና ነው” ይላል።

ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የነበሩት የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ቀርበው በመንግሥቱ አንዳቸውን በቀኙ አንዳቸውን በግራ እንዲያስቀምጣቸው በቀየቁት ጊዜ መጠየቅ የሚገባቸውን ባለማወቃቸውና የተመረጡበትን ዓላማ ባለመረዳታቸው ይወቅሳቸዋል። የቀሩት ሐዋርያትም ይህንን የወንድማማቾችን ጥያቄ በሰሙ ጊዜ እነርሱም በቅናት መንፈስ ይመኙት የነበረውን ሥልጣን ማግኛ አለመሆኑን ራሱን ምሳሌ አድርጐ በማቅረብ አስረዳቸው “የሰው ልጅ እንኳ ለማገልገልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጐ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ሲል አሳሰባቸው ማር. 10፡35-45። አገልጋይነት በትሕትና መኖር ብቻም ሳይሆን ከግል ፍላጐትና ጥቅም በመውጣት ለሌሎች ቤዛ መሆንን ይጠይቃል። የክርስቶስ አካል ክፍሎች እንደመሆናችን መጠን ከሌሎች መሥዋዕት ሆኖ የመቅረብን ሕይወት ከትሕትና ሕይወት ጋር አጣምሮ መለማመድ አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌላ የወንጌል መልእክቱ ለደቀ መዛሙርቱና ለሕዝቡ ያስተላለፈው መልእክት ምክር ብቻ ሳይሆን ማስጠንቀቂያም ጭምር ነበር። ማስጠንቀቂያው የእርሱ ተከታዮች እንደ ፈሪሳውያንና እንደ ሙሴ ሕግ መምህራን በሰዎች ዘንድ አድናቆትን ለማግኘት ብለው የታይታና የግብዝነት ሕይወት መኖር እንደሌለባቸው ማስጠንቀቅ ነበር። ማቴ. 23፡1-12

የሙሴ ሕግ መምህራንና የፈሪሳውያንን ማንነት ሲያመለከት “ሥራቸውን ሁሉ የሚያደርጉት ሰው እንዲያይላቸው ብለው ነው” በማለት ይገልጻል። የእርሱ ተከታዮች ግን መኖርና ማገልገል ያለባቸው በትሕትና መንፈስ መሆን እንዳለበት እንዲህ ሲል ይገልጻል፡- “ከእናንተ መካከል የበላይ ሹም የሆነው የእናንተ አገልጋይ ይሁን ፤ እራሱን ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል ፤ ራሱን ዝቅ የሚያደረግ ግን ከፍ ይላል” ማቴ. 23፡11-12።

በእግዚአብሔር ዘንድ እውነተኛ ትልቅነት እውነተኛ ትሕትና እንደመሆኑ መጠን እውነተኛ ጸሎትም በትሕትና መንፈስ የሚቀርብ ጸሎት መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትዕቢተኛ ፈሪሳዊውንና የትሑቱን ቀራጭ ጸሎት እንደ ምሳሌ ያቀርባል።

ሁለቱም ሰዎች ወደ ቤተመቅደስ ገብተው ሲጸልዩ ፈሪሳዊው በልበ ሙሉነት ቆሞ እንደ ሌሎችና በተለይም በአጠገቡ ሲጸልይ እንደነበረ እንደ ቀራጩ ኃጢያተኛ አለመሆኑን በመግለጽ በሳምንት ሁለት ቀን እንደሚጾምና ምፅዋትም እንደሚሰጥ ለእግዚአብሔር ያብራራለታል። በተቃራኒው ቀራጩ ግን በትሕትና በእግዚአብሔር ፊት ራሱን ዝቀ አድርጐ “አምላክ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” እያለ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ይጠይቅ ነበር። ከሁለቱ ሰዎች ምሕረትን አግኝቶ ወደ ቤቱ የተመለሰው ያ ትሑቱ ቀራጭ እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ተናግሯል። በእግዚአብሔር ዘንድ ጸሎታችን ተቀባይነት እንዲኖረው ኃጢያተኞች መሆናችንን በማመን በትሕትና መቅረብ እንደሚገባን ያስተምራል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲደመድመው የሐዋርያትን እግር በማጠብ የትሕትናን ትርጉም አስተማረ። በአይሁዳውያን ባሕል የጌታቸውንና የእንግዶችን እግር የሚያጥቡት አገልጋዮች ናቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በመነሣት ነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩን እንዳያጥብ የከለከለው። በኋላ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደኅንነት ዕቅድ እንዲህ መሆን እንዳለበት ስላስረዳው ጴጥሮስ በነገሩ ተስማምቶ እንዲያጥብ ሰጠው። “እኔም ለእናንተ እንዳደረግሁት፤ እናንተም እንዲሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ” ዮሐ. 13፡15። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምሕርና ጌታ ሳለ የሐዋርያትን እግር በማጠብ እርስ በርሳችን አንዳችን ሌላውን እንድናገለግል ምሳሌ ሰጠን። በጥምቀት የክርስቶስ የአካል ክፍል የሆነ ሁሉ ለራሱ ብቻ ከመኖር ይልቅ በትሕትና ሌላውን እንዲያገለግል ተጋብዟል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስን ትሕትና እንለማመድና ለአገልግሎት እንነሣ።

ምንጭ፡ የእረኞች ድምፅ ቁጥር 12 - አባ በቀለ ጌዳ /ሲታዊ/

28 June 2021, 10:19