ፈልግ

ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጀልባ ላይ ወርዶ በውሃ ላይ በተራመደበት ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጀልባ ላይ ወርዶ በውሃ ላይ በተራመደበት ወቅት  

የግንቦት 29/2013 ዓ.ም የትንሣኤ 6ኛ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ሮሜ 6፡ 1-14

2.   1ኛ ጴጥ 4፡4-11

3.   ሐዋ 23፡ 15-21

4.   ዮሐ.21፡ 15-25

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ጴጥሮስን ወደ ቀድሞ ቦታው መለሰው

በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወደኛለህን?” አለው።

እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፤ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወደኛለህን?” አለው።

ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ ‘ትወደኛለህን?’ ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤      እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ። እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።” ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።

ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ ራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር። ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ።

ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው። በዚህ ምክንያት ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰራጨ። ኢየሱስ ግን፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ እንደማይሞት አልነገረውም።

ስለ እነዚህ የሚመሰክረውና ይህን የጻፈው ይኸው ደቀ መዝሙር ነው፤ ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ እናውቃለን።

ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ቢጻፍ፣ ለተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ዓለም በቂ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሣኤ ስድስተኛ ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን መመሪያ የሆነውን ቅዱስ ቃሉን ቅድስት ቤተክርስቲያን ለዕለቱ ባዘጋጀችልን ንባባት አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን ልብ ይልካል። በእርግጥ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ቃሉን ወደ እኛ ሲልክ ቃሉን በሙሉ ልብ እንድናዳምጥና እንድናስተውል ቢሆንም የቃሉ መደመጥ ዋነኛ ዓላማውና ግቡ ያዳመጥነውን ቃል በሕይወታችን መተግበር እንድንችል ነው። ለዚህም ነው ሁል ጊዜ የቃሉ ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን በተግባር የምናውልበት ብርታትና ጸጋ ስጠን ብለን የምንለምነው።

እንግዲህ በዚህ መልኩ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልዕክት አድርጎ ዛሬ ለእኛም እግዚአብሔር ፍጹም መሐሪ ፍጹም ይቅር ባይ አምላክ መሆኑን ይነግረናል።

እኛ ልጆቹ ምን ያሕል ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳን በእርሱ ፊት ለመቆም የተገባንና ሥሙን ለመጥራት በአነጋገራችን ሆነ በአካሄዳችን ሆነ በምግባራችን የተገባን ባንሆንም እንኳን የእርሱ ፍቅር የእርሱ ቸርነት የእርሱ ምሕረት እኛ ከምንገምተው በላይ ነውና እጆቹን ዘርግቶ ሊያቅፈን ሊያበረታታን እውነተኛ አባትነቱን ሊያሳየን ዘወትር ወደ እኛ ይመጣል ከኃጢአታችንም ይፈታናል በፍቅሩና በጸጋውም ይሞላናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚሁ መልዕክቱ በቁጥር 2 ላይ እንደሚጠቅሰው እኛ ለኃጢአት ሞተናል ይላል። ለኃጢአት መሞት ማለት በእግዚአብሔር ጸጋ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በመሳተፍ ድሮ ከነበርንበት አሮጌ እኛነት በመውጣት በአንድያ የእግዚአብሔር ልጅ የተጎናጸፍነውን አዲሱን ከኃጢአት ነፃ የወጣውን ሰውነት ይዘን ወደ ቅድስና ጉዞ መጀመር ማለት ነው።

ለኃጢአት መሞት ማለት ማንነታችንን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ማስገዛት ማለት ነው።  ለኃጢአት መሞት ማለት ለራሳችን ፍላጎትና ስሜት ብቻ መገዛት ሳይሆን እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና እና አጋዢነት ለሚሰጠን መመሪያ ተገዢ መሆን ማለት ነው። ለኃጢአት መሞት ማለት ሰይጣንንና ከእርሱ የሚመነጨውን ማንኛውንም ዓይነት ክፉ ሃሳብና ምኞት መካድ ማለት ነው። ለኃጢአት መሞት ማለት ከማንኛውም ዓይነት ኃጢአት ነፃ በመሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ውስጥ መመላለስ ማለት ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተጠምቀናል ስንል ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን ሞተናል ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አብረን ወደ መቃብር ወረደናል እዛም በኃጢአት የበሰበሰውን አሮጌውን ሰውነት ወይም ማንነታችንን በመተው ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን በአዲስ ሰውነት ፣ በአዲስ መንፈስና  በአዲስ ኃይል ተነሥተናል ማለታችን ነው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆነናል ማለታችን ነው።

ይህ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነውን አዲስ ሕይወት በተለያዩ መንፈሳዊ እሴቶች ልንጠብቀው ልንንከባከበው ይገባል። በተለይም የእምነታችን መሠረትና የጸጋዎች ሁሉ ምንጭ በሆነው በመሥዋተ ቅዳሴ በመሳተፍ የምስጢራትና የጸጋዎች ሁሉ ባለቤት የሆነውን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወደሙ መልክ በመቀበልና ከእርሱም በምናገኘው ኃይል በየትኛውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፋይ በመሆን ልናሳድገው ይገባል።

ይህ የተቀበልነው አዲስ ሰውነት በዚህ መልኩ በየጊዜው እየታደሰ የማይሄድ ከሆነ የተቀበልነው ጸጋ ቀስ በቀስ ከውስጣችን በመውጣት ተመልሰን ወደ ድሮው ኃጢአተኛ እኛነታችን በማዘንበል እንደ ቀድሞው የሰይጣንና የእርሱ ሥራ ብቻ ተካፋዮች እንሆናለን። አንድ ተክል ተተክሎ አስፈላጊው እንክብካቤ ካልተደረገለት በምንም መልኩ ሊያድግ አይችልም። ማለትም ውኃ ማጠጣት መኮትኮት አረሙን ማስወገድ በዙሪያው ማዳበሪያ መጨመርና የመሳሰሉትን ከተነፈገ አድጎ ፍሬ ማፍራት አይደለም ማደጉ ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል ቀስ በቀስ ይጠወልጋል ይደርቃል በስትመጨረሻም ይሞታል። እኛም በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንደዚህ ነን አስፈላጊው መንፈሳዊ እንክብካቤ ከሌለ ቀስ በቀስ አንጠወልጋለን እንደርቃለን በስተመጨረሻም እንሞታለን።

ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስም በሁለተኛ መልዕክቱ ይህንን ሃሳብ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል ፤ ለኃጢአት ሞተናልና ከእንግዲህ ወዲህ የሥጋን ክፉ ምኞት በማድረግ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም መኖር አለብን ይለናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሌላ የሚያካፍለን ሃሳብ ሁልጊዜ የዓለም መጨረሻ ነገ እንደሆነ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መምጫ ነገ እንደሆነ አድርገን መኖር እንዳለብን ይነግረናል። ይህም ማለት ዘወትር ከኃጢአት ፀድተን በእግዚአብሔር ጸጋ እየተመላለስን እንድንኖር በትንሣኤው አማካኝነት ያገኘነውን አዲስ ሕይወት ጠብቀን ይዘን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድንሻገር መልዕክቱን ያስተላልፍልናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመቀጠል እንደ ባለ አእምሮ አስቡ ጸሎትን ለማድረግ ይረዳችሁ ዘንድ በመጠን ኑሩ ከሁሉ በላይ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ስጦታ ተጠቅማችሁ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በሚገባ አገልግሉ ይለናል። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው በሰጠን አዲስ ሕይወት ውስጥ እየኖርን ነን ብለን መናገር የምንችለው። ይህንን መተኪያ የሌለው ቀጥተኛ መንገድ መከተል ስንችል ብቻ ነው የመንግሥተ ሰማይ እጩዎች የእግዚአብሔርም ቃል ፈፃሚዎች ነን ብለን በሙላት መናገር የምንችለው።

በዛሬው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ያደረገውን ውይይትና ስለሰጠውም ኃላፊነት ይናገራል። ይህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ኃላፊነት ገና ከጅምሩ ጴጥሮስ ሲጠራ ዓሣ አጥማጅ ነበርክ አሁን ግን የሰዎች አጥማጅ ትሆናለህ ብሎ የተናገረው የክርስቶስ ቃል ተፈፀመ ፣ ምክንያቱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሦስት ጊዜ የዮና ልጅ ስምኦን ሆይ ከነዚህ ይልቅ አብልጠህ ትወደኛለህን? ብሎ ከጠየቀው በኋላ ግልገሎቼን አሰማራ ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ በጎቼን ፣ አሰማራ ብሎ ጥብቅ ትዕዛዝ እና ኃላፊነት ሰጥቶታል።

ስለዚህ በዚህ መልኩ የክርስቶስ የሆኑት ክርስቶስ በየስማቸው ይጠራቸው የነበሩት ከፊት ከፊትም በመሄድ ይመራቸው የነበሩት ስለእነሱም ሲል ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥላቸው የበጎቹ ጠባቂ አደረገው ፣ እኛም የክርስቶስ በጎች የሆንን ይህንን የክርስቶስን ቃል ሰምተን በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንሻገራለን። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በጎቹን በለመለመ መሥክ እንደሚመራ ሁሉ ቅዱስ ጴጥሮስም በተቀበለው ኃላፊነት መሠረት በጎቹንም ሆነ ጠቦቶቹን በለመለመ መሥክ ይመራል ፣ በዚህም መንጋ ውስጥ የተካተተ ሁሉ የኋላ ኋላ በክርስቶስ ጥላ ውስጥ ይኖራል ምክንያቱም ቅዱስ ጴጥሮስም በጎቹን እንዲያሰማራ ኃላፊነቱን ይውሰድ እንጂ በጎቹም ሆኑ ጠቦቶቹ ሁል ጊዜም ቢሆን የክርስቶስ ናቸው።

አንድ አንድ የቤተክርስቲያን አባቶች ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ የዮና ልጅ ስምኦን ሆይ ከነዚህ ይልቅ አብልጠህ ትወደኛለህን? ብሎ የጠየቀው ከዚህ በፊት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበት ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመካዱ ይህንን የክህደቱን ቃል መሰረዣና እንደ ንስሃም የሚቆጠር ነው ይላሉ።

ስለዚህ እኛም በሠራናቸው ኃጢአቶች በመፀፀትና እውነተኛ ንስሃ በመግባት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ባሳየን መንገድ ባስተማረን ትምህርት በሰጠን ጸጋ መመላለስ እንድንችል ዘወትር ከልጇ አጠገብ የማትለይው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእኛም አጠገብ ሆና የአንድያ ልጇን ጸጋና በረከት ለእያንዳዳችን ታሰጠን እጃችንንም ይዛ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሚገኝበት በለመለመው መስክ ትምራን።

የእርሷን ትሕትና ፣ የእንሷን ታዛዢነትና የእርሷን ቅድስና በመመልከት እኛም በተቻለን አቅም ሁሉ ትሑቶች ፤ ታዛዦቻና ቅዱሳኖች ለመሆን ጥረት እንድናደርግና ልክ እንደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅድስናን መንገድ መከተል እንድንችል እሷ ራሷ እጃችንን ይዛ ትምራን እርሷ ወደደረሰችበትም ቦታ ታድርሰን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

05 June 2021, 10:58