ፈልግ

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታዛዥነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታዛዥነት 

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታዛዥነት

ታዛዥነት ከእግዚአብሔር የጸጋ ሙላት የሚመነጭ የትሕትና ፍሬ ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ ትሑት ስለሆነች ታዛዥ ነበረች። ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ስለ ማርያም ታዛዥነት አስፍቶ ይናገራል። “የእግዚአብሔር መልአክ ፣ በናዝሬት ወደ ምትኖረው ድንግል ተላከ ፤ “አንቺ ጸጋ የተሞላሽ” እያለ ሰላምታ ባቀረበላት ጊዜ ፣ ይህንን ሰማያዊ ብሥራት “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ ፤ አንተ እንዳልህ ይሁንልኝ” እያለች መለሰችለት።” ሉቃ 1፡38 ቅዱሳን አበው ቤተ ክርስቲያን ፣ በአምላክ የድኅነት ሥራ ፣ ማርያም በዝምታ ሳይሆን በፈቃደኝነት ፣ በእምነትና በታዛዥነት እንደተሳተፈች ያምናሉ። ምንክያቱም ፣ ቅዱስ ኢረኒዮስ እንደሚለው ፣ እሷ ታዛዥ በመሆኗ ፣ ለራሷና ለሰው ዘር በሙሉ የድኅነት ምክንያት ሆነች። ስለዚህ አንዳንድ አበው ከቅዱስ ኢረኒዮስ ጋር በመሆን ፣ የሔዋን የእንቢተኝነት ቋጠሮ በማርያም ተፈታ ፤ ሔዋን ባለማመንዋ ያሰረችውን ነገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማመንዋ ፈታችው። … ብፅዕት ድንግል ማርያም ስላመነችና ስለታዘዘች ፣ የእግዚአብሔርን ልጅ በምድር ላይ ወለደችው። ለመውለድ የበቃችው ከወንድ ሳትገናኝ ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። በሁለቱም መካከል ንጽጽር በማድረግ ለማርያም “የሔዋን እናት” ብለው ይጠሩዋታል ፤ ቀጥሎም “ሞት በሔዋን መጣ” “ሕይወት ግን በማርያም መጣ” ይላሉ።

ቅዱሳን በእመቤታችን ማርያም ታዛዥነትና ፣ ስለ ታዛዥነትን ጥቅም እንዲህ እያሉ ይናገራሉ። ቅዱስ አጎስጢኖስ “ያቺ የመለኮታዊው እናት በመታዘዟ ፣ ሔዋን ባለመታዘዟ ያመጣችብንን ጉዳት ካሠች” ይላል። ቅዱስ በርናርዶስ ፣ “ሰማች - አየች ፤ ሰማች - አመነች ፤ አየች - ገባት።  ጆሮዎቿን ለመታዘዝ አዘነበለች” ይላል። “በብፅዕት ድንግል ማርያም ፣ መዘግየት የሚባል ነገር የለም። ስለዚህ ልክ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ነበረች” ይላል ቅዱስ በርናርዶስ።

ማርያም ፣ እግዚአብሔርን ከታዛዥነት በላይ የሚያስደስተው ነገር እንደሌለ ስለገባት ፣ በዚህ መንገድ ልታገለግለው ወሰነች። ታዛዥነት ፣ ትልቅ መስዋዕትነት ፣ መንፈሳዊ ጀግንነት ፣ የጽድቅ መንገድ እንደሆነ ስለተገነዘበች ፣ የሕይወቷ ዓላማ አድርጋ ያዘችው። ቅዱስ ጳውሎስ ፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር “እስከ ሞት ታዛዥ ሆነ” ፊል 2፡8 ይላል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ እንደ ልጇ፣ ከልጅነት እስከ ሞት ታዛዥ ሆነች። ይህንን ከባድ የታዛዥነት ቀንበር በደስታ ተሸከመችው። ለማን ትታዘዝ ነበር? መጀመርያ ለእግዚአብሔር ፣ በመቀጠል ለሰው ትታዘዝ ነበር።

ለእግዚአብሔር ትታዘዝ ነበር፦ “ለኃጢአት ስርየት የሚሆን መሥዋዕት እንዲቀርብልህ አትጠይቅም ፤ በዚህ ፈንታ የአንተን ትእዛዝ በመስማት እንዳገለግልህ አደርግኸኝ። … ሕግህን በልቤ አኖራለሁ።” መዝ. 40፡ 6-8 እያለች ፣ እግዚአብሔርን በሁለንተናዋ ልታገለግለው ፈቃደኛ እንደሆነች ገለጸችለት። የራሷን ፍላጎት ትታ ፣ ፈጣሪዋ ልክ እሱ እንደሚፈልገው የታዛዥነትን መስዋዕት ልታቀርብለት ቁርጥ ፈቃድ አደረገች። እግዚአብሔር የመድኃኔ ዓለም እናት እንድትሆን ሐሳቡን በገለጸላት ጊዜ ፣ ያ የምትወደው የነበረው የንጽሕና ሕይወቷን ትታ ፣ የሱን ቅዱስ ፈቃድ በደስታ ተቀበለችው። ይህ የሚያስደንቅ ታዛዥነቷ ደግሞ ለሰው ልጅ ድኅነትን አመጣ ፤ የኃጢአታችንም ካሣ ሆነ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  በመታዘዟ ምክንያት ፣ በኃጢአታቸው ተጸጽተው አማልጅነቷን ለሚማጠኑ ኃጢአተኞች ምሕረት እንዲያገኙ ፣ ከእግዚአብሔር ፊት ታቀርባዘዋለች። የሚያፈቅረው ልጁ በመስቀል ላይ መስዋዕት ሆኖ እንዲቀርብ የአባቱ ፈቃድ እንደሆነ ባወቀች ጊዜ ፣ ራሷን ዝቅ አድርጋ ፣ የአምላክን ፈቃድ ተቀበለችው። አምላክ በተለያየ መንገድ ሲገለጥላት ሳለ ፣ ቶሎ ብላ ትከተለው ነበር። ሁልጊዜ ይህንን መለኮታዊ ፈቃድ ፣ ፍላጎት ትመለከት ነበር። በተለያየ ዓይነት መከራ ውስጥ ብታልፍም በደስታ ትቀበለው ነበር። ታዛዥነቷ ፣ በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ፣ የሚያስደስት ፣ ፍሬ ያለው ነበር። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአነጋገሯ ፣ በሥራዋ ፣ በሓሳቧ እግዚአብሔርን አትቃወምም ነበር። ለራሷ ምንም ሳታስቀር ለእግዚአብሔር በሁለንተናዋ ትታዘዘው ነበር።

ዛሬ ላይ እኛስ ፣ እግዚአብሔርን እንደዚህ አድርገን እንታዘዘዋለን ወይ? ልክ እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁልጊዜ የሱን ፈቃድ ነው የምፈጽመው? ፤ ፈቃዱ ልፈጽም ነው የመጣሁት እንላለን ወይ? የእርሱን ቅዱስ ፈቃድ ፣ ከልባችን በታዛዥነት መንፈስ ቶሎ ብለን እንፈጽመዋለን ወይ?  የሕይወታችንስ ዓላማ ነውን? እስኪ እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ሕሊናችንን እንመርምር።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአምላክ በመቀጠል ለሰው ትታዘዝ ነበር፡- የአምላክ እናት ነኝ ፤ ከፍጥረት በላይ ነኝ ፤ ስለዚህ ለአምላክ እንጂ ለሰው መታዘዝ የለብኝም ፤ ምክንያቱም ከእኔ በታች ናቸው ብላ ለሰው መታዘዝን እምቢ አላለችም። ለሰው መታዘዝ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑ አውቃ ፣ ለወላጆቿ ፣ ለካህናት ፣ ለቅዱስ ዮሴፍ ፣ ለሁሉም በሷ ላይ ኃላፊነት ለነበራቸው ሁሉ ትታዘዝ ነበር። ለጨካኞቹ ዓለማውያን ባለስልጣኖችም ሳይቀር ትታዘዝ ነበር። ስለዚህ ከሰው ጋርም ታዛዥነቷ ፍጹም ነበር።

ይህ የሚያንጽ ታዛዥነት በእኛ ሕይወት ዛሬ ላይ ይገኝ ይሆን? ለወላጆቻችን ፣ ለቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ፣ ለመሪዎቻችን ፣ ለባለስልጣኖች እንዴት አድርገን ነው የምንታዘዘው? እነርሱ በሚያዙን ጊዜ በትሕትና እሺ ብለን እንታዘዛለን ውይ? በጥላቻ ፣ በንቀት ወይ በቸልተኝነት ደስ ሳይለን ነው የምንታዘዘው? የእግዚአብሔር ድምጽ የሆነችው ሕሊናችን ምን ትለን ይሆን?

ዘወትር የመታዘዝ እና የትሕትና ተምሳሌት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተምሳሌትነትዋን የሕይወታችን ክፍል እናደርገው ዘንድ በአማላጅነትዋ በልጇ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ታቅርበን። አሜን!!!

24 May 2021, 12:28