ፈልግ

2021.05.23 Mandato missionario Laudato si Tagle 2021.05.23 Mandato missionario Laudato si Tagle 

ካርዲናል ታግለ፣ የወንጌል ተልዕኮ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ ስጦታ መሆኑን ገለጹ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ የወንጌል ተልዕኮ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ ስጦታ መሆኑን ገለጹ። ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ይህን የተናገሩት በሮም ከተማ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንትን ምክንያት በማድረግ ሲካሄድ በቆየው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ መሆኑ ታውቋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንትን ማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት በአሲዚ ከተማም መፈጸሙ ታውቋል። በአውታረ መረብ በቀረበው ዝግጅት በኩል “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረት በማድረግ እና በተፈጥሮ ጥበቃ ወንጌላዊ መልዕክት በመመራት ወጣቶች፣ የሐዋርያዊ አገልጋዮች አስተባባሪዎች እና ምዕመናን በሙሉ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤን እንዲያደርጉ መልዕክት ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቤተክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ እያንዳንዱ ምዕመን በምስጢረ ጥምቀት የተቀበለውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳለበት ይህም የሚረጋገጠው የቤተክርስቲያንን ተልዕኮ በተግባር በመግለጽ መሆኑን በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ግንቦት 15/2013 ዓ. ም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ባቀረቡት ጸሎት ወቅት መላው ምዕመናን ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚደረግ ወንጌላዊ ተግባር በመመራት ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲያደርጉ በማለት ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የጸሎት ሥነ-ሥርዓት

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን 6ኛ ዓመት መታሰቢያ ሳምንት፣ በበዓለ ጴራቅሊጦስ በዓል ዕለት ግንቦት 16/2021 ዓ. ም መፈጸሙ ታውቋል። በሮም በሚገኝ የፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር ጠቅላይ ቤት ተገኝተው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ የመሩት በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ መሆናቸው ታውቋል።

በዓሉ በሮም፣ በአሲዚ እና በአምስቱም አህጉራት ተክብሯል

በአውታረ መረብ በኩል ወደ መላው ዓለም እንዲደርስ በተደረገው የመዝጊያ በዓል ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የአሲዚ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ሶረንቲኖ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስ ፍራንችስኮስ መኖሪያውን በጣሊያን ኡምብሪያ አውራጃ ውስጥ የቅዱስ ዶሜኒኮ ቤተክርስቲያን በሚገኝበት በማድረግ ከእግዚአብሔር በተቀበለው ጥሪ መሠረት ተልዕኮውን፣ ሥራውን እና አገልግሎቱን መፈጸሙን ብጹዕ አቡነ ሶሬንቶ አስታውሰው፣ በአውታረ መረብ አማካይነት በአምስቱም አህጉራት ለሚገኙት እና በተፈጥሮ እንክብካቤ ተግባር ላይ የተሰማሩ አባላት እና ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የአየር ንብረት ለውጥ የሚከታተል እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች በሙሉ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለመንከባከብ መጠራታቸውን አስረድተዋል።

የሁል ጊዜ መልዕክት ሊሆን ይግባል

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በመልዕክታቸው “ከሞት የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከእኛ ጋር ነው” ብለው፣ ይህን እውነት ለዓለም መመስከር እንደሚያስፈልግ በተለይም ዓለማችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሚሰቃይበት ባሁኑ ወቅት መመስከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት ጋር እንደነበረ ሁሉ ከእኛም ጋር ዘወትር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ዘላቂ፣ ሌሎችን እየደገፍን በሕይወታችን ሁሉ የምናበረክተው ጥሪ መሆኑን አስረድተዋል።

የብርሃን ምንጭ ነው

የተልዕኮ ጥሪን የተቀበሉ እና መልካም ምላሽ የሰጡት ካቶሊካዊ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቆጣጠሩ አባላት ከብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ፣ ከናይሮቢ፣ ከዋሽንግተን፣ ከሮም እና አሲዚ ከተሞች መሆናቸው ታውቋል። በአየር ንብርት ለውጥ ምክንያት በሚደርስ አደጋ የተጠቁ በተለይ የሕንድ እና ብራዚል ነዋሪዎች መሆናቸውን የፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ ሚካኤል ፔሪ በመልዕክታቸው፣ እነዚህ የአደጋው ተጠቂዎች ዕለታዊ መስቀላቸውን መሸከማቸውን አስገንዝበው፣ ለእነዚህ ሰዎች ወንድማማችነትን በመግልጽ ተልዕኮዋችንን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የጥረታችን ፍጻሜ የሚለካው ቸርነትን፣ ፍቅርን እና ትህትናን በማሳየት መሆኑን ከስብሰባው ተካፋዮች ጋር የሻማ መብራት በማብራት፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ገልጸዋል።

24 May 2021, 14:44