ፈልግ

ጌታ ከሙታን ተነስቷል ጌታ ከሙታን ተነስቷል  

የሚያዝያ 24/2013 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል እለተ ሰንበት አስተንትኖ!

የዕለቱ ንባባት

1.    1ቆሮ 15፡20-48

2.   1ጴጥ 1፡1-12

3.   ሐዋ  2፡22-36

4.   ዮሐ 20፡1-18

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ከሞት ተነሣ

በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች። ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።

“ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።

ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ

ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤ ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም።እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት።

እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት። እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው።

ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።

የእለቱ አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እንኳዋን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ እያልኩ የጌታችን ኢየሱስ ክረቶስን ትንሳኤ በዓል እንድናከብር ጸጋና በረከትን የሰጠን ፤ በጤናና በሰላም የጠበቀን ብሎም የበዓሉ ተካፋዮች ያደረገን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን።

በቤተክርስትያናችን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሠረት የዛሬው ሰንበት ዘትንሣኤ  በመባል ይታወቃል። በእዚህ ጊዜያት ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በቃሉ አማካኝነት የተለያዩ ትምህርቶችና መልዕክቶች ያስተላልፍልናል።

እግዚአብሔር በየዓመቱ ልዩና ጥልቅ የሆነ ፍቅሩ የተገለጸበትን የጌታችን ኢየሱስ ክረቶስን ትንሣኤ በዓል እንድናከብር ጸጋና በረከትን የሰጠን ፣ በጤናና በሰላም የጠበቀን ብሎም የበዓሉ ተካፋዮች ያደረገን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን።

የትንሣኤን ወቅት ወይም በዓል ማክበር በክርስቲያኖች ዘንድ በዓል ከማክበር ባለፈ የክርስቶስን ጥልቅ ፍቅር የምናይበት እና የክርስቶስ መሆናችንን በይበልጥ የምናድስበት የኃላፊነት ወቅት ነው።

ሕይወትና የሕይወት ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እኔ ትንሣኤና ሕይወትም ነኝ ብሏል። ዮሐ 11፡25 “…ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል።”

ትንሣኤ-መነሳት-ተነሣ፤ ማለትም ከተቀመጡበት፤ ከተኙበት፤ ካንቀላፉበት… ሲባልም መንፈሳዊ ሕይወትን በመዘንጋት፣ በድክመት ፣ ኃላፊነትን ፣ ግዴታን እንዲሁም ክርስቲያናዊ ጥሪያችንን በማሰብ ተነሥተን መንቀሳቀስ መቻልና ሕይወት እንዳለን ማሳየት ማለት ነው። በመሠረቱ አንድ ክርስቲያን ለሆነ ሰው በእግዚአብሔር ጸጋ በሚገኝበት ሕይወት ውስጥ ሲሆን ሁልጊዜ ትንሣኤ ነው ፤ ምክንያቱም ሕይወታችን በዘመናትና በዘመን ፤ በዓመታትና በዓመት ፤ በወራትና በወር ፤ እያለ በጊዜያት የተከፋፈለ በመሆኑ በዚህ ሁሉ ውስጥ እግዚአብሔር በጸጋው ከእኛ ጋር እንዳለአለ የምንመለከትበት ምስጢር ስለሆነ።

በእግዚአብሔር ጸጋ አማካኝነት በየቀኑ… ትንሣኤን የማይለማመድ ሰው የትንሣኤን ምንነት እንዴት ሊረዳው ይችላል? በክርስትና ሕይወት መኖር ማለት ትክክለኛ ትርጉም እርሱ ብቻ ነውና። ቅዱስ ዳዊት ራሱ እንዲህ ይላል ሕያው ሰው የእግዚአብሔር ክብር ነው። ሕይወት በባሕርይዋ ተንቀሳቃሽ ናትና መኖርን ለማየትና ለማወቅ ዓይነኅሊናችንን ወይም የእምነት አይናችንን መክፈት ማለት ነው። ልባችን በዓለም ላይ ብቻ አተኩሮ እንዳይቀር መንቃት… ማለት ነው። ለዚህም ነው -ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ-… ትነሣኤህን ላመነው ብርሃንህን በኛ ላይ ላክ.. በማለት የሚዘመረው።

ሕይወት ዘለዓለማዊት ስለሆነች አትሞትም። እግዚአብሔር ሕይወት ነው፡፡ የሰው ልጅም ሕይወት ምንጩዋ እና መሠረቷ ከዘለዓለማዊ ሕይወት ነው ፤ ዘፍ 2፡7። “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር አፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።”

ስለሆነም ሕይወትን ሕይወት እንዳልሆነች ሊያረጋት የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል መቼም ፤ የትም ቢሆን ሊኖር አይችልም። የሕይወት ሌላ ስም ብርሃን ነው ፤ ብርሃኑም በጨለማ ያበራል ፤ ጨለማውም ብርሃንን ከቶ ሊያሸንፈው አይችልም። በዮሐ 1፡5 እንዲህ ይላል “ብርሃን በጨለማ ያበራል ጨለማውም አላሸነፈውም።”  

እግዚአብሔር ግን ሁሉን ቻይ ነውና ሞቱ ሕይወትን ትሰጣለች ሕይወትን ለመስጠት የማይሞተው ሞተ ፤ ለሞቱት ሕይወትን ለመስጠት በኃጢአት ለሞቱት የቅድስናን ፤ የንጽሕናን ሕይወት ፤ አዲስ ፍጥረት ለማድረግ አምላክ ሞተ።

የፈጣሪ መሞት እውነትን የሚፈልጋት ሁሉ እንዳይሞትና እሱን እንዳያጣው ነው። የሰውን ልጅ የፈጠረው ለዚሁ ነውና ፤ ሰው ሆይ በዘለዓለማዊ ሕይወት ትኖር ዘንድ እግዘአብሔር ይጠረሃል ፤ ትንሣኤው ላንተ እና ለእኛ ለሁላችን ነው ፤ አምላክ ሞትን አያውቅም ፤ ያወቃትና የተለማመዳት ለኛ ሲል ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ራሳችንን እንድናይ ጥያቄ ያቀርብልናል።

ስለዚህ ፋሲካ ሽግግር ነውና ከየት ወዴት ተሻገርኩኝ…ዐቢይ ጾም ምንን ፀንሶ ምንንስ ወልዶ ይሆን…የጾማችናን የጸሎታችን ውጤትስ ምን በረከት አምጥቶልናል…. ስንደክም ውለን  እንተኛለን ነግቶ ከእንቅልፍ ስንነሳ  ምን ለውጥ አለን… ብለን እንጠይቅ።

ሰዎች በሰኔ በዝናም ወቅት ዘርተው በመስከረም ወይንም በአጨዳ ጊዜ ለመሰብሰብ…ምንስ…እንዴትስ ተንከባከብኩኝ…ምንስ ልሰበስብ በማለት ከመሬት ማለስልስ ብሎም እስካጨዳ እንደማይቦዝኑና እንደማይደክሙ ሁሉ የእኛም ሕይወት ወይም ነፍስ በጊዜዋ ከነፍሬዋ እንድትነሣ አናኗራችንንና ወደ ትንሣኤያችን ለመድረስ ያደረግነውን ጉዞ እንመርምር።  እንግዳውስ የክርስቶስ ትንሣኤ እንደመስተዋት ከፊታችን ይሆንና ራሳችንን እያሳየን በል እስኪ እውነት ተናገር የትንሣኤ ልጅ ነህን? መልስህ አዎን ከሆነ ብጹዕ ነህ ፤ አይደለም ከሆነ ደግሞ ያንተን ትንሣኤ ለማክበር እንደገና አሁንም ጊዜው ያንተው ነው።

ምክንያቱም ትንሣኤ ሕይወትን የመኖር ጉዳይ እንጂ የወቅት ጉዳይ አይደለም። ጊዜውን ወይም ወቅትን ካየሁ አልፏል እንደልማዱም ሊያልፍ ነው ፤ ጊዜ ተንቀሳቃሽ ባቡር…መኪና…ከቦታ ቦታ የሚያደርስ መጓጓዣ ነው እኛም በዚሁ ባቡር ወይም መኪና…ላይ ተሳፍረናል ተሽከርካሪው ከተወሰነለት ቦታ ሳይደርስ መቆምን አያውቅም አሽከርካሪውም በማያሳስት ሁኔታ ወደ ግቡ እያበረረው ነው ፤ አንተ ተሳፋሪ ሰው ወዴት ነህ… ሌሎች ሲሳፈሩ ብቻ አይተን ነው ወይስ… አስበንና አውቀን ፤ ወደንም… ነው የተሳፈረነው… እንግዲያውስ የጊዜውን አሽከርካሪ የኛ ትንሣኤ ግብን ማሳወቅ ይኖርበታል።

በሕይወት የሚያምኑና ተገቢውን ሕይወትን የሚኖሩ ሊሞቱና እንደሌሉ ሊሆኑ አይችሉም። ልጅ በተፈጥሮ ወላጅን ይመስላል ባሕሪያውም ነውና ፤ ዘለዓለማዊ እግዚአብሔር ሰው የሆነው  ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደመሆኑ መጠን ፈጣሪያችን ፤ ሰው እንደመሆኑም መጠን ወንድማችን እኛም ልጆቹ ፤ ወንድሞቹ እህቶቹ ፤ በሕይወትም በሞትም ፤ በትንሣኤም እሱን እንድንመስል ዘለዓለማዊ ፈቃዱ ሆኖአል። እግዚአብሔር በባሕሪው እና በማንነቱ እንዲሁም በሁለ ነገሩ ልዩ የሆነና ልዩነቱንም ለሰውም ልጅ በፍጡር ደረጃ ያካፈለንና የሕያዋን አምላክም ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደልም ፤ ማር፡12፡27። እንግዲያውስ ፋሲካችን ከአሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ የምንሸጋገርበት የደስታ እወጃ እና ብሥራት ነው ፤ በብሥራት ደስታ እንጂ ሐዘን የለም። ስለሆነም በራሱ በጌታ ደስ ይበለን።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከዓለም ሁሉ ከባዱ እሥር ቤት የተዘጋ ልብ ነው ያሉ ሲሆን ፤ በእውነት በሩ ሳይከፈት በውስጥ ገብቶ ሰላም ለአንተ ፤ ለአንቺ ይሁን የሚል ብሥራት ሊሰማ የሚችለው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ይህም የትንሣኤው በዓል ትልቅ መልዕክት ነው። ይህን ተስፋ አድርጋ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ሁኔታ በዘመነ ፋሲካ ተናዘን መቁረብ እንድንጀምር ታዘናለች ፤ ምክንያቱም አንዴ ተዘግቶ እስከ ወዲያኛው ሳይከፈት የሚቀርና ክርስቶስ የማይሰብረው ልብ የለምና ነው። በርግጥ በእንደዚህ ዓይነት አናኗር ውስጥ ራሳችንን ስናገኝ ወደ ሰው ወይም ወደ ነገሮች መፍትሔ ፍለጋ ማሰባችን ግድ ነው ሆኖም ግን የውስጣችን መድረስ ለሰውና ለነገሮች አይቻላቸውም ፤ ክርስቶስ ብቻ በተዘጋውና በተቆለፈው ውስጠኛ ማንነታችን ወይም ግላዊ ድክመታችን ውስጥ የመግባትና የመታደግ ብቃትም ሆነ ፍላጎት አለው። ይህ የአናኗር ትንሣኤ ሲከናወን ብቻ ነው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ፋሲካችን ማለትም መሸጋገሪያችን ክርስቶስ ነው ማለት የምንችለው።

ይህንን ለመፈፀም እና  ለመኖር እንዲያስችለን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋና በረከት ከልጇ ታማልደን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

የተባረከና የተቀደሰ ዘመነ ትንሣኤ ያድርግልን።

መልካም ዘመነ ትንሣኤ!!!

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

01 May 2021, 10:40