ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት 

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለ2013 ዓ.ም የትንሳሄ በዓል ያስተላለፉት መልእክት

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ብፁዓን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያንና/ውያት

ክቡራን ምዕመናን

በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ

ክቡራትና ክቡራን

“አይዟችሁ አትፍሩ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ከፈለጋችሁ ተነሥቶአል” (ማር.16:6)

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በሙሉ እንኳን ለ2013 ዓ/ም  የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን በማለት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስምና በራሴ ስም መልካም ምኞቴን እገልጽላችኋለሁ።

የሰንበት ቀን እንዳለፈ ወደ መቃብሩ ለሄዱት ለእነመቅደላዊት ማርያም መልአኩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን በነገራቸው ጊዜ ልባቸው በደስታና በፍቅር ተሞልቶ ነበር። እርሱ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ ተሻግሯል። እርሱ በሞቱና በትንሣኤው ከአብ ጋር አስታርቆን የሰማይ አባታችን ልጆችም እንድንሆን አድርጐናል። እናም ዛሬ በትንሣኤው ጸጋ ከኃጢያት ተነስተን በእርሱ ልንኖር ያስፈልገናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በቀራንዮ ላይ የተቀበለው ስቃይ ውርደትና ሞት ለሰው ደኅንነት በእግዚአብሔር የታቀደ ነው። እርሱ ከሙታን በመነሣት የሃዘንና የስቃይ ዘመን አልፎ ሰላምና ደስታ አስግኝቶልናል። በመስቀል በፈጸመው መስዋዕትነት ወደ እግዚአብሔር አቅርቦናል። ከእርሱም ዕርቅና ሰላም እንድናገኝ አድርጐናል። እናም በአርባ ጾም ጊዜ ያሳለፍናቸው ጾምና ጸሎቶቻችን ለኃጢያቶቻችን ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ለእኛነታችን መታደስ ሆነው እንዳለፉ ተስፋ እናደርጋለን።

ቅዱስ ጳውሎስ “ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያርቅ ክፉና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ” (ዕብ.3፥12) ይለናል። ስለዚህ በክርስቶስ ትንሣኤ ሁላችንም ክፋትን ሁሉ ከልባችን ውስጥ አስወግደን በክርስትና ጉዟችን ውስጥ ክርስቶስን በመምሰል ከተበላሸው ሕይወታችን ጸድተን የእርሱ አብነት ተከታዮች መሆን ይገባናል። እኛም እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በሕይወት ዘመናችን እምነትና አለኝታችን በአምላካችን ላይ መታደስ ይገባዋል። ይህ እንደ ጥላ ከሚሸሽ እንደ ጭጋግ ጢስ ከሚበን እንደ ጤዛም ባልታወቀ ጊዜ እንደ ዋዛ ከሚረግፈው ሕይወት፣ ከተዋጥንበት ትካዜና ጨለማ መውጫ ቀዳዳውን እንዲያሳየንና እንዳንወድቅ መሠረትና ድጋፍ እንዲሆነን ከእኛ የራቀ የሚመስለው የእግዚአብሔር ፍቅር ወደ ሕዝቦቿና ወደ አገራችን አንዲመለስ በእርሱ ተግሳፅና ምክር እንኑር።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ሲነሣ የሰጠው ትልቁ ስጦታ ሰላም ነው። እኛ እርሱን አምነነው እንድንከተለው እና የሰላም መሣሪያ እንድንሆን ጠርቶናል። ዛሬ በሃገራችን በሀዘን ሆነን የምናየው በጐሣና በሃይማኖት ባለን ልዩነት ላይ ተመስርተን በጥላቻ ንግግር፣ የሰውን ሕይወት በማጥፋት፣ ንብረትን በማውደም፣ በመዝረፍ፣ ሰዎችን በማሳደድ፣ የሃሳብ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት በመሞከር እና ከሰላም፣ ከይቅር ባይነት ይልቅ ጥላቻን በመዝራት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ትውልድ የሚተላለፍ መርዝ ትተን ኃጢያትን ያሸነፈው፣ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ በሚሰጠን ኃይልና ጸጋ ይሄን መጥፎ ሁኔታ መሻገር አለብን።

የሀገራችን ሕዝቦች ሁሉ ሰላም ፈላጊዎች ናቸው፤ ሁሉም ጸሎታቸው ስለ ሰላም ነው። ይህች ሰላም ደግሞ በጥል በጦርነት በኃይል የምትገኝ አይደለችም። ስለሆነም ይህን ሰላም ማግኘት የምንችለው እርስ በእርስ በመዋደድ በመያያዝ በትዕግስትና በመቻቻል ሲሆን በመለኮታዊ ቃሉ “ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ ለእነርሱ አድርጉላቸው” (ሉቃ.6፣31) የሚለውን ቃል ይዘን ስንመራ ብቻ ነው።

በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር አብ መንፈሱን አብልጦ እንዲሰጠን መለመን አለብን። ለዚህ ደግሞ ራሳችንን በንፁህ ልብና ሕሊና አቅርበን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ እውነት እየተመራን በፍቅርና በደግነት ለመኖር የነፍሳችን አባት ወይም ባለቤት የሆነውን አምላካችንን ሌትና ቀን ሳናቋርጥ በመጸለይ አሁን የገባንበት ችግርና መከራ እንዲሁም ጭንቀት፣ ስደት፣ መገፋት፣ ጦርነት ሁሉ ተወገዶ የእርስ በእርስ መዋደድንና ፍቅርን እንዲሰጠን ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ቂምና በቀልን፣ ክፋትና ጥላቻን፣ ጭንቀትና ሐዘንን፣ ደካማነትን አውጥቶ በእርሱ ፋንታ ሰላምና እርቅን ባለፈውም ነገር መጽናናትን እንዲሰጠን እርሱ የሚጠላውን መሥራት ትተን እርሱ የሚወደውን እናድርግ።

እግዚአብሔር በአርዓያና በአምሳሉ ፈጥሮ ካስቀመጠን ከእርሱ ልጅነት ዝቅ ብለን፤ በጦርነት የሰው ነፍስ በማጥፋት፣ ሰውን በማሳደድና በማሰቃየት እግዚአብሔርንና ሰዎችን የሚያሳዝን ስሜት ተፈጥሮብናል። በላያችን በነገሡት ነገሮች እግዚአብሔር የሰጠን ጸጋ እየከሰመ እንዳይሄድ መጠንቀቅ አለብን። በየቦታው ጥይት በሰዎች ላይ እየዘነበ ግልጽ ግድያና ሽብር፣ ስደትና መከራ እየተስፋፋ ሁላችንም ሰላም ነን ለማለት አንችልምና ሁሉን አቁመን ሰላምን እንፈልጋት እንከተላትም። (መዝ.34፣14)

እንደ ዳዊት "ተስፋችን እኮ አንተ ነህ" እያልን እንጸልይ እርሱ የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ተስፋ እንደነበረ ለተቸገሩትና ለተበደሉት ለታመሙትና ለተጨነቁት ሁሉ ተሰፋቸውና ረዳታቸው እንደነበረ ለእኛም ተስፋችንና ረዳታችን እንዲሆንልን ወደእርሱ እንጠጋ።

የተወደዳችሁ ምዕመናን

የጌታችንን የትንሣኤ በዓል በምታከብሩበት ወቅት በሐዘን ላይ ያሉትን፣ የተቸገሩትንና የተሰደዱትን፣ በጐዳና ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን፣ በቤታቸው ሆነው አስታዋሽ ያጡትን በማሰብና በመርዳት እንድታከብሩ አደራ ማለት እወዳለሁ።

በትምህርት፣ በኑሮ፣ በሥራ፣ በስደትና በተፈናቃይነት ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በህመም በየቤታችሁና በየሆስፒታሉ የምትገኙ ህሙማን ጌታ በትንሣኤው ምሕረትን፣ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ የሕግ ታራሚዎች የትንሣኤ በረከትን፣ በጦርነትና በግጭት መካከል ያላችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንዲሁም ልጆቻችን በሁሉም ጐን ያላችሁ የሀገራችን ሕዝቦች እንደዚሁም  በስደት ላይ በሀገር ውሰጥና በውጭ የምትገኙ ተፈናቃዮች በየዕለቱ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች እግዚአብሔር በበጐ አድራጊዎች አቅርቦ ይንከባከባችሁ፣ በዚህ በዓልም ይርዳችሁ።

እግዚአብሔር ለሕዝባችን ሰላሙን ጤንነቱን እርቁን ምሕረቱን ያውርድልን አገራችንን ወደ ሰላም ይምራልን በምሕረቱ ይታረቀን።

መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንልን!

 † ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት

02 May 2021, 11:16