ፈልግ

በኢየሩሳሌም የምትገኘው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ መከራውን ሊቀበል ወደ ኢየሩሳሌም ባታላቅ ክብር የገባበት የሆሳዕና በዓል ባከበረችበት ወቅት በኢየሩሳሌም የምትገኘው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ መከራውን ሊቀበል ወደ ኢየሩሳሌም ባታላቅ ክብር የገባበት የሆሳዕና በዓል ባከበረችበት ወቅት  

የሕማማት ሣምንት

በመላው የክርስቲያን ማሕበረሰብ ዘንድ የሕማማት ሳምንት በሚያዝያ 17/2013 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል። በእዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ እኛን ለማዳን እና ከእግዚኣብሔር ጋር እኛን ለማስታረቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ እየሩሳሌም ከገባበት እለተ ሰንበት አንስቶ ሞትን ድል አድርጎ እሰከ ሚነሳበት ቀን ድረስ ያለውን የአንድ ሳምንት ጊዜ የሚያመልክት ነው።

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራት ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

1.     እሁድ እለት

ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ (ሉቃስ 19፡28-40)

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ቀድሞአቸው ይሄድ ነበር። ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህምጡት። ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።” የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው። እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ። ከዚያም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሳቸውንም በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ አስቀመጡት። ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሳቸውን ያነጥፉ ነበር። በደብረ ዘይት ተራራ ቍልቍል ወደ ሚወስደው መንገድ በተቃረቡ ጊዜ፣ ቍጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት ስላዩት ታምራት ሁሉ ደስ እያላቸው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር፤ “በጌታ ስም የሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!” “በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!” በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት። እርሱም፣ “እላችኋለሁ፤ እነርሱ ዝም ቢሉ፣ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው።

2.     ሰኞ እለት

ኢየሱስ በቢታንያ ሽቱ መቀባቱ (ዩሐንስ 12፡1-11)

የፋሲካ በዓል ስድስት ቀን ሲቀረው ኢየሱስ፣ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ወደሚኖርበት፣ ወደ ቢታንያ መጣ። በዚያም ለኢየሱስ ሲባል ራት ተዘጋጀ። ማርታ ስታገለግል፣ አልዓዛር ከእርሱ ጋር በማእድ ከተቀመጡት አንዱ ነበር። ማርያምም ዋጋው ውድ የሆነ፣ ግማሽ ሊትር ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ አምጥታ በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰች፤ እግሩንም በጠጒሯ አበሰች፤ ቤቱንም የሽቱው መዓዛ ሞላው።

ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ግን በመቃወም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?” ይህን የተናገረው የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቊሮ አልነበረም።

ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ ለቀብሬ ቀን የታሰበ ስለ ሆነ እንድታቈየው ተዋት፤ ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔን ግን ሁል ጊዜ አታገኙኝም።”

በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁድ ኢየሱስ በዚያ መኖሩን ዐውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ብለው ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ከሙታን ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር። ስለዚህ የካህናት አለቆች አልዓዛርን ጭምር ለመግደል ተማከሩ፤ ይህም በእርሱ ምክንያት ብዙ አይሁድ ወደ ኢየሱስ እየሄዱ ያምኑበት ስለ ነበር ነው።

3.     ማክሰኞ እለት

አልፎ እንደሚሰጥ ኢየሱስ መናገሩ (ዮሐንስ 13፡18-38)

“ስለ ሁላችሁ መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኋቸውን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን፣ ‘እንጀራዬን አብሮኝ የቈረሰ ተረከዙን አነሣብኝ’ የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። “ሲፈጸም እኔ እንደሆንሁ ታምኑ ዘንድ፣ ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን ነገርኋችሁ።እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የላክሁትን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔን የተቀበለም የላከኝን ይቀበላል።” ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” ሲል በግልጽ ተናገረ።

ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ “ማንን ማለቱ እንደሆነ ጠይቀው” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ደገፍ ብሎ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህን ቊራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቊራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው። ይሁዳም ቊራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት።

4.     ረቡዕ እለት

ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ (ማቴ 26፡14-26)

ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የነበረውና የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣ “እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን አመቺ ጊዜ ይፈልግ ነበር።

5.     ሐሙስ እለት

ኢየሱስ መከራውን ከመቀበሉ በፊት  ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ራት ከመብላቱ በፊት የሐዋርያቱን እግር ያጠበበት፣ እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የጀመረውን መንፈሳዊ ተልዕኮ እንድያስቀጥሉ በማሰብ ምስጢረ ክህነትን የመሰረተበት እና በተጨማሪም የመጨረሻ ራት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የተካፈለበት ምስጢረ ቅዱስ ቁራባንን የመሰረተበት እለት ነው።

6.     ዐርብ እለት

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሞት የተፈረደበት፣ የተሰቃየበት፣ በመስቀል ላይ ተስቅሎ የሞተበት እና የተቀበረበት የስቅለተ ዐርብ እለት ነው። ይህም የስቅለተ ዓርብ እለት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊነት፣ በጾም እና በጸሎት በስግደት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስትስ ስቃዮን በተቀበለበት ወቅት የተጓዛቸውን አስራ ዐራት የስቃይ መንገዶች የሚታወሱበት የመስቀል መንገድ ጸሎት እና ስግደር በማደርግ ይከበራል።

7.     ቅዳሜ እለት

ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ መሆኑን የምናስታውሰበት እና የእርሱን ከሙታን መነሳት ለማክበር የምንዘጋጅበት እለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ ተሰቃይቶ፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱን፣ ከእዚያም በኋላ ሞትን ድል አድርጎ እንደ ሚነሳ በተስፋ የምንጠባበቅበት ቀን ነው።

8.     እሁድ እለት

ኢየሱስ ከሞት ተነሣ (ዩሐንስ 20፡1-20)

በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች። ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።

“ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።

ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ

ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤ ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት።

እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት።

እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው። ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው”አላት። መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።

26 April 2021, 10:56