ፈልግ

የሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ዘኒቆዲሞስ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ዘኒቆዲሞስ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  

የሚያዝያ 10/2013 ዓ.ም ዘኒቆዲሞስ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.      ሮሜ 7:1-18

2.    1ዮሐ 4:18-21

3.    ሐዋ 5:34-42

4.    ዮሐ 3:1-11

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ኒቆዲሞስን አስተማረ

ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደሆንህ እናውቃለን” አለው።

ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው።

ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።”

ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም።

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! በዚህ ሰንበት ለሕማማት ሳምንት ብሎም ለብርሃነ ትንሣኤው በምንዘጋጅበት የጾም ወቅት ላይ ዛሬም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የቅድስት ቤተክርስቲያን አብሮነት ከእኛ ጋር አለ። ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆችዋ ዘወትር በእግዚአብሔር ቃል እንዲቀደሱና እንዲታነጹ በማሰብ በየዕለቱ የምንባረክበትንና የምንቀደስበትን የክርስትና ሕይወታችንም መመሪያ ጭምር የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ለእያንዳዳችን ታደርሳለች። በዚህም መሠረት እንግዲህ ዛሬ የዓብይ ጾም 6ኛ ሰንበት የሆነውን ዘኒቆዲሞስ የተሰኘዉን ሰንበት እናከብራለን።

በዛሬው ንባባት አማካኝነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለውን ዕቅድ  ወይንም ደግሞ የእግዚኣብሔር ትዕዛዝ ልጆቹን ዘወትር  ወደ መልካምነትና ወደ ጽድቅ እንደሚመራ ያስተምሩናል። በእግዚአብሔር ትዕዛዝ የሚመላለስ ሰው ዘወትር መልካም የሆነውን ፍሬ ይዘራል መልካም የሆነዉን ፍሬ ያጭዳል መልካም የሆነውን ፍሬም ይበላል ከሱም አልፎ ለሌሎች ያካፍላል። በእግዚአብሔር ጸጋ የሚመላለስ ሰው ሕይወቱን በየት አቅጣጫ እንደሚመራ አስቀድሞ ይገነዘባል። ይህንንም ቃል  ቅዱስ ዳዊት መዝሙሩ ምዕራፍ119፡ 97  ላይ ሲመሰክር “አቤቱ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው፣ ለዘለዓለም ለእኔ  ነውና ትዕዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ፣ ከትዕዛዝህ የተነሳ አስተዋልሁ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ፣ ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው ይላል።” እኛም ወደ እግዚአብሔር መጠጋታችን አስተዋዮችና የሐሰትን መገድ ሁሉ እንድንጠላ ያደርገናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚነግረን አይሁዳውያን በእግዚአብሔር ዘንድ ጻድቅ ተብሎ ለመጠራት እነዚህን በቁጥራቸው እጅግ በጣም የበዙትን ሕግጋት ቃል በቃል ለመፈፀም ይተጉ ነበር። አብዛኞቹ አይሁዳውያን ሕግን ቃል በቃል ለመፈፀም ይትጉ እንጂ በሕጉ ውስጥ ባሉት መንፈሳዊ እሴቶች ራሳቸውን ለማሳደግ ያን ያህል አይጨነቁም ነበር። ለእነሱ ሕግን መጠበቅ ብቻ  ዋና ግባቸው አድርገው በመመልከት ህጉን እንጂ ከህጉ የሚመነጨውን ብርሃን ለማስተዋል አልቻሉም። ምን አልባት በዚህም ምክንያት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የአብ አንድያ ልጅ መሆኑንና ወደ ምድር ለእነርሱና በእነርሱም አማካኝነት ለሰው ልጆች ሁሉ ደህንነት መምጣቱን እንዳይቀበሉ እንቅፋት ሆኖ ከጋረዳቸው ምክንያቶች አንዱ ሊሆን ይችላል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመቀጠል ሕግ በማንኛውም ሰው ላይ ስልጣን የሚኖረው በሕይወት ለሚኖር ሰው ብቻ ነው የሞተ ሰው ሕግን የመፈፀም ግዴታ የለበትም። ሰው ከሞተ በኋላ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ሕጎች አይመለከቱትም ከሕግ ውጪ ነው። ስለዚህ እኛም ከክርስቶስ ጋር አብረን ሞተናልና ልክ እንደ አይሁዳውያኑ ለሕግ ሳይሆን ለኃጢአት በመሞት ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋር አብረን በመነሳት በጽድቅ ጎዳና ልንመላለስ ይገባናል።

በአይሁዳውያኑ ሕግ መሰረት እንዲሁም በክርስትናው ባል ከሚስቱ ወይንም ሚስት ከባሏ በሞት ምክንያት ከተለየች ሌላ ለማግባት በሕግ እንደማይያዝ ሁሉ እኛም ቀድሞ ለታሰርንበት ኃጢአት ከሞትን በአዲስ መልክ ከጌታችን እየሱስ ጋር አዲስ ውህደት ለመፍጠርና አብረነው ለመጓዝ የሚይዘን አንዳችም ነገር አይኖርም ምክንያቱም ለኃጢአት በመሞታችን ከቀድሞ ኃጢአታችን ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በእርሱ ጸጋ ተለያይተናልና ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 6፡ 4-5 እንዲህ ይላል፣ እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀቱ ከእርሱ ጋር ተቀበርን፣ ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን። ሰው ከኃጢአት ጋር ሲቆራኝ ከክርስቶስ ፊት ይርቃል ውጤቱም የሞት ፍሬ ማፍራት ብቻ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ሰው ከኃጢአት ጋር ተለያይቶ ከክርስቶስ ጋር ሲቆራኝ ውጤቱ ለሕይወት ፍሬ ማፍራት ነው። ይህንንም በማድረጉ በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ቤቱ ሰላምን ደስታን ፍቅርን ይጎናጸፋል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ልባችንና አእምሮአችን በጽድቅና በመልካምነት የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመፈጸም ካልሆነ በስተቀር በክፋት እንዳይሞላ አበክሮ ያሳስበናል  ምክንያቱም ልባችን በክፋት ከተሞላ አእምሮአችን በተንኮል ከተወጠረ እግራችን ወደ ክፋት እንዲሮጥ እጃችን ኃጢአትን ለመፈጸም እንዲቀድም ምላሳችን ሃስትን ለመናገር እንዲፈጥን መንገድ እንከፍታለን።

 በመጀመሪያው የዮሐንስ መልዕክት 4፡18-21 ሲነበብ እንደሰማነው ሰዎች የሚፈሩት ኃጢአት መሥራትን ሳይሆን ቅጣትን ነው። እግዚአብሔር ግን ለእኛ ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሳ በጌታችን እየሱስ ከርስቶስ በኩል ከኃጢአታችን ሁሉ ነፃ አደረገን በጌታችን እየሱስ ከርስቶስ በኩል ራሱን ለእኛ ለልጆቹ በሙላት ገለፀልን ስለዚህ እኛ በውስጣችን ያለውን ፍርሃት ሁሉ በማስወገድ በፍጹም ፍቅር ልንቀርበው ይገባል። የእግዚአብሔርን ፍርድ በመፍራት ወደ እርሱ የምንቀርብ ከሆነ ፍቅራችን ፍጹም ፍቅር ሊሆን አይችልም። በመጽሐፈ ምሳሌ 1፡7 ላይ “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ይላል ይህ ማለት ግን የአክብሮት ፍርሃት የፍቅር ፍርሃት እንጂ የቅጣት ፍርሃት አይደለም።

እግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ስለሆነ በፍቅር ብቻ ልንቀርበው ይገባል። እርሱንም ማፍቀራችንን በዙሪያችን የሚገኙትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ሁሉ በማፍቀርና በመንከባከብ ልናስመሰክር ይገባል። ምክንያቱም እግዚአብሔርን ማፍቀርና ወንድም እህቶቻችንን ማፍቀር የማይነጣጠሉ ሁልጊዜም አብረው የሚሄዱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። በአንድ መልኩ ስንመለከተው እግዚአብሔር መንፈስ ሰለሆነ እርሱን መውደድና ማፍቀር ሰውን ከመውደድና ከማፍቀር ትንሽ ቀለል እንደሚል ልንገምት እንችል ይሆናል ምክንያቱም በምናደርገው ክፋትና ኃጢአት እግዚአብሔር ከእርግማን ይልቅ ምክርን ከቁጣ ይልቅ ትዕግስትን፤ ከቅጣት ይልቅ ምህረትን፤ ከመራቅ ይልቅ ቅርብነቱን ስለሚያሳየን ይህንን እንደ ሞኝነት ቆጥረነው ሊሆን ይችል ይሆናል ።

በአጠገባችን ያሉ ሰዎች ግን በተለያየ መንገድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ስለሚያበሳጩን፣ ስለሚያሳዝኑን እና ስለሚያናድዱን ለሠራነው ክፋት ወዲያውኑ አፀፋውን ስለሚመልሱልን በሙሉ ልብ ለማፍቀር ይከብደናል  ነገር ግን ልብ ልንል የሚገባው ነገር በ 1ኛ ዮሐንስ 2፡4 ላይ አንደተፃፈው በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች ሳንወድ እግዚአብሔርን እንወዳለን ብንል ሐሰተኞች ነን ሐሰትንም እንናገራለን ይላል። ለዚህ ነው እግዚአብሔርንና ሰውን መወደድ የማይነጣጠሉና ሁልጊዜም አብረው የሚጓዙ እውነታዎች ናቸው የምንለው።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን ሰዎች ሲሰድቡት፣ ሲገርፉት፣ ሲያሰቃዩት እና ሲያዋርዱት ብሎም በመጨረሻም በመስቀል ላይ ሲሰቅሉት እርሱ ግን ስለእነሱ ይጸልይ ነበር አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው በማለት ከእግዚአብሔር ምሕረትን እንዲያገኙ ይለምንላቸው ነበር። እንግዲህ እኛም መከተል ያለብን መንገድ ይህን ነው የቱንም ያህል ወንድሞቻችንንና እህቶቻችን ቢበድሉን፣ ቢያሰቃዩን እና ቢያዋርዱን ስለ እነርሱ ከእግዚአብሔር ምሕረትን መለመን ያስፈልጋል። የበለጠ ወደእነሱ በመቅረብ ልናግዛቸው ይገባል እግዚአብሔር ወደ ልቦናቸው እንዲመልሳቸው ማስተዋልን እንዲጨምርላቸው ወደ እርሱ መጸለይ ያስፈልጋል ይህ ነው እግዚአብሔርን በፍጹም ነፍስ  በፍጹም ኃይል በፍጹም ልብ ባልጀራንም ደግሞ እንድ ራስ አድርጎ መውደድ ማለት።

ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯልና በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የእግዚአብሔር የሆነ ነገር አለ እንግዲህ በዓይናችን የሚታየውን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን  በውስጡ የእግዚአብሔርን መንፈስ የያዘውን ሰውን ሳንወድ እንዴት አድርገን በዓይናችን ያላየነውን እግዚአብሔርን እንወዳለን ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን?

በዚህ በዛሬው የዮሐንስ ወንጌል 3፡1-11 ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ከሚባል የአይሁድ ኃይማኖታዊ ሸንጎ አባልና የአይሁድ አለቃ ጋር ስላደረገው ውይይት እንመለከታለን። ኒቆዲሞስ የአይሁድን ሥርዓት ጠንቅቆ የሚያውቅና የተማረ ሰው ነበረ። ነገር ግን በአይሁድ ሸንጎ ዘንድ እንደ ነብይ ከማይቆጠረውና እንደ ነውጠኛ ከሚታየው ከእየሱስ ዘንድ አንድ እውነታ እንዳለ በጽኑ ያምን ነበረ። ይህ ኒቆዲሞስ ውስጠ ቀናና በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነቢይነት በእግዚአብሔር አንድያ ልጅነት ያምን የነበረ በዚህም ምክንያት ማታ ማታ ወደ እርሱ በመሄድ ከእየሱስ ጋር ይወያይ ነበረ።

አይሁዳውያኑ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ በአንፃርነት ሲነሱ ሲቃወሙ ሰዎችን ሲያነሳሱ ኒቆዲሞስ ግን እየሱስን በተቻለው አቅም ይከላከልለት ነበር ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል 7፡50-52  እንዲህ ይነበባል። ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምን እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ላይ ይፈርዳልን አላቸው? እንርሱም መለሱና አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሳ መርምረህ እይ አሉት ይላል። ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የአይሁድ ሕግ አስተማሪ ቢሆንም ሕጋቸው ስለ ተከሳሽ ማንነት ሳያጣራ የእርሱን የመከላከያ ቃል ሳይሰማ ፍርድ መስጠት አግባብ አለመሆኑን አሳምሮ ያውቃል ይህም የእግዚአብሔርን ሕግ በተገቢ መልኩ አለመተርጎም መሆኑን ተረድቷል።

ይህ መልካም ሰው ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የነበረው አመለካከት በዚህ አልተቋጨም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የቅርብ ሰዎች የነበሩት ሐዋርያት ከእርሱ ጋር አብረው የበሉና አብረው የጠጡት ከእርሱ ጋር አብረው ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ብዙ ተዓምር ሲያደርግ በዓይናቸው የተመልከቱት በዛ በጭንቅ ሰዓት ሲሸሹት ይህ ኒቆዲሞስ ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞተ በኃላ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ በመምጣት እንደ አይሁድ አገናነዝ ስርዓትና ልማድ ከገነዙት ከሽቶ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከከፈኑት በቅርቡ በነበረም የአትክልት ሥፍራ አዲስ መቃብር ውስጥ ካኖሩት መልካም ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው። ዮሐንስ ወንጌል 19፡39።

ይህ ሰው በዚህ ድርጊቱ ከሐዋርያቱ የበለጠ ለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያለውን ታማኝነት አስመስክሯል። ይህ እንግዲህ ለእያንዳዳችን የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንም እንኳን ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕብረት ቢኖረንም ለእርሱ ያለንን ታማኝነት በይፋና ጉልህ በሆነ መልኩ ማንንም ሳንፈራ ማስቀመጥ ይገባናል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር በነበረው ውይይት ያስተማረው አንድ ጥልቅና መሠረታዊ  ነገር አለ ይኸውም በዚሁ በዛሬው በዮሐንስ ወንጌል 7፡5-6 ያለው “እውነት እውነት እልሃለው ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው የሚለው ነው።”

እውነት ነው ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ የሚችለው ሕግን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሲታደስ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አምኖ በዕምነቱም ምክንያት አዲስ ሕይወት መልበስ ሲችል ብቻ ነው። በገላትያ 2፡16 ላይ እንዲህ ይላል “ነገር ግን ሰው በእየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አወቅን ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ እየሱስ አምነናል።” እንግዲህ ዛሬም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እያንዳዳችን በአዲስ መልክ ከውኃና ከመንፈስ እንድንወለድ ይፈልጋል ይኸውም ኃጢአታችንን በምስጢረ ንስሃ አማካኝነት እንድናጥብና ለኃጢአት እንድንሞት ብሎም በእግዚአብሔር መንፈስ እንድንሞላ ይህንንም አድርገን የዘለዓለማዊ ሕይወት ተካፋዮች አንድንሆን ይፈልጋል።

ሰው በጥምቀትና በምስጢረ ንስሃ አማካኝነት ኃጢአቱን ካጠበ መላ እሱነቱ በመንፈስ እንደሚሞላ ግልጽ ነው ይህ መንፈስ ነው ታዲያ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንድንመላለስ የሚያደርገን የሰይጣንን ዕቅድ በሙላት እንድንዋጋ ብርታት የሚሆነን ዘወትር ከሚስጢራት ጋር የሚያቆራኘን። ስለዚህ ሰው ሁል ጊዜ በመንፈስና በሥጋ መታደስ ይገባዋል ይህንን ካደረገ ብቻ ምድራዊ ሕይወቱ የተስተካከለ የታረመና የተቀደሰ ይሆናል የመንግሥተ ሰማይም እጩ ይሆናል።

እንግዲህ እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ ውስጥ እየተመላለስን መኖር እንድንችልና የእርሱ እውነተኛ ደቀማዛሙርት በመሆን በተለይም በዚህ የጾም ወቅት መንፈሳዊ ፍሬ የምናፈራበት እንዲሆንልን የዘውትር ጠባቂያችንና አማላጃችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ጠበቃ ሆና ትቁምልን በሥጋና በመንፈስ ለመታደስ እንድንችል በረከቱን ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን።

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

17 April 2021, 20:48