ፈልግ

የመጋቢት 26/2013 ዓ.ም ዘደብረ ዘይት ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 26/2013 ዓ.ም ዘደብረ ዘይት ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  

የመጋቢት 26/2013 ዓ.ም ዘደብረ ዘይት ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.     1ተሰ. 4፡13-18

2.     2ጴጥ 3፡7-14

3.     ሐዋ.ሥ. 24፡1-21

4.     ማቴ 24፡1-14

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የዓለም መጨረሻ ምልክቶች

ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ፣ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱ ግን፣ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተክቦ የምታዩት፣ ሳይፈርስ እንዲህ እንዳለ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም” አላቸው።

በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ በማለት በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ ትሰማላችሁ፤ እነዚህ ነገሮች የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ሆኖም መጨረሻው ገና ስለ ሆነ በዚህ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው።

“በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም። ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ። ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘደብረ ዘይት ወይም ደግሞ የዐብይ ጾም አምስተኛ ሳምንት እኩለ ጾም የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን።

በዛሬው  በመጀመሪያ መልእክት ማለትም 1ተሰ.4፡13-18፡- ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰሎንቄ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱ ከመሞታቸው በፈት ወዲያዉኑ ተመልሶ ይመጣል ብለው ያስቡ ለነበረው የተሳሳተሐሳብ ትክክለኛና ቀጥተኛ መልስ ሲሰጣቸው እናያለን። ይህ መልስ ዛሬም ለኛ በዚህ ዘመን ለምንኖር ሰዎችም ጭምር ያገለግላል።

እንዲህም ይለናል ወንድሞቼ ሆይ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አትሁኑ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አትዘኑ ምክንያቱም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳት ለጥያቄዎቻችን ሁሉ አጥጋቢ መልስ ይሰጠናል። 1ኛ ቆሮ 15፡55 ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ?” እያለ የሞትን ሽንፈት ያበስረናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ይሁን ከመጣ በኃላ እምነት ያለውም ይሁን እምነት የሌለው ሰው በውስጡ የሚያሰላስለው አንድ ጥያቄ አለ ይኸውም የሰው መጨረሻ ወይም የሰው ፍጻሜ ምን ይሆናል? ሰው ከሞተ በኃላ ወደየት ይሄዳል? ምንስ ይገጥመዋል የሚሉት ናቸው።

እያንዳንዱ ሃይማኖት የራሱ የሆነ መልስና አማለካከት እንዲሁም እምነት  አለው እኛ ክርስቲያኖች ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ በመነሳቱ ሞት የሰው ፍጽሜ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት እንናገራለን ይህንንም እምነታችንን በጸሎተ ሃይማኖት በሙታን ትንሳኤ በዘለዓለም ሕይወት አምናለሁ ብለን የምስክርነት ቃላችንን እንሰጣለን።

ሞት የምድራዊ ሕይወታችን ማብቂያ ቢሆንም የአዲሱ ሰማያዊ ሕይወት ደግሞ መጀመሪያ መሆኑን ልንረዳ ይገባል። ስለዚህ ራሳችንን ማዘጋጀት ያለብን ይህን ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመውረስ እንጂ ምድራዊ ሕይወት ለማጣጣም ብቻ መሆን የለበትም፤ ይህን ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመውረስ የሚያበቃንን ሥራ ካልሠራን ዘለዓለማዊ ሞት ይጠብቀናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሁሉ አንዲድን ስለሚፈልግ መንገዱን አበጅቶልናል አቅጣጫውንም አሳይቶናል።የዮሐንስ ወንጌል ም 10፡9 ላይ “በሩ እኔ ነኝ ይለናል በዚህ በር የሚገባ ቢኖር ይድናል ይገባል ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል” ይላል። ነገር ግን በዚህ መንገድ ለመጓዝ በዚህ በር ለመግባትና ለመውጣት ምርጫው የየግላችን ነው። የማቴዎስወንጌል ም 7፡ 14 ላይ እንደሚጠቅሰው ወደ እውነት የምትወስደው በሯ ጠባብ መንገዷም የቀጠነች መሆኗን ማስታወስ ያስፈልጋል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚመክረን በሕይወታችን ስንፍናና ተስፋ መቁረጥን ከውስጣችን ነቅለን በማውጣት በመንፈሳዊ ሕይወታችን እየበረታንና እያደግን ልንሄድ ይገባል ምክንያቱም ስንፍናና ተስፋ መቁረጥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን አለመጠንከር ምክንያት የሚመጣ በሽታና የሚያስከትለውም መንፈሳዊ ውድቀት ወይንም ችግር ሰፊ በመሆኑ ነው።

በሁለተኛው የጴጥሮስ መልዕክት ምዕራፍ 2 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው ቅዱስ ሐዋርያው  ጴጥሮስ የክርስቶስ መዘግየት ሊያስጨንቀን እንደማይገባ ይነግረናል፤ ምክንያቱም የጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መዘግየት ለእኛ ለሰዎች የመዳንን ፀጋ ለመስጠት ወደ ንሰሐ የምንገባበትን ዕድል ለሁላችን ለማመቻቸት አስቦ ነው።

ይህንን ሁሉ ዕድል ከሰጠን በኃላ ግን ድንገት ሊመጣ ይችላል የዛን ጊዜ ንስሐ ለመግባት ጊዜ አይኖረንም።  እያንዳንዳችን መቼ እንደምንጠራ አናውቅም ዛሬ፣ ነገ፣ ከነገ ወዲያ፣ከሰዓት በኋላ አናውቅም ስለዚህ ዘወትር ከኃጢአት ርቀን በንስሐ ታጥበን ተዘጋጅተን ልንኖር ያስፈልጋል።

ሰው ድንገት አደጋ ደርሶበት ሕይወቱ ወድያውኑ ሊያልፍ ይችላል በዛን ጊዜ ንስሐ ለመግባት ሁኔታው አይፈቅድም ይሆናል።  ስለዚህ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደው ጥሪ መቼ እንደሆነ ስለማይታወቅ ዘወትር ተዘጋጅተን መንቀሳቀስ ይገባናል። ዘወትር ወደ ቅድስና ወደሚወስደን ወደ ቅድስና  ወደሚመራን ከኃጢአታች ወደ ሚያጥበን ወደ ሚስጢረ ንስሐ ያለመታከት ጉዞ ልናደርግ ይገባል።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትም ልክ እንደዚሁ ድንገት ሊሆን ይችላል አሁን ግን ጊዜ ሰጥቶናል ዕድል ሰጥቶናል፣ በዕድሉ መጠቀም የየራሳችን ፈንታ ነው።

ኖህ መርከቡን በመሥራት ላይ እያለ ከሠራም በኃላ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ይለምናቸው ነበር እነርሱ ግን አሾፉበት የመርከቡ በር ከተዘጋ በኃላ ግን እባክህ እያሉ ቢለምኑትም ሊሆንላቸው አልቻለም።

እነዛ 5ቱ ብልህ ያልሆኑ ወይም ሞኞቹ ልጃገረዶችም ዘይት ሊገዙ በሄዱበት ሙሽራው መጣ እንግዳው ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ውስጥ ገብቶ በሩ ከተዘጋ በኃላ ደረሱ እናንተን አላውቃችሁም ወደመጣችሁበት ተመለሱ ተባሉ።

ይህ ሁሉ ተገቢውን ነገር በጊዜው እንድናደርግ ያስታውሰናል ያስተምረናልም። በዓለም መጨረሻ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በድፍረት መቆም እንድንችል እንዳናፍር ከአሁን ጀምሮ ሕይወታችንን ማስተካከል ይገባናል።

ማቴ.24፡1-14 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ፍፃሜ ብዙ ነገር መናገሩን እናስተውላለን።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ብዙ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ተሰቅሎ እንዳዳነን የመስቀል መንገድንም እንዳስተማረን እኛም ያለምንም መታከት በየዕለቱ መስቀላችንን ተሸክመን ልንከተለው ይገባል ይህ ነው የትንሳኤ ጉዞ።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቶስ ፍቅር ሲል ብዙ መከራ ተቀብሏል በመስቀል ጉዞ ውስጥ በማለፍ የትንሳኤ ተሳታፊ እንደሚሆን ተረድቷል እኛም በዚህ በመስቀል ጉዞ ወደዘለዓለማዊ ደስታ እንደምንደርስ የምስክርነት ቃሉን ይሰጠናል።

የዛሬው የዕለቱ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበላችን ምክንያት በተለይም በመጨረሻው ዘመን ብዙ መከራና ችግር እንደሚደርስብን ይናገራል። ነገር ግን ሕይወታችን በጸሎትና በእምነት የጠነከረ ከሆነ ምንም ዓይነት የፈተና ማዕበል አያናውጠንም።  በዛች ጠባብ መንገድ ላይ በፅናት ለመረማመድ አያስቸግረንም።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደተናገረው እስከ መጨረሻ የሚፀና ይድናል እንዳለው እኛም በፈተናዎች መብዛት ሳንሰናከል በፅናት እንድንቆም ያስፈልጋል።

ከዚህም በፊትም እንደምንለው ፈተናዎች ሁሉ የእምነታችን መጠንከርና የእምነታችንን ፅናት ማሳያ ሥፍራና ቦታ እንጂ ከእምነታችን ወደ ኃላ የማፈግፈጊያ ምክንያት ሊሆኑ አይገባም።

ምንም እንኳን የሃሰት ነቢይ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ በስሙ ሊያስተኝ ቢመጣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ቢነሳ ረሃብና ቸነፈርም ምድርን ቢያናውጥ በጽናት ከቆምኩበት ዓለት ማንም ፈቀቅ ሊያደርገኝ እንደማይችል ላስመሰክር ይገባል።

በክርስቲያናዊ አካሄዳችን ላይ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች በሙሉ እምነታችን ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን የምንፈትሽበትና በዛው መጠን ፀጋና በረከት ከእግዚአብሐር የምንቀበልበት አጋጣሚ ነው። አሁን የምንገኝበት የእኩለ ጾም ሰንበትም እስከ አሁን ባለፉት አራት የጾም ሳምንታት ውስጥ ምን ያህል መንፈሳዊ ለውጥ እንዳመጣንና እንዲሁም ደግሞ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ትንሳኤ ለማክበር ወደፊት እየተጠጋን መሆኑን ያበስሩናል። በዚህም ጊዜ የበለጠ መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግና ለሚገጥሙን እክሎች በሙሉ መንፈሳዊ ምላሽ በመስጠት እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን ልናሳይበት ይገባል።

በዚህም ወቅት በፈተናው ሳንሰናከል ጠንክረን ቆመን ከተገኘን የበለጠ የምንጠነክርበትንና የበለጠ ምስክር የምንሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንድንችል ጸጋውን እንዲያበዛልን። በፈተናው ተሸንፈንም ከሆነ ደግሞ በንስሐና ጾም ጸሎት አማካኝነት ታድሰን ተመልሰን ዳግመኛ ላለመውደቅ በእግዚአበሔር ጸጋ እየታገዝን የምንሄድበትን ብርታት ለእያንዳዳችን እንዲሰጠን ዛሬ ነገ ሳንል ጉዞአችንን መጀመር እንዳለብን ያሳስበናል።

ለዚህም ዘወትር የቅርብ እረዳታችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ይህንን ጸጋና በረከቱን ታሰጠን በፊቱም ጠበቃ ሁና ትቁምልን።

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

03 April 2021, 11:21