ፈልግ

የሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም 4ኛ የዐብይ ጾም ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም 4ኛ የዐብይ ጾም ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የሚያዝያ 03/2013 ዓ.ም 4ኛ የዐብይ ጾም ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.     2ኛ ዜና መዋዕል 36፡14-16፣ 14-21

2.     መዝሙር 136

3.     ኤፌሶን 2፡4-10

4.     ዮሐንስ 9፡1-41

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።

የእለቱ አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደ ምን አረፈዳችሁ!

በዚህ የዐብይ ጾም አራተኛ እለተ ሰንበት (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር የሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናንን ይመለከታል) መስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓተ መግቢያ ላይ “ኢየሩሳሌም ሆይ ደስ ይበልሽ ...” (ኢሳያስ 66፡10 ይመልከቱ) በማለት ይጀምራል። ለዚህ ደስታ ምክንያት ምንድነው? በእዚህ በምንገኝበት የዐብይ ጾም አኩሌታ ላይ የደስታችን ምክንያት ምንድነው? የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚነግረን “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ 3፡16) ይለናል፣ ይህ አስደሳች መልእክት የክርስትና እምነት ልብ ነው - የእግዚአብሔር ፍቅር በከፍተኛ ሁኔታ የተገለጠው ለእኛ ደካሞች እና ኃጢአተኛ ለሆንን የሰው ልጆች አንድያ ልጁን በመስጠት ነው፡፡ ለእኛ ለሁላችን አንድያ ልጁን ሰጠን።

በኢየሱስ እና በኒቆዲሞስ መካከል በሌሊት በተደርገው ውይይት ውስጥ የሚታየው ይህ ነው ፣ ይህ ክፍል በተመሳሳይ የወንጌል አንቀፅ ውስጥ ተገልጧል (ዮሐ 3፡14-21 ይመልከቱ)። ኒቆዲሞስ ፣ ልክ እንደ እያንዳንዱ የእስራኤል ሕዝብ አባል ፣ መሲሑን ይጠብቃል ፣ በዓለም ላይ በኃይል የሚፈርድ ለየት ያለ ጠንካራ ሰው እንደ ሚመጣ ይጠባበቃል። ይልቁንም ኢየሱስ በሦስት ዓይነት መንገዶች ራሱን በማቅረብ ይህንን ተስፋ ይቃወማል፣ የሰው ልጅ በመስቀል ላይ ከፍ ከፍ እንደ ሚል፣ የእግዚአብሔር ልጅ ዓለምን ለማዳን እንደ ተላከ እና እውነትን የሚከተሉ እና ውሸትን የሚከተሉ ሰዎችን የሚለይ ብርሃን እርሱ እንደ ሆነ ይናገራል። እስቲ እነዚህን ሦስት ገጽታዎች እንመልከት- የሰው ልጅ ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እና ብርሃን። ኢየሱስ ከሁሉ አስቀድሞ ራሱን የሰው ልጅ አድርጎ አሳይቷል (ዮሐንስ 3፡14-15)። ጽሑፉ የነሐስ እባብን ዘገባ ይጠቅሳል (ዘዑልቅ 21: 4-9  ይመልከቱ) በእግዚአብሔር ፈቃድ ሕዝቡ በመርዛም እባቦች ሲጠቃ በበረሃ ውስጥ በሙሴ አማካይነት በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ነበር፣ በእነዚህ እባቦች የተነደፉ ሰዎች ይህንን ከነሐስ የተሰራውን እባብ የተመለከቱ ሁሉ ድነው ነበር። በተመሳሳይ መልኩም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የነበረ ሲሆን በእርሱ የሚያምኑ ከኃጢአት ተፈወሱ በሕይወትም ይኖራሉ።

ሁለተኛው ገጽታ የእግዚአብሔር ልጅ ነው (የሐንድ 3፡16-18)። እግዚአብሔር አብ ልጁን እስከ “መስጠት” ድረስ ሰውን ይወዳል - ቃል ስጋ በለበስበት ወቅት ለእኛ ልጁን ሰጥቷል፣ አሁንም ለእኛ ሲል እንዲሞት አሳልፎ ሰጠው። የእግዚአብሔር ስጦታ ዓላማ እያንዳንዱ ሰው የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው በእውነቱ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ላይ ለመፍረድ ሳይሆን ነገር ግን ዓለም በኢየሱስ እንዲድን ነው። የኢየሱስ ተልእኮ የማዳን ፣ ሁሉንም ሰዎች የማዳን ተልዕኮ ነው።

ኢየሱስ ለራሱ የሰጠው ሦስተኛው ስም “ብርሃን” የሚለው ነው (የሐንስ 3፡19-21)። ቅዱስ ወንጌል “ብርሃን ወደ ዓለም መጥቷል ፤ ሰዎች ግን ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ” ይላል (የሐንስ 3፡19)። ኢየሱስ ወደ ዓለም መምጣቱ ወደ ምርጫ ያመራናል - ጨለማን የሚመርጥ ሁሉ የውግዘት ፍርድ ይገጥመዋል ፣ ብርሃንን የመረጠ ሁሉ የመዳን ፍርድ ይኖረዋል። ፍርዱ ሁል ጊዜ የእያንዳንዱ ሰው ነፃ ምርጫ ውጤት ነው - ክፉን የሚያደርግ ሰው ጨለማን ይፈልጋል ፣ ክፋት ሁል ጊዜ ይደብቃል ፣ ራሱን ይሸፍናል። እውነትን የሚፈልግ ማለትም መልካም የሆነውን በተግባር የሚያደርግ ወደ ብርሃን ይመጣል የሕይወትን ጎዳና ያበራል። በብርሃን የሚሄድ ፣ ወደ ብርሃን የሚቀርብ ፣ ክፉ የሆኑ ነገሮችን ሳይሆን መልካም ሥራን መሥራት ይችላል። በዐቢይ ጾም ወቅት በተለይ ልናደርገው የሚገባው ጉዳይ ይህ ነው፣ ብርሃንን ወደ ሕሊናችን ለማምጣት፣ ልባችንን ወደ ማለቂያ ለሌለው የእግዚአብሔር ፍቅር ፣ ርህራሄን እና ቸርነትን ለተሞላ ምህረቱ ማቅረብ፣ ይቅር ማለት ይኖርብናል። ይቅርታን በትህትና ከጠየቅን ሁል ጊዜም እግዚአብሔር ይቅር እንደሚል አትዘንጉ። ይቅርታን መጠየቅ ብቻ በቂ ነው እርሱም ይቅር ይላል። በዚህ መንገድ እውነተኛ ደስታን እናገኛለን እናም በሚታደስ እና ህይወትን በሚሰጥ የእግዚአብሔር ይቅርባይነት መደሰት እንችላለን።

እራሳችን በኢየሱስ "ውስጥ ማስገባት እንዳንፈራ” እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን። ደስታችን የተሟላ ይሆን ዘንድ ጤናማ የሆነ ቀውስ ውስጥ መግባት ያስፈልጋልና።

10 April 2021, 11:07