ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የዓለም መንግስታት ክትባት ለድሃ ሀገራት እንዲደርስ እንዲሠሩ ጥሪ አቀረቡ!

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሁሉም ወገን COVID 19 የመከላከል እርምጃዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና የዓለም መንግስታት ክትባት ለድሃ ሀገራት እንዲደርስ በህብረት እንዲሠሩ ጥሪ አስተላለፉ።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በአሁኑ ጌዜ የCOVID 19 ስርጭት እያየለ፣ የምናውቃቸውን እና የምንወዳቸውንም ሁሉ እያጣን በመሆኑ ኢዮጵያውያን በጤና ሚኒስቴር በኩል በየጊዜው የሚተላለፉልልን መመሪያዎች በማክበር ንጽህናችንን በመጠበቅ፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክን በአግባቡ በማድረግ እና ርቀታችንን በመጠበቅ ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድናደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል። አያይዘውም በመላው ዓለም የCovid 19 ወረርሺኝ ከተከሰተ ጀምሮ ብዙ ምርምር ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ በእግዚአብሔር ቸርነት ክትባቱ መገኙቱ ወረርሺኙን በዘላቂነት ለመግታት የሚያግዝ በመሆኑ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ብለዋል። የዓለም መንግስታትም ክትባቱ ለድሃ ሀገሮች ጭምር መድረስ እንዲችል  ትብብር እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም ክትባቱ በምርምር እና ጥናት የተገኘ ለህጻናት እና ለአዋቂዎች እንደሚሰጡ ሌሎች ክትባቶች ሁሉ በእውቀት እና በጥበብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ቤተክርስቲያናችን ትቀበለዋለች። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት እና ሳይንስ እንደማይቃረኑ ግልጽ አስተምህሮ ያላት በመሆኑ የሳይንሳዊ ምርምር ውጤቶችን መቀበል እና በእነርሱ መገልገል ፈጽሞ በእግዚአብሔር አለማመን አይደለም። ሀይማኖት ለአመክንዮ እንደሚያስፈልገው ሁሉ አመክንዮም ለሃይማኖት ያስፈልገዋል ብለዋል።

የCOVID 19 ክትባትን መከተብ  ለራሳችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን የሚገኙ ወንድም እና እህቶቻችንን ለመጠበቅ ያለብንን ኃላፊነት መወጣትም ጭምር ነው። የወረርሺኙ ስርጭት ባለበት እንዲገታ የበኩላችንን እገዛ እገዛ ማድረግም ማለት ነው። በመሆኑም ክትባቱ ተገቢ እና አስፈላጊ ነው።

ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሀብታሞች ብቻ ተከትበው ድሆች ሳይከተቡ ቢቀሩ ዘላቂ መፍትሄ ሊገኝ አይችልም በማለት ባለፈው የፈረንጆች የፋሲካ በዓል ላይ የዓለም መንግስታት ክትባቱ በተለይ ድሃ ለሆኑ ሃገራት መዳረስ እንዲችል ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈውላቸዋል። እርሳቸው ራሳቸውም ክትባቱን በመከተብ አብነት ከመሆን አልፈው በሚኖሩበት በቅድስት መንበር አካባቢ የሚገኙ ድሆችም ክትባቱን እንዲያገኙ አድርገዋል።

በእኛም ሕብረተሰብ ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ወገኖቻችን፣ አረጋውያን እና አቅመደካሞችን በተለይ ደግሞ በየቤታቸው በተለያዩ ምክንያቶች የአልጋ ቁራኛ ሆነው የሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ ጋር ይደርስ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

ብፁዕነታቸው ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት ዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም.  በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የሥ ራኃላፊዎች እና የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች በተገኙበት የCOVID 19 የመጀመሪያ ዙር ክትባት በተከተቡበት ወቅት ነው። ብፁዕነታቸው የCOVID 19 ክትባት ወደ ሀገራችን ገብቶ በጤና ሚኒስቴር በኩል ለሕዝባችን እንዲዳረስ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ምስጋናችንን እየገለጽን መንግሥት ክትባቱን ለሁሉም ለማድረስ ለሚያደርገው ጥረት ቤተክርስቲያናችን ከጎናችሁ መሆኗን ለማረጋገጥ እወዳለሁ ብለዋል።

09 April 2021, 11:44