ፈልግ

የመቁጠርያ ጸሎት ጉዞአችንን ከማርያም ጋር በፍቅር እንድንጓዝ ይረዳናል። የመቁጠርያ ጸሎት ጉዞአችንን ከማርያም ጋር በፍቅር እንድንጓዝ ይረዳናል። 

የመቁጠርያ ጸሎት እንዴት የካቶሊኮች ጸሎት ሊሆን እንደቻለ የሚያሳይ አጭር ታሪክ

ከጥንት ጀምሮ ገዳማዊያን፤ካህናት፤ ሲስተሮች (እህቶች)፤ ወንድሞች ሁሉ 150ውን የመዝሙረ ዳዊት ምዕራፎች ለዕለታዊ ጸሎት ይጠቀሙ ነበር፣ ሆኖም ግን ይህ በቤታቸው ሆነው ለመጸለይ ለሚፈልጉ ምዕመናን አስቸጋሪ ነበር፣ ምክንያቱም በድሮ ጊዜ መዝሙረ ዳዊት ማግኘት በጣም ከባድ ስለነበር ነው፤ እንደዛሬ መጽሐፍትን በህትመት የማባዛት ቴክኖሎጂ ያልታወቀበት ዘመን ስለነበር እያንዳንዱ መጽሐፍ በእጅ ነበር የሚጻፈው፣ ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ሕዝብ ማንበብና መጻፍ አይችልም ነበር፣ በዚህ ሁኔታ የነበረው የእግዚአብሔር ሕዝብ የመቁጠርያ ጸሎትን ፈጠረ፣ 150 ጊዜ “ጸጋ የሞላሽ ማርያም” እየተባለ የክርስቶስን የልጅነት ሕይወቱን፤ ሥቃዩንና ሞቱን፤ እንዲሁም ከሞት መነሳቱን እያሰላሰሉ መጸለይ ተጀመረ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በቅርቡ ደግሞ ር.ሊ.ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የኢየሱስን ይፋዊ ሕይወቱንና ሥራውን የሚያስታወሱ አምስት ምሥጢራትን በመጨመር የብርሃን ምሥጠራት ተብሎ እንዲጠሩ ደንግገዋል፣ እመቤታችን ቅድስት ማርያም በፈረንሳይ አገር ሉርድ በተባለ ሥፍራ እና በፖርቹጋል ሀገር ፋጢማ በተባለ ሥፍራ ለሦስት ህጻናት በተገለጠች ጊዜም የመቁጠርያ ጸሎትን አዘውትረው እንዲጸልዩ ታበረታታቸዉ ነበር። የመቁጠርያ ጸሎት በምናደርስበት ጊዜ ለመቁጠር እንዲያመቸን ከእንጨት ወይም ከብረት የተሠሩ ድቡልቡል ክብ ነገሮችን ለመቁጠር እንጠቀማለን፣ ይህም የመቁጠርያ ጸሎት ጉዞአችንን ከማርያም ጋር በፍቅር እንድንጓዝ ይረዳናል።

በክርስቶስ ሕይወት ዙሪያ በምናደርገዉ የመቁጠርያ ጸሎት ጉዞ አራት ደረጃዎች አሉት፤

የመጀመሪያው ደረጃ፡ የክርስቶስን የመጀመሪያዎቹ የ12 ዓመታት ህይወቱን የሚመለከቱ ሲሆኑ እነሱም የደስታ ምሥጢራት ተብለዉ ይጠራሉ፣

ሁለተኛዉ ደረጃ፡ የክርሰቶስን ይፋዊ ሕይወቱንና ሥራዎቹን የሚመለከቱ ሲሆኑ እነሱም የብርሃን ምሥጢራት ይባላሉ፣

ሦስተኛዉ ደረጃ፡ የኢየሱስን ሥቃይና ሞቱን የሚያስታውሱ ክፍሎች ናቸው፤ እነዚህ ክፍሎች የህማም ምሥጢራት ይባላሉ፣

አራተኛዉ ደረጃ፡ የክርስቶስን ከሙታን መነሳት የሚያወሱ ናቸዉ፣ እነዚህ ደግሞ የክብር ምሥጢራት ተብለው ይጠራሉ፡፡

ከእያንዳንዱ አሥር “ጸጋ የሞላሽ” በኋላ የሚደገመው የፋጢማ ጸሎት

ከእያንደንዱ አሥር “ጸጋ የሞላሽ” በኋላ የሚከተለውን የፋጢማ ጸሎት ተብሎ የሚጠራውን ጸሎት እንደግማለን ይህም ጸሎት የሚከተለው ነው . . .

“ጌታ ሆይ በደላችንን (ኃጢአታችንን) ይቅር በለን፣ ከገሃነም እሳት ሰዉረን፤ ለነፍሳት ሁሉና ያንተ ምህረት ለሚያስፈልጋቸዉ ሁሉ መንግስተ ሰማይን ክፈትላቸዉ፤ አሜን።”

የመቁጠርያ ጸሎትን እንዴት መጸለይ እንዳለብን የሚያሳይ ምሳሌ

እዚህ ላይ የመጀመሪያዎቹን አስሮች ወይም የመጀመሪያ የደስታ ምሥጢር እንዴት እንደሚጸለይ እንይ፤  “ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ተጸነሰ” በሚገልጸው ምስጢር ላይ እናሰላስላለን።

በዚህ ምስጢር፡

-   ሊቀ መልአኩ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ማርያም ቤት ሲገባ በሀሳባችን እናስታውሳለን፤

-   ከዚያም አሥሩን “ጸጋ የሞላሽ” እናደርሳለን፤ ይህ አሥሩ “ጸጋ የሞላሽ” ለርሷ በጣም ቅርብ እንድንሆን ይረዳናል፤ በተጨማሪም በጸጥታ እየጸለይን በመልአኩ ብሥራት ጊዜ የማርያምን ቤት የሞላውን ራስን በሙላት ለእግዚአብሔር የመክፈትን ድባብ በመንፈስ እንቃኛለን፡፡

የመቁጠርያ ጸሎታችንን መስቀሉ ያለበት ቦታን በመያዝ የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት በመድገም እንጀምራለን፣ ከዚያም በኋላ ሦስቱን ትንንሽ ድቡልቡል (ጠጠሮችን) አንድ በአንድ በመያዝ እግዚአብሔር እምነት፤ ተስፋና፤ ፍቅር እንዲሰጠን እንጠይቃለን፣ ከዚህ በኋላ ከእያንዳንዱ አሥር “ጸጋ የሞላሽ” በፊት “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ!” የሚለውን ጸሎት እናደርሳለን፣ አሥሩን “ጸጋ የሞላሽ” በምናደርስበት ጊዜ አሥሩን ድቡልቡሎች እንቆጥራለን፣ ከእያንዳንዱ አሥር “ጸጋ የሞላሽ” በኋላ “ለአብና ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይሁን” የሚለውን ጸሎት እናደርሳለን፡፡

08 April 2021, 10:47