ፈልግ

የዛምቢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ ሉንጉ፣ የዛምቢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ ሉንጉ፣ 

የዛምቢያ ወጣቶች በኅብረት ሆነው ሙስናን እንዲቃወሙት ጥሪ ቀረበ

በዛምቢያ ውስጥ መጋቢት 3/2013 ዓ. ም. የተከበረውን ብሔራዊ የወጣቶች ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት ያስተላለፉት፣ የዛምቢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ ሉንጉ፣ የአገሪቱ ማኅበራዊ ሥርዓት በሙስና እጅግ በመበላሸቱ ምክንያት ለወጣቶች ዘላቂነት ያለውን መልካም ሕይወት ለማዘጋጀት የተጀመረውን ጥረት መደናቀፉን ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የዛምቢያ ወጣቶች በኅብረት ሆነው ሙስናን እንዲቃወሙ በማለት፣ የዛምቢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን በመወከል ብጹዕ አቡነ ሉንጉ ጥሪያቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዛምቢያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባወጣው መግለጫ፣ በዛምቢያ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና ወጣቶች በኅብረት ሆነው እንዲዋጉት ጥሪውን አቅርቧል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን መልዕክት ለአገሪቱ ወጣቶች ያስተላለፉት በዛምቢያ የቺፓታ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ ሉንጉ ናቸው። በአገሪቱ ውስጥ የተስፋፋው ሙስና ለወጣቶች ጠቅላላ ዕድገት ተብለው የተወጠኑ ቋሚ የዕድገት እቅዶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ አክለውም፣ አገሪቱን ያስጨነቀው ሙስና የወጣቶችን ሕልም በመንጠቅ፣ እግዚአብሔር ለጋራ ጥቅም እንዲሆን የሰጣቸውን እምቅ ችሎታ በተግባር እንዳያውሉ ያግዳል ብለዋል። ስለዚህ የዛምቢያ ወጣቶች የትም ሆኑ የት፣ የፀረ-ሙስና ትግሉን እንዲቀላቀሉት በማለት ጥሪ ያደረጉላቸው ሲሆን ይህን ትግል በግል ማስኬድ ውጤታማ የማደርግ በመሆኑ የሁሉም አስተዋፅዖ ታክሎበት የጋራ እርምጃን መውሰድ ያስፈልጋል በማለት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ ሉንጉ አሳስበዋል።

ሙስና ወጣቱን ወደ ኋላ ይጎትታል

“ሙስና ወጣቱን ከዕድገት ወደ ኋላ ስለሚያስቀር ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” ያሉት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ ሉንጉ፣ ሙስና ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉንም ማኅበረሰብ ወደ ድህነት ሕይወት እንደሚመልስ ገልጸው፣ በሕይወት የመኖር ዕድልን እና ተስፋን በማጨለም ለድህነት የሚዳርግ መሆኑን አስረድተዋል። “ወጣቶች ፣ የተረጋጋ እና ዘላቂ የወደፊት ሕይወትን ይገንቡ” በሚለው የዘንድሮ ብሔራዊ የወጣቶች ቀን መሪ ቃል በመታገዝ፣ ወጣቶች ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ የወደፊት መልካም ሕይወት ዋስትናን ለመስጠት በኅብረት መቆም እንዳለባቸው በማለት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ ሉንጉ አሳስበዋል። ብጹዕ አቡነ ጆርጅ በመልዕክታቸው፣ ወጣቶች ለውጥን ዛሬ በማምጣት፣ የተሻለ ነገን ለማስገኘት የተዘጋጁ ጠንካራ ተዋናዮች መሆናቸውን ገልጸው፣ ጥረታቸውን እና ሕልማቸውን እውን ማድረግ እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያን ዘላቂ ድጋፏን በመስጠት ከጎናቸው መቆሟን ታረጋግጣለች ብለዋል።

የወጣትነት ጥንካሬ

የዚህ ዘመን ሰዎች በተለይም የድሆች ደስታ እና ተስፋ ፣ ህመም እና ጭንቀት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ደስታ እና ተስፋ ፣ ህመም እና ጭንቀት እንደሆኑ፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ “ደስታ እና ተስፋ” በሚለው ሐዋርያዊ ድንጋጌ እንደሚያብራራ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ዙማይሬ አስታውሰው፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ወጣቶች እምነታቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ፣ የወጣቶችን ጉጉት ፣ ውስጣዊ ስሜት እና ትዕግስታቸውንም ማወቅ እንደምትፈልግ ገልጸዋል። በመጨረሻም ወጣቶች በኢየሱስ ክርስቶስ በመማረክ እና በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ሩጫቸውን ወደፊት ለመቀጠል ይችላሉ ብለዋል።      

ብሔራዊ የወጣቶች ቀን አጀማመር በዛምቢያ

በዛምቢያ ውስጥ ብሔራዊ የወጣቶች ቀን በመንግሥት አስተባባሪነት የተጀመረው በ 1958 ዓ. ም. ሲሆን፣ ዓላማውም ሀገሪቱ በቅኝ ግዛት በነበረችበት ወቅት፣ መጋቢት 12/1954 ዓ. ም. የቅኝ ግዛት መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በበርካታ የአገሪቱ ወጣቶች ላይ በወሰደው የጥቃት እርምጃ የሞቱትን ወጣቶች ለማስታወስ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በዛምቢያ የሚከበረው ብሔራዊ የወጣቶች ቀን ዋና ዓላማ፣ ወጣቶች የሀገሪቱ የነገ መሪዎች እንደመሆናቸው፣  ወጣቶች በኅብረተሰቡ መካከል ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ለሀገር ልማት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ታውቋል። 

16 March 2021, 12:55