ፈልግ

የእስያ-አሜሪካዊያን የዘረኝነት ተቃውሞ ሰልፍ የእስያ-አሜሪካዊያን የዘረኝነት ተቃውሞ ሰልፍ 

የአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት በእስያ-አሜሪካውያን ላይ እያደገ የመጣውን አመፅ አወገዙ

በአሜሪካ የሚገኙ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በቅርቡ በአትላንታ ጆርጂያ በሚገኝ ሦስት የእስያ-አሜሪካዊያን ንግድ ማዕከል ላይ በተከፈተ ተኩስ ስምንት ሰዎች የተገደሉበትን እና አንድ ሰው የቆሰለበትን ጥቃት በጠንካራ ድምጽ አውግዘውታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመጋቢት ወር የተፈጸመውን ጥቃት ያካሄደው የ21 ዓመት ዕድሜ ነጭ አሜሪካዊ ሲሆን፣ ወጣቱ በታጠቀው መሣሪያ ስምንት ሰዎችን ገድሎ አንድ ሌላ ሰው ካቆሰለ በጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች እጅ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል። የእስያ ዝርያ ባላቸው ስምንት አሜሪካዊያን ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአገሩ ሕዝብ መካከል የመከራከሪያ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል። ወንጀሉን የፈጸመው ግለሰብ ከድርጊቱ በስተጀርባ የዘረኝነት ዓላማ የለም በማለት ክዷል።

የ ”ሶልት ሌክ” ከተማ ጳጳስ፣ የአሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር እና የእስያ እና ፓሲፊክ ደሴት ነዋሪዎች ጉዳይ ተጠሪ ንኡስ ኮሚቴ አባል የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኦስካር ሶሊስ በአገራቸው የሚታየውን የግድያ፣ የጥላቻ እና የአመጽ ባሕልን አውግዘው፣ አቅመ ደካማ ለሆኑት ወገኖች ድጋፍ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በአሜሪካ ሕዝቦች መካከል ዘርን፣ ጎሳን እና ጾታን ለይቶ የሚፈጸመውን የጥላቻ እና የአመጽ ተግባር የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ በጥብቅ የሚያወግዘው መሆኑን ብጹዕ አቡነ ኦስካር ገልጸዋል። በማከልም ይህ አሁን የተፈጸመው ጥቃት ብሔራዊ የመወያያ ርዕስ ሆኖ መቅረቡን አስታውሰው፣ በአሜሪካ የሚፈጸም ጸረ-እስያዊያ ጥቃት የተለያየ መልክ በመያዝ የአካል ጥቃት፣ የቃላት ሽኩቻ እና የንብረት መውደም ማስከተሉን አስታውሰው ላለፉት ዓመታት በእስያ-አሜሪካዊያን ማኅበረሰብ መካከል ስጋትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የአትላንታ ከተማ ሊቀ ጳጳስ፣ የብጹዕ አቡነ ግሬርጎሪ ሃርትሜየር ድምጽ በመደገፍ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ሰዎች እና አቅመ ደካሞች ጎን በመቆም አንድነትን መግለጽ እንደሚያስፈልግ አሳስበው “እያንዳንዱ ሰው በአፍቃሪ እግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንድም ወይም እህት ነው” በማለት በድጋሚ ተናግረዋል።

በተለይም በዚህ የአብይ ጾም ወቅት እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ያሳየንን ፍቅር እና ያደረገልንን ምህረት በማሰብ ልባችንን መለወጥ ያስፈልጋል ብለው፣ ይህን በማድረጋችን በእግዚአብሔር ፍቅር አንድ ሆነን ከጎረቤቶቻችን በሙሉ ጋር የእግዚአብሔርን ፍቅር መጋራት ይኖርብናል በማለት አሳስበዋል።

የእስያ እና ፓሲፊክ ዝርያ ባላቸው አሜሪካዊያን ላይ የዘር መድልዎ ተግባራት መፈጸማቸው በተሰማበት በግንቦት ወር 2020 የፈረንጆች ዓመት፣ ሦስት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ እርስ በእርስ በመተባበር ፣ በደግነት እና በፍቅር የታገዙ ተግባራትን በመፈጸም፣ ከገባንበት ቀውስ ለመውጣት እንደ አንድ የአሜሪካ ሕዝብ ወደ ኅብረት ጎዳና ላይ በመድረስ፣ የዘር ፣ የጎሳ ፣ የፆታ ወይም የሃይማኖታዊ ልዩነት ሳይለየን፣ በሁሉም ሰብዓዊ ሕይወት ውስጥ ዋጋን የሚሰጥ ሕዝብ ለመሆን ጠንከር ያለ ውሳኔ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በአሜሪካ ውስጥ የቻይና፣ የጃፓን፣ የሕንድ፣ የፊሊፒን፣ የቬትናም፣ የኮርያ እና ሌሎች የእስያ አገሮች ዝርያ ያላቸው እስያ-አሜሪካዊያን ቁጥር ከ20 ሚሊዮን በላይ መሆናቸው ሲነገር፣ እነዚህ በሙሉ አንድ ዓይነት መድልዎ ሲያጋጥማቸው መቆየቱ ታውቋል።

በ 19 ኛው ክፍለ ዘመን ቻይናውያንን የሚያግል ሕግ መጽደቁ፣ እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓኖችን እንደ ኋላ ቀር ዜጋ ከመመልከት አዝማሚያ ጋር ተዳምሮ፣ በቅርቡ የወጣው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በአሜሪካ ውስጥ የእስያ ዝርያ በሆኑ ሰዎች ላይ የዘር ትንኮሳ እና ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው የ COVID-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ካለፈው ዓመት ወዲህ መሆኑ ታውቋል።

24 March 2021, 14:26