በሶርያ ፣ የአሌፖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሕዝቡን የስቃይ ጩሄት አሰሙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ተስፋችን በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ የለም” በማለት፣ በስቃይ ላይ የሚገኘውን የሶርያ ሕዝብ ሕመም እና ድምጽ ያሰሙት በሶርያ የአሌፖ ማሮናዊያን ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ቶቢጂ፣ ሶርያ ከአሥር ዓመታት ጦርነት በኋላ በከፍተኛ ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ገልጸዋል። በጦርነቱ ምክንያት በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸዋን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች መፈናቀላቸውን ወይም መሰደዳቸውን፣ የሞት እና የጥፋት አደጋን በቤታቸው ሆነው ለመቀልበስ የሚሞክሩ ቤተሰቦች ሕይወትም በስቃይ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ቶቢጂ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሱ በማከልም ባሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የረሳቸው መሆኑን ተናግረው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያለፈው እሑድ እኩለ ቀን ላይ ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ የሚላው ዓለም ክርስቲያን ምዕመናን ለሶርያ ሰላም ጸሎትን እና ጾምን እንዲያድርግ ማሳሰባቸውን ካስታወሱ በኋላ፣ የዓለም ሕዝብ ሳይዘጋ ለሶርያ ሰላም የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ በማለት አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ለሶርያ ሰላም በማለት ያቀረቡት የጸሎት እና የጾም ጥሪ፣ ተረስተን ለቆየነው የሶርያ ሕዝብ ትልቅ እርካታ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ፣ በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለከፍተኛ ችግር በማጋለጡ ከሕዝቡ ቁጥር 83 ከመቶ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች መሆኑን አስታውሰዋል። በአገሪቱ የተጣለው ማዕቀብ እና በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት ይበልጥ የሚያጠቃው ምንም የማይመለከተውን ድሃ የሶርያ ሕዝብ መሆኑን ካስረዱ በኋላ፣ በመከራችን ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሶርያ ሕዝብ ጎን መሆን ደስታ እና መጽናኛ መሆናቸውን ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ገልጸዋል።
የሶርያን ቤተ ክርስቲያን ከባድ መከራ እና ስደት ደርሷታል ያሉት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ጦርነት እና አመጽ በሶርያ ውስጥ ሲጀመር ከነበረው የክርስቲያን ቁጥር አሁን ሩቡ ብቻ መቅረቱን ገልጸው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት እና ሞያዊ ብቃት ያላቸው ሰዎች መሰደዳቸውን ገልጸው አገር ውስጥ የቀሩት ድሆች እና አቅመ ደካሞች መሆናቸውን አስረድተዋል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ቤተ ክርስቲያንም ብትሆን ወደ ፊት መጓዝ እንደሚከብዳት እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷንም በሚገባ መከታተል የሚሳናት መሆኑን አስረድተዋል። ዘንድሮ ለቅዱስ ቁርባን ምስጢር የሚዘጋጁ ስምንት ሕጻናት ብቻ መገኘታቸውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ለምዕመናን የሚቀርቡ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በችግር መካከልም ቢሆን ሳይቋረጡ የሚቀርቡ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ሁሉ ችግር መካከል ጉዳት እና ውድመት የደረሰባቸው ቤተ ክርስቲያናት ጥገና እና መልሶ ግንባታ እየተደረገላቸው መሆኑን ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አስረድተዋል።