ፈልግ

የመጋቢት 12/2013 ዓ.ም ዘምኩራብ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 12/2013 ዓ.ም ዘምኩራብ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  

የመጋቢት 12/2013 ዓ.ም ዘምኩራብ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.     ቆላ 2፡16-23

2.     ያዕ 2፡ 14-26

3.     ሐ.ሥ. 10፡1-8

4.     ዮሐ 2፡13-25

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጠራ

ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጡ። የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምን ዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ። የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው።

ደቀ መዛሙርቱም፣ “ለቤትህ ያለኝ ቅናት ያቃጥለኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው። አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው።

አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ ታነሣዋለህ?” አሉት። ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር። ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ።

በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ታምራት አይተው በስሙ አመኑ፤ ኢየሱስ ግን ሰውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ አይታመንባቸውም ነበር፤ በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም።

      

የእለቱ ቅዱስ ወንጌርል አስተንትኖ

“የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላይ ወድቋልና” (መዝ 69፡9)።

በጌታችን ኢይሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘምኩራብ የሚለውን ሰንበት እናከብራለን።

በዚህ ዕለት በተለይም በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚአብሔር ቃል ሊያስተምረን የሕይወትን መንገድ ሊያመላክተን በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ወደ እያንዳንዳችን መጥቶ የልባችንን በር ያንኳኳል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆልስያስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የአይሁድ ሕግ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት ይለናል፤ የመጀመሪያው “ሞራላዊ ሕግ” ይህም ዐሥርቱ ትእዛዞችና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ግን ስለ መሥዋዕት ማቅረብ፣ ስለ መንጻት ሥርዓትና ስለ አይሁድ በዓሎች አከባበርን ያካተተው ሕግ ነው። ይህ ሕግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደንብና ሥነ ሥርዓቶችን ያካትታል ማር 7፡1-4 እና ኤፌ 2፡15

በቆላስያስ የነበሩ አንዳንድ አማኞች ለእነዚህ ደንቦችና ሥነ ሥርዓቶች እየተገዙ ነበር። ይህን ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህን ደንቦችና ሥነ ሥርዓቶች የማያከብሩ ክርስቲያኖችን እያወገዙ ነበር። እነዚህን ሥነ ሥርዓቶችና ደንቦችን በሚገባ  ካልጠበቀ አይድንም በማለት ያስተምሩ ነበር።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ስህተት የሚያስተምሩትን ሰዎች በፍጹም አትስሟቸው ይላል። ምክንያቱም ሰው የሚድነው በጸጋ አማካይነት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ባስተማረውና በኖረው ሕይወት ውስጥ በመሳተፍ ብቻ ነው ይለናል። ዮሐ 14፡6 “መንገዱ እኔ ነኝ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”  ይለናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በዛሬው መልእክቱ ስለ እምነትና ሥራ ይናገራል ይህም በቁ. 14 ላይ “ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ኝ ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን?” ብሎ በጥያቄ ይጀምራል።

አምናለሁ ማለት ቀላል ነገር ነው፤ ነገር ግን እንዲህ ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም ወይም ትርጉም አይሰጥም። ምክንያቱም እምነታችን እውነተኛ ስለመሆኑ እራሳችንን በየዕለቱ መጠየቅ ይኖርብናል። እምነታችን እውነተኛ ይሁን ወይም ሐሰተኛ፤ ጠንካራ ይሁን ደካማ በምን ልናውቅ እንችላለን? ይህ የሚታወቀው በሥራችን ነው። ይህም የፍቅር ሥራችን፣ የመታዘዝ ተግባራችን የእምነታችን ማረጋገጫ ነው። እምነታችንን የሚገልጽ ሥራ ከሌለን እንዲህ ያለው እምነት አያድነንም ወይም እርሱ ለሰጠን ክብር አያበቃንም።

ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በ ቁ.  15-16 ስለ ሐሰተኛ እምነት ሲናገር ይህ በቃላት ብቻ እንጂ በሥራ እንደማይገለጽ ፍቅር ነው ይለናል። ለተቸገሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደምንወዳቸው እየተናገርን በችግሮቻቸው የምንረዳቸው እና የማንደርስላቸው ከሆንን እምነታችን ሐሰተኛ እና ጥቅም የለሽ ነው። 1ዮሐ 3፡17-18 “ማንም ሀብት እያለው ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል? ልጆች ሆይ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።”  በማለት የያዕቆብን መልእክት ያጠናክርልናል። እንዲህ ዓይነቱ እምነት ማንንም አይጠቅምም፤ በተመሳሳይ መልኩ እምነታችን በሥራ ካልተገለጸ ዋጋ የለውም።

እውነተኛ እምነት ሁል ጊዜ በሥራ የሚገለጽ ነው፤ ሥራ ሁል ጊዜ ከእምነት ጋር የሚሄድ ነው፤ ያለሥራ የሚገለጽ እውነተኛ እምነት የለም ይህም እምነት ወደ ፍቅርና መልካም ሥራ ይመራናል።

መልካም ሥራ ሁል ጊዜ ከመታዘዝና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመውደድ ጋር የተገናኘ ነው ይህንንም በዮሐ 14፡15 ላይ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ።” በማለት ያሳስበናል። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ እኛ እንድናደርግ የሚፈልገው ነገር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ እንድንፈጽም ዘንድ ነው። ይህም ትእዛዝ በዮሐ 15፡12 እንደተገለጸው “ትእዛዜ ይህች ናት፣ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።” የሚል ነው። ስለዚህ እውነተኛ እምነት እራሱን የሚገልጸው በፍቅር ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሰው እራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሌላውንም ሰው ቢወድ እና መውደዱንም ቢያሳይ ይህ ሰው እውነተኛ እምነት እንዳለው ማሳያ ምልክት ነው።          

በዛሬው የወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ፋሲካ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ በቤተ መቅደስ መግባቱንና በዚያም ይገበያዩ የነበሩትን አይሁድ ባየ ጊዜ የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሰዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ማስወጣቱን የምናስብበት ሰንበት ነው።

በዚህ ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ባልሆነ ትርፍ ተግባር ተጠምደን እንዳንገኝ ያሳስበናል።በእግዚአብሔር ሥፍራ ሌላ ዓለማዊ ድርጊት እንዳይፈጸምበት ጌታችን በኃይለ ቃል ያስተምራል። ኢየሱስ በአይሁድ ቤተመቅደስ ገብቶ ያገኘው ነገር ከቤተመቅደሱ ዓላማ ጋር የሚጣጣም አልነበረም፤ የእግዚአብሔር መሆን የሚባው ነገር የሰው ሆኖ፣ የእግዚአብሔር ቤት ያለ ዓላማው ተይዞ ነበር፤ ስለዚህ ኢየሱስ የገመድ ጅራፍ አበጅቶ “ሰዎችን ሁሉ ከበጎችና ከበሬዎች ጋር ከቤተመቅደስ አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፣ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ…” (ዮሐ 2፡15) ።

ይህ ሁኔታ ዛሬ ቤተክርስትያን ያለችበት ሁኔታ እንድንፈትሽ መልእክት ያስተላልፋል የእግዚአብሔር ቤት እንደስሟ ተገቢ ማንነቷን ጠብቃ መቆየቷን እና የእግዚአብሔር ባልሆነው ትርፍ ተግባር አለመጠመዷን መመልከቱ ተገቢ ነው። በቤተክርስትያን በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት የተቀበልነውን ኃፊነት እና  አገልግሎታችን  የእግዚአብሔርን ክብር የሚያንጸባርቅ ስለመሆኑ ዘወር ብለው እንድንመለከት የዛሬው ወንጌል ጥሪ ያቀርባል። በየተሰማራንበት  የአገልግሎት  ዘርፍ የራሻችን የእውቀት ደረጃ፣ ዝና፣ ክብር ሁሉ የእግዚአብሔርን ክብር እና ሁሉን ቻይነት የሚጋርድ የትዕቢት ግድግዳ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንዳለብን ኢየሱስ ይናገራል።

በመጨረሻም በቤተመቅደስ ውስጥ ያለው ሁኔታ የእያንዳንዶቻችንን ሕይወት ይወክላል፤ ኢየሱስ ወደ እያንዳንዳችን ልብ ሲመጣ ልባችን የእግዚአብሔር ባልሆነው ትርፍ ነገር ተጠምዶ እንዳያገኘው የዛሬው ወንጌል ያሳስባል። ሁላችም በጌታ ኢየሱስ ክብር ደም የተገዛን የእግዚአብሔር አብ ውድ ልጆች እና የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደሶች እንደመሆናችን መጠን ልባችን ለእርሱ ጠብቀን ማቆየት ይገባናል። ኢየሱስ ማን መሆኑን ያላስተዋለው የቤተ መቅደሱ የገበያ ሁካታ በእያንዳንዳችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ለኢየሱስ ተገቢ ቦታ የማይሰጠውን ጥድፊያ እና ሁካታ ያመለክታል። ኢየሱስ በዚህ ወጀብ መካከል ተገኝቶ ማዕበሉን ጸጥ በማሰኘት ታንኳይቱን ያረጋጋት ዘንድ ለእርሱ እናስረክብ፤ እርሱ በሁሉ ነገር ተገቢውን ቦታ ይያዝ፤ ይህ ሆኖ ሲገኝ እግዚአብሔር በእኛ ይከብራል፤ ቤተመቅደሱም ቅድስናውን ጠብቆ የበረከት ምንጭ ይሆናል።

ቅዱስ ቃሉ እንደሚለን እምነታችን በሥራችን ተመስክሮ የቤትህ ቅንዓት አቃጠለኝ ብለን በዕለታዊ ሕይወታችን በመግለጽ የምንኖርበትን በእውነትና በእምነት የተቀበልነውን ክርስትናችንን በሕይወታችን የምንኖርበት እንዲሁም የምንመሰክርበትን ጸጋ ለሁላችንም ያብዛልን።

የእናታችን ቅድስት ድንግል ምርያም አማልጅነት ከሁላችንም ጋር ይሁን!

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

20 March 2021, 19:41