ፈልግ

እህት አን፣ የጸጥታ አስከባሪዎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጭካኔ ተግባር እንዳይፈጽሙ ተንበርክከው ሲለምኑ  እህት አን፣ የጸጥታ አስከባሪዎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጭካኔ ተግባር እንዳይፈጽሙ ተንበርክከው ሲለምኑ  

እህት አን፥ “ራስን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ የግድያ ወንጀል መፈጸም የለበትም” !

በሚያንማር ውስጥ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች፣ ራስን መከላከል በማይችሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚፈጽሙት የግድያ ተግባር እንዲቆም በማለት እህት አን ኑ ታዋንግ ተንበርክከው ለምነዋል። ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኩል ለተሰጣቸው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሚያንማር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መነኩሴ የሆኑት እህት አን በአገራቸው የጸጥታ አስከባሪዎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚወስዱትን የጭካኔ ተግባር እንዲያቆሙ በማለት መሬት ላይ ተንበርክከው ያቀረቡት ጥያቄ፣ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማትን ትኩረት ስቧል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም ለሚያንማር ሕዝብ በመራራት ላሳዩት ድጋፍ እህት አን ቅዱስነታቸውን አመስግነዋል። ከፍተኛ የሕዝብ ድምጽን በማግኘት አገርን እንዲመሩ የተመረጡት የቀድሞ ፕሬዚደንት አውንግ ሳን ሱ ኪ እንዲፈቱ እና በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲረጋገጥ በማለት ከጥር 1/2021 (እ.አ.አ) አንስቶ ሕዝባዊ ተቃውሞ እና አመጽ ሲካሄድ ቆይቷል። ይህን ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ርኅራሄ የለሽ ጥቃቶችን በማድረስ በርካቶችን ገድሏል።

“ቅዱስነታቸው ስላስታወሱን እናመሰግናለን”

ቅዱስነታቸው እ.አ.አ 2017 ወደ ሚያንማር ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት እህት አን፣ በሚያንማር ሕዝብ መካከል መገኘት በመፈለጋቸው “ፊደስ” በተባለ የቫቲካን ዜና አገልግሎት በኩል ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። እህት አን፣ በከባድ የታጠቀ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል የካቲት 21/2013 ዓ. ም ክሊኒካቸው ድረስ በመምጣት ሰልፈኞችን ለመበተን ተኩስ በከፈቱባቸው ወቅት በርካታ ወጣት ሰልፈኞች በክሊኒካቸው ውስጥ መሸሸጊያ መፈለጋቸውን ለቢቢሲ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። የጸጥታ አስከባሪ ኃይሉ ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽም መዘጋጀቱን ያወቁት እህት አን ወደ ጸጥታ አስከባሪዎች ቀርበው “ራስን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም” በማለት ተምበርክከው ጠይቀዋል።  

“እኔን ግደሉኝ”

ሰዎች ሲሰቃዩ እንደገና ማየት አልፈልግም ያሉት እህት አን፣ የጸጥታ አስከባሪዎች እንደሚያከብሯቸው እና ነገር ግን ሰልፈኞቹ ሥርዓት እንዲይዙ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተነግሯቸዋል። በከባድ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ የተነገራቸው እህት አን “ከፈለጋችሁ እኔን ግደሉኝ እንጂ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ላይ የሚገኝ እና ራሱን መከላከል የማይችል ሰልፈኛን በጦር መሣሪያ ማጥቃት ተገቢ አይደለም” በማለት ተናግረዋል። ይህ ጥያቄአቸው በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በመላው ዓለም ተሰራጭቶ የብዙዎችን ድጋፍ አግኝቷል።

ቅዱስነታቸው፡ “እኔም ተንበርክኬ እጠይቃለሁ”

እህት አን ተንበርክከው ያቀረቡት የ “አትንኳቸው”! ጥያቄ ልብን ከነካቸው ሰዎች መካከል የሚገኙት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችውን ባቀረቡበት ወቅት የመነኩሴዋን ጥያቄ ደግመው አቅርበዋል። ቅዱሰነታቸው መጋቢት 8/2013 ዓ. ም ሐዘናቸውን በመግለጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሚያንማር ሕዝብ ስቃይ እንዲያበቃ አስቸኳይ ድምጽ ማሰማት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት በተለይም የወጣቶችን ሕይወት ከሞት በማትረፍ ለአገሪቱ ተስፋን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን መልዕክት ሲያጠናክሩ “እኔም በማያንማር ጎዳና ላይ ተንበርክኬ እጆቼን በመዘርጋት ሁከት ቆሞ ውይይት እንዲደረግ እጠይቃለሁ!” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የእያንዳንዱ ክርስቲያን ተግባር

ከጸጥታ አስከባሪዎች በኩል ሰላማዊ ጥረት እንዲደረግ ተንበርክከው የተማጸኑት እህት አን፣ እያንዳንዱ የሕዝብ አመጽ እና ጥያቄ በሰላማዊ ውይይት ምላሽ እንዲያገኝ በማለት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጥሪ አስታውሰው፣ ተንበርክከው ያቀረቡት ጥያቄ የቅዱስነታቸውን ልብ እንደነካ ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ስሜት እና ተግባር እንዲሆን አሳስበዋል። “ከሕዝባችን ጎን ሆነን ስቃያቸውን እንካፈላለን” ያሉት እህት አን፣ በሚያንማር የሕዝብ ተቃውሞ ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመምጣቱ የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል። በግል የሚሰሩ አገልግሎት መስጫ ክሊኒኮች መዘጋታቸውን እህት አን አስታውሰው፣ ባሁኑ ጊዜ በአካባቢው የተጎዱትን ተቀብሎ መጠነኛ የሕክምና አገለግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የማኅበራቸው ክሊኒክ ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሳቸው ሰልፈኞች መካከል በቂ ሕክምናን ካለማግኘት የተነሳ ሰዎች እየሞቱ መሆኑን እህት አን አስረድተዋል።

የተስፋ ምልክት

በደረሰብን ከባድ ችግር ውስጥ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመጽናኛ መልዕክት፣ የተስፋ ምልክት መመልከታቸውን የገለጹት እህት አን፣ መጠነኛ የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸው ሁለት እናቶች ወደ ክሊኒካቸው ደርሰው የማዋለድ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። የቆሰለን የማከም ተልዕኮአቸውን እንደማያቋርጡ የገለጹት እህት አን፣ ዓላማቸው የተጎዱትን ማፅናናት እና ሕይወትን ከሞት ማዳን መሆኑን ተናግረዋል።   

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አርዓያነት

የሰላም ተማጽኖን ማቅረብ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንግዳ ነግር ባይሆንም እ. አ. አ ሚያዝያ 11/2019 ዓ. ም ወደ ቫቲካን የተጋበዙት የደቡብ ሱዳን የጦር መሪዎች፣ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳይመለሱ በመማጸን እግሮቻቸው ሥር ወድቀው መለመናቸው የሚታወስ ነው። 

20 March 2021, 17:27