ፈልግ

የመጋቢት 19/2013 ዓ.ም ዘመፃጉዕ ዕለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 19/2013 ዓ.ም ዘመፃጉዕ ዕለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የመጋቢት 19/2013 ዓ.ም ዘመፃጉዕ ዕለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ገላ 5፡14-20

2.   ሐ.ሥ 3፡1-11

3.   ዮሐ 5፡ 1-18

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በቤተ ሳይዳ የተደረገው ፈውስ

ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች። በእነዚህም መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። [የውሃውንም መንቀሳቀስ እየተጠባበቁ፣ ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር። በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር። ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው።

ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው። ኢየሱስም፣ “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም ተሸክሞ ሄደ። ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር። አይሁድም የተፈወሰውን ሰው፣ “ሰንበት ስለ ሆነ መተኛህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት።

እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደፈወ ሰው አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው። 15ሰውየውም የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው።

ወልድ ሕይወትን ይሰጣል

አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር። ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው። እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።

የእለቱ አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዘወትር የሚወደንና በቃሉ አማካይነት ለሕይወታችንም የሚጠቅመውን እና የሚያሻግረንን ምክር የሚሰጠን እግዚአብሔር አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የዐብይ ጾም አራተኛ ሳምንት ዘመፃጉዕ ተብሎ የሚጠራውን ሰንበት እናከብራለን።

በዚህ ዕለተ ሰንበት በተለይም በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚአብሔር ቃል ሊያስተምረን የሕይወትን መንገድ ሊያመላክተን በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ወደ እያንዳንዳችን ልብ በር ያንኳኳል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው መልእክቱ ስለ ነፃ መውጣት ይናገራል “ክርስቶስ ነፃ ያወጣን በነፃነት እንድንኖር ነው” የሰው ልጅ በተለየ መልኩ ነፃ መሆን ይፈልጋል፤ ነገር ግን የፍፁም ነፃነት ምንጭ ጌታችን እይሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በዮሐ 8፡35 ላይ ፍፁም ወደሆነው ሕይወት እና ነፃነት የሚመራ እርሱ እራሱ እንደሆነ ይናገራል።

እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ለሕግ መታዘዝ ወይንም የኦሪትን ሕግ መፈጸም በእግዚአብሔር ዘንድ የኃጢአት ስርየት የሚያስገኝ በመሆኑ ምክንያት የመገረዝ ሥርዓትም የኃጢአትን ሥርእየት ለማግኘት ብለው የሚያከናውኑት ሥርዓት መሆኑን ያሳያል። ነገር ግን ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከፀጋው እርቃችኋል ከመለኮታዊው ፍቅር ውጭ ሆናችኋል ይላል።

በዚህ መልእክት ውስጥ ሕግን መጠበቅ እና በፀጋው ምሕረት ማግኘት በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የተመሰረተ ሕያው እምነት እንጂ ጊዜያዊ በሆነ በሚታይ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ አይደለም።

በመጀመሪያው የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 1፡3 ላይ “ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨውን ድካማችሁንና በጌታችን በእየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን” በማለት ይህንን ሃሳብ ያጠናክርልናል።

እንዲሁም በ 2ኛ ጢሞ 2፡5 ላይ የተቀበልነው የክርስትና ሕይወት ዘወትር የምንተጋበት በውድድሩም አሸናፊዎች የሚያደርገን ትጋት የምናሳይበት የሕይወት ክፍል እንደሆነ እንዲህ በማለት ይናገራል። “እንደዚሁም በውድድር የሚሳተፍ ሰው፣ የውድድሩን ሕግ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም።”

የክርስትና ሕይወታችን ትርጉም ሁል ጊዜ ከጸጋው ሙላት በቃሉና በምስጢራቱ አማካይነት እየተካፈልን በትጋት የምንኖረውና ማግኘት ያለብንን ጸጋ ወይም የእግዚአብሔር ስጦታ ለመቀበል በእምነት መትጋት እንዳለብን የሚያሳይ ነው።  በፀጋው ነፃ ብንወጣም በጽናት እና በእምነት እስከፍፃሜው መትጋት ያስፈልገናል ስለዚህም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለት ነገር ላይ ላይ እንድናተኩር ይጋብዘናል፤ ነፃነታችን በእግዚአብሔርና እርስበርሳችን በፍቅር የምናገለግልበትን እንዲሆን።

ነገር ግን ሕግን በመጠበቅ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ክብርን ለማግኘት መድከም እንደሌለብን ይህ ደግሞ ተመፃዳቂነት እና ሌላውን የመቃወም መንፈስ እንዲያድርብን ያደርጋል።

ይህም በመሆኑም  በእምነት የምናደርገው ጸሎት ከእግዚአብሔር ምላሽ እንዳለው እና የበለጠ በእርሱ የምንታመን  እንድንሆን ያደርገናል።

በተለየ ሁኔታ በዚህ ዓብይ ጾም ወቅት ወደ እግዚአብሔር እውነት መቅረብ፣ እራሳችንን በምስጢረ ንሰሃ በማደስ እና በማዘጋጀት የእግዚአብሔር ቅርብ ልጆች እንድናደርግ እንጋበዛለን።  

በሐዋርያት ሥራ በዛሬው መልእክት የነ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ አገልግሎት በፈተና የተሞላ ቢሆንም ግን አገልግሎታቸውን በፅናት እና ከእርሱ በተቀበሉት የጸጋ ስጦታ የክርስቶስን ሥራ መቀጠላቸውን ያሳየናል እንዲሁም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥም የሚሠራ ኃይል ያለው መሆኑን እና በስሙ የመዳን ተግባር እንደፈፀሙ እናያለን።                                                            

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ   “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረደዋል፤ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፤ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም፤ እኔስ አቤቱ ማረኝ አልሁ” (መዝ 41፡ 2-4)

የዛሬው ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሽተኞችን የፈወሰበትን እና ወደ ሕሙማን ቀርቦ ከእነርሱ ጋር የተወያየበትን የፈውስ ተግባር የምናስብበት ክፍል ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሳ ስምንት ዓመት በሕመም ይሰቃይ ወደነበረው ሰው ቀርቦ ጠየቀው። በዚያ ሁሉ ዓመታት ይህንን ሰው ወደ ፈውስ ውኃ የሚያስገባው ዘመድ ወይም ወገን አልነበረውም፤ አሁን ግን የፈውስ ባለቤት የሆነው አምላክ መጥቶ ‹‹መዳንን ትወዳለህን? ብሎ ይጠይቀዋል። ሰውየው ወደ ውኃው የሚያስገባው አለመኖሩን ይናገራል። የእርሱ ፈውስ በውኃው ዘንድ ብቻ መሆኑን አምኗል። ኢየሱስ ግን  “አልጋህን ተሸክመህ ሒድ” አለው። ሰላሳ ስምንት ዓመት በሕማም ሲሰቃይ የነበረው ሰው በቤተ መቅደስ ከወንድሞቹ ጋር ለመቆም በቃ። አልጋውን ተሸክሞ ኢየሱስ እንዳዳነው እየመሰከረ ሔደ።

ይህ ሰንበት ዘመፃጉዕ ተብሎ ሲጠራ ሁላችንም ወደ ውስጣችን ቁስል በጥልቀት ተመልክተን ኢየሱስን እንድንጠራው ያሳስበናል። ሥጋዊና መንፈሳዊ ቁስሎቻችንን ለእርሱ በማቅረብ እንድንፈወስ “እናንተ ሸክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ 11፡28) ያለውን ጌታ በማመን ወደ እርሱ እንጩህ።

እያንዳንዳችን ለማንም የማናካፍለው ቁስል፤ እንዲህ ሆንኩ ብለን ለመናገር የማያስደፍረን ሕማም ፤ማንነት፤ በሱስ እሥራት ባርያ የሆንበት ነገር፤ ከሰው ተደብቀን የምንገዛለት እሥራት ወ.ዘ.ተ ይኖረናል። ኢየሱስ ይህንን አይጠየፍም፤ ታሪካችንን ሰምቶ ከጀርባችን አያወራም፤ ነገር ግን የእርሱ አመለካከት የተለየ ነው። ያ በውኃ አጠገብ ተኝቶ የነበረውን ታማሚ ባየው ጊዜ “ኢየሱስ እስከ አሁን ለብዙ ዘመን እንዲህ እንደነበረ ዐውቆ ልትድን ትወዳለህን” (ዮሐ 5፡6) አለው።

ለእያንዳንዳችን ሕመም፤ ቁስል፤ ባርነት፤ እሥራት ወ.ዘ.ተ የኢየሱስን ጥያቄ ይህ ነው “ልትድን ትወዳለህን?” “ልትድኚ ትወጃለሽን?”  የእኛ ፋንታ እሺ ብሎ መዳን ነው። እሺ ብሎ መዳን! ስለዚህ ወደ ኢየሱስ ቀርበን ከእርሱ ዘንድ ለመፈወስ ጊዜው አሁን ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በበለጠ እንዲህ እያለ ያበረታታናል “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፤ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው” (2ኛ ቆሮ 6፡2) የመፃጉዕ ሰንበት እንግዲህ በሥጋዊ ዐይን ስለምናያቸው ሕሙማን የምናስብበት እኛን የማያጠቃልል በዓል ሳይሆን የራሳችንን ሥጋዊና መንፈሳዊ ቁስሎች እንዲሁም ሕማም ይዘን በኢየሱስ ፊት በትህትና በመቆም ፈውስ የምንለምንበት ጊዜ ነው።

ይህንን ለማድረግ የእናታችን ቅድስት ድንግል ምርያም አማልጅነት ከሁላችንም ጋር ይሁን!

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

    

 

27 March 2021, 19:26