ፈልግ

ሠራተኞች በሥራ መስክ ሠራተኞች በሥራ መስክ 

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በሥራው ዓለም አዲስ ሥርዓት እንዲዋቀር አሳሰበ

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እ. አ. አ ግንቦት 1/2021 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወዝአደሮች ቀንን በማስመልከት ባስተላለፍው መልዕክት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሕገ-ወጥ ስደተኞች ላይ የጉልበት ብዝበዛ እንዲስፋፋ ማድረጉን ገልጾ፣ በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ ብዙ የሥራ መስኮች በሕገ-ወጥ ስደተኞች ላይ ለሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛ ተቀባይነት ሊሰጠው አይገባም በማለት አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት እንዳስታወቁት በአገራቸው በተስፋፋው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ውስንነት በግልጽ እንዲታይ አድርጓል ብለዋል። አክለውም ወረርሽኙ በሥራው ዓለም የነበረውን የክፍያ አለ መመጣጠንን ከማባባሱም በላይ ተጨማሪ ድህነትን አስከትሏል ብለዋል። የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ በመጽሐፈ ነህምያ ምዕ. ሦስት ላይ “ሕዝቡም ስለ ሥራው ግድ ይለዋል” በሚለው በዘንድሮ መሪ ቃሉ እ. አ. አ ግንቦት 1/2021 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወዝ አደሮች ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፈው መልዕክቱ፣ የሰውን ልጅ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሕይወት ያገናዘበ አዲስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጾ፣ ይህ ሥርዓት በሲቪል ማህበረሰብ እና ሕዝባዊ ድርጅቶች ተነሳሽነት ጥንካሬን በማግኘት፣ ዛሬን በመሰሉ አስቸጋሪ ጊዜያት ልዩነትን በማስወገድ ማኅበራዊ አንድነትን የሚያመጣ መሆን አለበት ብሏል።       

እንደገና ለመጀመር ያለው ፍላጎት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን በማባባስ የሥራ-አጥ ችግርን የጎላ አድርጎታል ያሉት የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በተለይም መደበኛ ባልሆኑት ሠራተኞች ላይ የጉልበት ብዝበዛ እንዲፈጸም ማድረጉን እና በወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ከሥራ የመባረር ዕድል ሲያጋጥም ችግሩ እጅግ የከፋ እንደሚሆን አስረድተዋል። እ. አ. አ. በ2020 ዓ. ም. በጋ ወራት ላይ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በማደጋቸው ተስፋ ሰጭ ምልኮቶች መታየታቸውን የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ ወረርሽኙ ሲቀንስ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው እንደገና በመጨመር ያጋጠሙትን ከባድ ችግሮች ለማቃለል እና  ህብረተሰቡ ከደረሰበት ቀውስ የሚያገግምበት ተስፋ እንደሚኖር ገልጸው፣ ሆኖም ግን የማኅበራዊ ደህንነት ተቋማቱ የዕርዳታ መረቦቻችውን ማጠናከር በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ አክለውም ከወረርሽኙ በኋላም ቢሆን የሥራ ዓለምን መለወጥ እና ወደ አስተማማኝ ደረጃ የመመለስ መንገዶችን መፈለግ፣ ሰዎች እንዲሰደዱ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የሆነው ጦርነት ተወግዶ የጦር መሣሪያ ምርትም እንዲቆም ያስፈልጋል ብለዋል። ጳጳሳቱ አክለውም ሥነ-ምህዳራዊ ሽግግር በማድረግ ለሰው ልጅ ክብር ቅድሚያን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሁሉም ለጋራ ጥቅም ይሁን

“በዓለማችን የገባው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሰው ልጅ ምን ያህል እርስ በእርስ የተገናኘ እና የሚደጋገፍ መሆኑን ለማውቅ አስችሎናል” ያሉት የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳቱ “እኛ ሁላችን ለጋራ ጥቅም በርትተን እንድንሰራ ተጠርተናል” ብለው ዕጣ ፈንታችንም ከሰው ልጅ መዳን ጋር የተገናኘ መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ባለፈው የጎርግሮሳዊያኑ ግንቦት 31/2020 ዓ. ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ያስተላለፉትን ሐዋርያዊ አስተምህሮ ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ ቅዱስነታቸው በመልዕታቸው “ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስከተለብን ቀውስ የከፋው እራሳችንን በእራሳችን መዝጋት ነው” ማለታቸውን ገልጸው፣ ይህ የፈተና ወቅት ችግርን እና መከራን ተቋቁሞ ለማለፍ የሚያስችል አቅምን ለማግኘት ብርታት የሚገኝበት ውድ ጊዜ መሆኑን እና ማኅበራዊ ቀውሱም በኤኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ አዳዲስ መንገዶችን ለመፈለግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

“በአገራት መካከል ባለው አንድነት፣ በአውሮፓ አገሮች መካከል የበለጠ ውህደት መኖሩን እያየን እንገኛለን” ያለው የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ መልእክት፣ የህዝብ አገልግሎት ዘርፍ ለትምሕርት እና ለጤና አጠባበቅ የበለጠ ትኩረት በመስጠት የጋራ ፋይናንስ ስልቶችን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቦ፣ የሥራ ቅኝቶች ዘላቂነት ፣ የሙያ እና የኢኮኖሚ ሕይወትን ከግል እና ከቤተሰብ ሕይወት ጋር በማዛመድ በአፈፃፀም ላይ በብቸኛ መርህ ላይ የተመሠረተ የውድድር ሥነ-ልቦና በመከተል መንፈሳዊ ሕይወትን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።  

የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” መርህ አቅጣጫ

የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በተጨማሪም ብዙዎች በርቀት እንዲያከናውኑት የተደረገው የሥራ አፈጻጸም ፣ የሥራ ጊዜን እና በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን መተሳሰብ ለማስታረቅ ዕድል የሰጠ መሆኑን አስረድተው፣ ቀደም ሲል ያልታወቁ ፣ በራሳቸው ጊዜ ብቻ ሥራ ፈጣሪ የመሆን ዕድል ያላቸው ፣ በሥራ ፍላጎቶች ፣ በስልጠና ፣ በማኅበራዊ ግንኙነቶች እና በመንፈሳዊ ሕይወት መካከል በሚስማማ መንገድ ለመገናኘት የበለጠ ዕድል መገኘቱን ገልጸዋል።

በርቀት ወይም በቤት ውስጥ በሚከናወኑ የሥራ ዘርፎች፣ ፊት ለፊት የሚደረጉ ግንኙነቶች እጅግ በማሳደግ በብዙ ሁኔታዎች ውስጥ የሥራ ታታሪነትን በመጠበቅ ወይም በመጨመር ወደ ሥራ አካባቢዎች ለመድረስ የሚወስደውን የጉዞ ጊዜን ለመቆጠብ ያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም ለጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ እና ለሥራው ዓለም አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት ጠቋሚ መንገዶች መኖራቸውን አስታውቀው የመጀመሪያው፥ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑን ገልጸው “ከዚህ ቃለ ምዕዳን የምንረዳው ወንድማማችነት በሥራ መስክም ቢሆን እንደ ብርሃን በማብራት የአንድነትን እና የመጋራት ልምዶችን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸው፣ ወንድማማችነት በችግር ጊዜ ከሁሉም ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ፣ በተለይም ከማኅበረሰቡ ተገልለው ለአደጋ የተጋለጡትን ሰዎች ወደ ህብረት ጎዳና የሚመልስ መሆኑን አስረድተዋል።  

ሁለተኛው፥ በጣሊያን ውስጥ ታራንቶ ከተማ እ. አ. አ. ከጥቅምት 21-24/2021 ዓ. ም. በአከባቢ ጥበቃ እና በሥራው ዓለም መካከል ያለውን የግንኙነት ጭብጥ ለማስገንዘብ የተዘጋጀው ማህበራዊ ሳምንት፣ የሰውን ልጅ ጊዜያዊ በላይነት ከሚንጸባረቅበት የምርት ማዕከላዊነት ከምንም ሊስተካከል ወደማይችለው የመጭው ትውልድ አስፈላጊነት መሆኑ ታውቋል። ዘንድሮ የተከበረው የሠራተኛው የቅዱስ ዮሴፍ በዓል፣ በሀገረ ስብከቶች ውስጥ “ይህንን አስቸጋሪ የሕይወት ምዕራፍ ሳይዘነጉ ለመኖር የሚያግዝ መሆን አለበት” ያሉት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ በሀገረ ስብከቶች ጥንካሬ በኩል በብዙ ቤተሰቦች እና ሰዎች ላይ የሚታዩ ቁስሎችን መፈወስ ይቻላል ብለው፣ ነገር ግን የሕዝቡን ጭንቀት በመጋራት የኢጣሊያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አዳዲስ የሥራ ፈጠራን እና የእንክብካቤ ዓይነቶችን ብምትችለው ሁሉ ለመደገፍ ኃላፊነት መውሰድ የምትፈልግ መሆኗን ብጹዓን ጳጳሳቱ ገልጸዋል።

31 March 2021, 15:42