ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2013 ዓ.ም. የዐቢይ ጾምን በማስመልከት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2013 ዓ.ም. የዐቢይ ጾምን በማስመልከት  

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2013 ዓ.ም. የዐቢይ ጾምን በማስመልከት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ” (ማቴ 6፡15)፡፡

 

ብፁዓን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያንና/ውያት

ክቡራን ምዕመናን

በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ

ክቡራንና ክቡራት

እንኳን ለ2013 ዓ. ም. ዐቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የተቀደሰ የተባረከ የጾም፣ የጸሎትና መልካም ተግባራትን የምንፈጽምበት ልዩ የመታደስ ዘመን ያድርግልን፡፡

የዐቢይ ጾም ወራት በራሳችን እና በሌሎች ላይ ባደረስነው በደል ተጸጽተንና  ንስሐ ገብተን ለእግዚአብሔር አባታችን ታማኝ ልንሆን ቃል የምንገባበት  ወቅት ነው፡፡ የዐቢይ ጾም ወራት ነፍስን ከሚያሳድፍ ከሥጋዊ ተድላና ደስታ ርቀን በንስሐ እግዚአብሔርን የምንማጸንበት የሚፈለግብንን መንፈሳዊ አገልግሎት በትሕትና፣ በታማኝነትና በንቃት በመፈጸም ቅዱሳት ምሥጢራትን በትጋት ለመሳተፍ ጥረት  እንድናደርግበት የተሰጠን ዕድል ነው፡፡

የሰው ልጅ በሕይወት እስካለ ድረስ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ሊፈጽማቸው ከሚገባቸው መንፈሳዊ በጐ ተግባራት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ጾም፣ ጸሎትና ምጽዋት ናቸው፡፡ መሠረታዊ ምንጩ ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ነው፡፡ ቅድስት  ቤተክርስቲያናችንም በትዕዛዛቶቿ “ቤተክርስቲያን የምታዝዘውን ጾም ጹሙ” በማለት ማስተማርዋን ትቀጥላለች፡፡

 

በደኀንነት ታሪካችን  “የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፤ የነነዌ ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ፤ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፤ አዋጅም አስነገረ፣ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፣ እንዲህም አለ ሰዎችና እንስሶች፣ ላሞችና በጐች አንዳች አይቅመሱ፣ አይሰማሩም፣ ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፡፡ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፣ ምንአልባት እግዚአብሔር ራርቶልን ቁጣውን ይመልስ ይሆናል እኛም ከጥፋት እንድናለን፤ እግዚአብሔር ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን ተመለከተ፡፡ ስለዚህም ራርቶላቸው በእነርሱ ላይ ሊያመጣ የነበረውን መዓት መለሰ”፡፡ (ትን. ዮና 3፡5-10) ይለናል፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን እግዚአብሔርን የሚፈልግ ትሑት ልብ ይኖረን ዘንድ እንለምነው ጾማችን ውጪያዊ ሆኖ በመልካም ተግባር ያልታጀበ ሕይወትን የማያንጽ ለታይታ ብቻ እንዳይሆን መጠንቀቅና ይልቁንም መልካም የሆነውን ነገር ለሰዎች በማድረግና ፍትሕን በመፈጸም በማስተዋል ሕይወታችንን መምራት ይኖርብናል፡፡

በሌላም ሥፍራ ነብዮ ኢዩኤል (2፡12-13) እንዲህ ሲል ምክሩን ይሰጠናል “እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በለቅሶና በዋይታ ወደእኔ ተመለሱ” ይላል፡፡ “ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ቁጣውም የዘገየ፣ ምሕረቱም የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና”” በማለት ከልባችን እንድንጾም፣ ንስሐ እንድንገባ እንድንጸጸት ከልባችንም ባልንጀሮቻችንን እንደዚሁም ጐረቤቶቻችንን ይቅር እንድንል ያስተምረናል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾምና ጸሎት ሊያስተምረን ስለፈለገም “ወደ ተራራ ወጣ ሌሊቱንም ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ (ሉቃ 6፡12)፡፡ ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ፤ ወደ ምድረ በዳም ሄደ፣ እንደምትሰማኝ አወቅሁ (ማር 1፡35) “አባት ሆይ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ” (ዮሐ 11፡41-42) ያለውን እናስተውል፡፡ አንድ መልካም የሆነ አማኝም በሚጸልይበት ጊዜ ላደረገው ጸሎት መልስ እንደሚያገኝ ከዚሁ ከቅዱስ ቃሉ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በሌላም ቦታ የክፋትን ሠራዊት ለማሸነፍ ጾምና ጸሎት ለነፍሳችን እጅግ ጠቃሚዎች መሆናቸውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምረን  “እንዲህ ዓይነት ጋኔል በጸሎትና በጾም ካልሆነ በቀር አይወጣም” አላቸው (ማቴ 17፡21) የተባለውን  እናስተውል፡፡ በዋናነት በምንጾምበትና በምንጸልይበት ጊዜ ማስወገድ ያለብንን ነገሮች ሳናስወግድ መጾም ተገቢ አይሆንም፡፡ በጾም ወቅት ከሃሜት፣ ከቂም በቀል ፈጽሞ መራቅን መለማመድ ያስፈልጋል። በዚህ ፋንታ ፍቅር እና ይቅርታ ሕይወታችንን እንዲገዙ መጣር አለብን፡፡ ያኔ የሰላም መልእክተኛ በመሆን ሰላማዊውን ኢየሱስን መስበክ  እንችላለን፡፡

ውድ ምእመናን በጾማችን ወቅት የመንፈስ ቅዱስን ኃይልና ጸጋ በመለመን ታላቁ ሊቀ ካህናችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንን፡-

የታመሙትን በመጐብኘት፤

የታረዙትን በማልበስ፤

የተራቡትን በማብላት፤

የተጠሙትን በማጠጣት፤

ያዘኑትን በማጽናናት፤

የተጣሉትን በማስታረቅ፤

የታሰሩትን በመጠየቅና ምግባረ ሠናይ ተግባራትን በመፈጸም ጾማችን አጥብቀን እንያዝ፡፡

        

ውድ ካቶሊካውያን ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁላችሁ በተለይ አሁኑ ባለንበት ሁኔታ ስለሀገራችን ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንድንጸልይ እንድንጾም በትሕትና እጠይቃችኋለሁ፡፡ በተለይም በዚህ ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በጦርነት፣ በተለያዩ የእርስ በእርስ ግጭቶች፤ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙትን ውድ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ወደየቀያቸው ተመልሰው የተለመደውን የተረጋጋ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ልዩ ጸሎት፣ ተጋድሎና በሚቻንለው መጠን ሁሉ የጾማችን ፍሬ የሆንውን በጎ የፍቅር ሥራ ሁሉ እንድናከናውን መለውን ምዕመናን ሁሉ አደራ እላለሁ። የእያንዳንዳችን ጸሎት ፍሬ አፍርታ ውጤት እንደምታስገኝ ትልቅ እምነት አለኝ፡፡ ያለ ጸሎት ፀጋ ያለፀጋም ድኅነት አይገኝምና  ወደየራሳችን ማንነት ተመልሰን ለጸሎት እንምበርከክ፡ ይህንን ጊዜ ማለፍ የምንችለው በጸሎት እና በእግዚአብሔር በመተማመን ብቻ ነው፡፡

በመጨረሻ እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ፍቅሩ ለመላው ሕዝባችን ሰላሙን ፍቅሩን አንድነቱን ያውርድልን፡፡ በዘመናችን የተከሰተውን ዓለማችንን ያስጨነቀውን የኮቪድ 19 ወረርሽን  ያስወግድልን፡፡ በተለያዩ ሕመሞች የተያዙትን ሁሉ ፈውስ ይስጥልን፣  የሞቱትን ነፍሳት ይማርልን፡፡ ላዘኑ ሁሉ መጽናናትን ይስጥልን፤ እኛንም  በምሕረቱ ይጐብኘን፣ የትንሣኤው ተካፋዮችም አንድንሆን በጸጋው ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

… ካርዲናል ብርሃነየሱስ

   ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

   የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት

06 March 2021, 10:35