ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እ.አ.አ 2018 ዓ. ም. ታማሚ ሕጻናትን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ እ.አ.አ 2018 ዓ. ም. ታማሚ ሕጻናትን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ 

ሃያኛው ዓለም አቀፍ የጸረ ካንሰር ቀን ተከብሮ ዋለ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የካቲት 8/2013 ዓ. ም. የተከበረውን 20ኛ ዓለም አቀፍ የልጆች ጸረ ካንሰር ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሕመሙ የተጠቁ ልጆችን እና ሕመሙን ለመቀነስ የሕክምና አገልግሎትን በመስጠት ላይ የሚገኙትን በሙሉ የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል። በጣሊያን ብቻ የካንሰር ሕመም ዕድሜአቸው እስከ 15 ዓመት የሚሆናቸውን አዳጊ ሕጻናትን እና 19 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ወጣቶች፣ በድምሩ 2300 ልጆችን በየዓመቱ የሚያጠቃቸው መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አዳጊ ልጆችን በማጥቃት ላይ የሚገኘው የካንሰር በሽታን ለመቋቋም የሚሰጡ ዘመናዊ የሕክምና ዓይነቶች መልካም ውጤቶችን በማስገኘት ላይ መሆናቸው ታውቋል። ውጤታማ ናቸው የተባሉት ዘመናዊ የሕክምና ዓይነቶች 85 ከመቶ ለሚሆኑት ልጆች ፈውስን የሚያስገኝ መሆኑ ታውቋል። የሕጻናትን እና የታዳጊ ልጆች ዕድሜን በመለየት እንዲሁም ስለ በሽታው ትክክለኛ መረጃን በመስጠት ልዩ ትኩረት ከተደረገበት ከበሽታው መዳን የሚቻል መሆኑን በ“ባምቢኖ ጄሱ” የሕጻናት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ፍራንቸስካ ደል ቡፋሎ አስታውቀዋል። ዶ/ር ፍራንቸስካ በማብራሪያቸው ሕጻናትን የሚያጠቃው የካንሰር ዓይነት የደም ሕዋስን የሚያጠቃ የካንሰር ዓይነት መሆኑን አስረድተው፣ ብዙን ጊዜ ሕጻናትን የሚያጠቃው የካንሰር ዓይነት ዋናውን የነርቭ ስርዓቶችን የሚያቃውስ የጭንቅላት ካንሰር መሆኑን አስረድተዋል። በጣሊያ ውስጥ በሕጻንነት የዕድሜ ክልል በሚገኙት ልጆች ላይ በተደረጉት ምርመራዎች ዕድሜአቸው እስከ 15 ዓመት የሚሆናቸው በቁጥር 1500 ልጆች እና ዕድሜአቸው 19 ዓመት የሚሆናቸው 800 አዳጊ ወጣቶች፣ የካንሰር ሕመም ተጠቂዎች መሆናቸውን ዶ/ር ፍራንቸስካ አስታውቀዋል።

ከረጅም ጊዜ ፈውስ አንፃር

ከካንሰር ሕመም የሚፈወሱ የሕጻናት ቁጥር ተስፋን የሚሰጥ እና አበራታች መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፍራንቸስካ፣ ባአሁኑ ጊዜ የምርምር ውጤቶች እንደሚያመለክቱት በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ሰዎች መካከል 70 ከመቶ ከሕመሙ መፈወስ መቻላቸውን አስታውቀዋል። ለግለ ሰቦች የሚሰጥ የካንሰር ሕክምና አገልግሎትን የተመለከት እንደሆነ ውጤቱ እጅግ አመርቂ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ፍራንቸስካ፣ በዓለማችን እየተሰጠ ያለው የካንሰር ሕክምና የሕሙማንን ዕድሜ በአምስት ዓመት የጨመረ መሆኑን እና ከበሽታው የሚፈወሱት ሰዎች ቁጥርም ወደ 85 ከመቶ መድረሱ አስረድተዋል።

ለካንሰር ሕመም ፈውስ ውጤታማ የሆኑ የሕክምና ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?

የካንሰር ሕመምን ለማከም አስፈላጊ የሆኑ ሦስት የሕክምና ዓይነቶች መኖራቸውን የገለጹት የሕጻናት ሐኪም ዶ/ር ፍራንቸስካ ደል ቡፋሎ፣ የካንሰር ሕመምን ለማከም እንደ ፍቱን መድኃኒት በመሆን በቅድሚያ የሚጠቀስ ኬሞቲራፒ የተባለ የሕክምና ዓይነት መኖሩን አስረድተው፣ የደም ውስጥ ካንሰርን ለማከም የሚያገለግል ራዲዮቴራፒ የተባለ የሕክምና ዓይነት እና ሦስተኛው እና በብዛት የተለመደው የካንሰር ሕመም ማከሚያ መንገድ የቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት መሆኑን ገልጸዋል። በካንሰር ሕመም ከተጠቁት ሕጻናት መካከል 70 ከመቶ ከበሽታው የሚፈወሱት እነዚህን ሦስቱን የሕክምና ዓይነቶች በመጠቀም መሆኑን ገልጸው፣ ሕክምናውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሕጻናትን ወይም የታካሚውን የዕድሜ ገደብ ማወቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም አከለው አስረድተዋል። በሕክምናው ዘርፍ ከፍተኛ እድገት መታየቱን የገለጹት ዶ/ር ፍራንቸስካ ደል ቡፋሎ፣ እስካሁን በርካታ ጥናቶች እና ምርምሮች መደረጋቸውን ገልጸው፣ ከምርምር ውጤቶች አንዱ ኢሚዩኖቴራፒ የተባለ አዲስ የካንሰር ሕክምና ዓይነት መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ የሕክምና ዘዴ በተለይም የደም ውስጥ ካንሰርን በማከም የተገኘው የሕክምና ውጤት አመርቂ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በፊት በተለመዱት የካንሰር ሕክምና ዓይነቶች መልካም ውጤት ያልተገኘባቸው እና ሕጻናትን በማጥቃት ላይ የሚገኝ የደም ውስጥ ካንሰር፣ በኢሚዩኖቴራፒ የሕክምና ዓይነት ጥሩ ውጤቶችን ማስገኘቱን አስረድተዋል።

በካንሰር ሕመም ለተጠቁት ሕሙማን በሽታው እንዳለባቸው ማሳወቅ ድንጋጤን እንደሚፈጥርባቸው የገለጹት ዶ/ር ፍራንቸስካ ደል ቡፋሎ፣ ቢሆንም ለሕሙማኑ ያለበትን የሕመም ዓይነት ማሳወቁ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው በተለያዩ የዕድሜ ክልል ለሚገኙት ማለትም ለልጆች እና ለአዋቂዎች እንደ ዕድሜአቸው ገደብ የመወያያ ስልቶችን በማዘጋጀት ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ዶ/ር ፍራንቸስካ ደል ቡፋሎ አክለውም ሕሙማኑን በተለያዩ መንገዶች ተስፋን እና ብርታትን በመስጠት ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አስረድተው ይህን አገልግሎት ለመስጠት በሆስፒታላቸው ውስጥ የሥነ-ልቦና አገልግሎት መስጫ ማዕከል መኖሩን ገልጸዋል።

ሕጻናት በካንሰር ሕመም መጠቃት የዘመናችን እውነታ መሆኑን ያስታወቁት ዶ/ር ፍራንቸስካ ደል ቡፋሎ፣ በእርግጥ እንደ ዕድል ሆኖ ዕድሜአቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑት እና 2 ከመቶ በታች የሆኑ ሕጻናትን ብቻ የሚያጠቃ በሽታ መሆኑን አስረድተው፣ የሕክምና ማዕከላቸው ባለፉት ዓመታት ውስጥ ውጤታማ እና ተስፋን የሚሰጡ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን እና በበሽታው ከተጠቁት ሰዎች መካከል እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታማሚ ፈውስ ማግኘት መቻሉንም አስታውቀዋል። ጥረታቸው ከበሽታው የሚድኑትን ሕጻናት እና አዋቂዎች ቁጥር ወደ መቶ በመቶ ለማድረስ መሆኑን ገልጸው፣ ወደ ፊት ይህን ውጤት ለማምጣት እርግጠኛ መሆናቸውን በ “ባምቢኖ ጄሱ” የሕጻናት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ፍራንቸስካ ደል ቡፋሎ አስታውቀዋል።

15 February 2021, 13:16