ፈልግ

የሉርድ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በፈረንሳይ የሉርድ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በፈረንሳይ 

የሉርድ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በፈረንሳይ

የእመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም በሉርድ ለቅድስት ቤርናዴት ሱብሩ መገለጽ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ፒዮስ 9ኛው (1846-1878) እ.አ.አ. በታህሣሥ 8 ቀን 1854 ዓ.ም. እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች ናት በማለት በይፋ ካወጁት ቀኖናዊ የእምነት እውነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የእዚህ ዝግጅት ዝቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም በሉርድ ለቅድስት ቤርናዴት የተገለጸችላት 18 ጊዜ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸችላት እ.አ.አ. በየካቲት 11 ቀን 1858 ዓ.ም. ነበር፡፡ የተገለጸችላትም ከእህቱዋና ካንዲት ጓደኛዋ ጋር ሆና ማሳቤይ (አሮጌ ድንጋይ) በሚባለው መንደር በሚገኘው በጋቤ ወንዝ አከባቢ እንጨት ለቀማ ስትሄድ ነበር፡፡ ይኸውም ወንዙን ለመሻገር ጫማዋን ስታወልቅ ሳለ የነፋስ እንቅስቃሴ የሚመስል የሽውሽውታ ድምፅ ሰማች፡፡ ከዚያም በኋላ አንገቷን ቀና አድርጋ ስትመለከት ነጭ ቀሚስ የለበሰች በራሷ ነጭ ሻሽ አድርጋ ወገቧን በሰማያዊ መቀነት የታጠቀች በሁለቱም እግሮቿ ላይ ወርቅማ ቀለም ያለው የጽጌረዳ አበባ የነበራት አንዲት ሴት አየች፡፡ ወዲያውኑ በመንበርከክ የመስቀል ምልክት አድርጋ ከሴትዮዋ ጋር የመቁጠሪያ ጸሎት ደገመች፡፡ በጸሎቱም ፍጻሜ ሴትዮዋ እንደ ተሰወረችባት ቅድስት ቤርናዴት መስክራለች፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ዋና ነገር ቢኖር ለእመቤታችን እጅግ ንጽሕት ድንግል ማርያም ወዳጆች ሁሉ የመቁጠሪያን ጸሎት መድገም አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ድንግል ማርያም በሉርድ ለቅድስት ቤርናዴት ለመጨረሻው ጊዜ የተገለጸችላት እ.አ.አ. በሐምሌ 16 ቀን 1858 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዚህ ዐይነት የእመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ቤርናዴት በሉርድ የመገለጽ ክሥተት ለአምስት ወር ሙሉ ቆይቶ እንደ ነበር መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የመገለጿም ምሥጢር ትልቅ እንደ ሆነ ከዚሁ ለመረዳት እንችላለን፡፡ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም በሉርድ ማንነቷን ለቅድስት ቤርናዴት ሱብሩ የገለጸችላት በ16ኛው የመገለጿ ዕለት ሲሆን እ.አ.አ. በመጋቢት 25 ቀን 1858 ዓ.ም. ነበር፡፡ ዕለቱም እንደ ላቲን ሥርዓተ አምልኮ የምሥጢረ ሥጋዌ ማለትም የጌታችን ኢየሱስ ሰው የመሆን ምሥጢር በዓል በሚከበርበት ዕለት ነበር፡፡ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅደስት ቤርናዴት በሉርድ አከባቢ ቋንቋ ማንነቷን የገለጸችላት “Que soy immaculada Councepciou” በማለት ነበር፡፡ ትርጓሜውም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነስሁ ነኝ ማለት ነው፡፡ በመገለጿ ሂደት እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ቤርናዴት የሰጠቻት መሠረታዊ ትእዛዞች ሁለት ነበሩ፡፡ ይኸውም ሂጂና ከምንጩ ውኃ ጠጪ፤ ሂጂና ካህናት አንድ የጸሎት ቤት እዚህ እንዲሠሩና ሰዎች ለጸሎት በኡደት እዚህ እንዲመጡ እንዲያደርጉአቸው ንገሪአቸው የሚሉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁለቱም ትእዛዞች በተግባር እንደ ተፈጸሙ ከሉርድ ታሪክ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ይኸውም ቅድስት ቤርናዴት በእመቤታችን ትእዛዝ መሠረት በእጇ በመጫር ምንጭ እንዲፈልቅ በማድረግ የጠጣችበት የውኃ ምንጭ እስከ ዛሬ ድረስ ለብዙ ሺ ሰዎች የፈውስ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

በሉርድ እንዲሠራ እመቤታችን ለቤርናዴት ስለ ጠየቀቻት ቤተጸሎት ከተነሣ ደግሞ በትንሹ በሉርድ ከተማ ለእመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር አምስት ባዚሊካዎች ተሠርተዋል፡፡ ይኸውም እ.አ.አ. በ1866 ዓ.ም. የተመረቀው የምድር ቤት ባዚሊኮ በመባል የሚታወቀው ባዚሊካ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ሁለተኛው ባዚሊካ ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰችው እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ነው፡፡ ይኸው ባዚሊካ የተመረቀው እ.አ.አ. በ1876 ዓ.ም. ነበር፡፡ የሉርድ ሦስተኛው ባዚሊካ የመቁጠሪያ ባዚሊካ ሲባል ሥራው እ.አ.አ. በ1883 ዓ.ም. ተጀምሮ እ.አ.አ. በ1899 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ በ1901 ዓ.ም. ነበር የተመረቀው፡፡ አራተኛውና ትልቁ የሉርድ ባዚሊካ የቅዱስ ፒዮስ 10ኛው (1903-1914) ባዚሊካ ሲሆን የሉርድ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም መገለጽ 100ኛውን ዓመት ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀት ለማክበር ታስቦ የተሠራ ነበር፡፡ ባዚሊካው የምድር ቤት ባዚሊካ ሲሆን ባንድ ጊዜ 25,000 (ሃያ አምስት ሺ) ሰው የመያዝ አቅም ያለው ነው፡፡ የተመረቀውም እ.አ.አ. በ1958 ዓ.ም. በካርድናል አንጀሎ ሮንካሊ በኋላ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛው በነበሩት (1958-1963) በቅዱስ ዮሐንስ 23ኛው እጅ ነበር፡፡ አምስተኛው የሉርድ ባዚሊካ የቅድስት ቤርናዴት ባዚሊካ ሲሆን በጋቤ ወንዝ ማዶ ለመጨረሻው ጊዜ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ቤርናዴት በተገለጸችላት ቦታ ነው የተሠራው፡፡ የተመረቀውም እ.አ.አ. በ1988 ዓ.ም. ነበር፡፡

ባጭሩ በየዓመቱ 350,000 (ሶስት መቶ ሀምሳ ሺ) የሚሆኑ መንፈሳውያን ተጓዦች ፈውስ እየተመኙ በሉርድ ምንጭ ውኃ ይታጠባሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶች መንፈሳዊ መጽናናትን አግኝተው ሲመለሱ ሌሎቹ ደግሞ ካለባቸው አካላዊም ሆነ አእምሮአዊ ሕመም እንደሚፈወሱ ይነገራል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በሉርድ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ተፈጽመዋል በማለት የሚነገርላቸው ተአምራዊ ፈውሶች ብዛት ከ7,000 በላይ ሲሆን ቤተክርስቲያን በይፋ ያረጋገጠቻቸው እውነተኛ ተአምራዊ ፈውሶች ብዛት ግን እስካሁን 69 ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ቤርናዴት ያስተላለፈቻት ዋናው መልእክት “ዓለም ንስሐ እንዲገባና ወደ ጌታ እንዲመለስ ጸልዪ፤ ተጋድሎም አድርጊ” የሚል ነበር፡፡ ለቤርናዴት ደግሞ በግል ደረጃ ያለቻት፣ “በዚህ ዓለም ደስተኛ እንድትሆኚ ልረዳሽ ቃል አልገባልሽም፤ በሚመጣው ሕይወት ግን ደስተኛ እንድትሆኚ ላደርግልሽ ቃል እገባልሻለሁ” በማለት ነበር፡፡ እንግዲህ እኛ ሁላችንም ንስሐ እንድንገባ፣ ተጋድሎም እንድናደርግና ወደ ጌታ እንድንመለስ የሉርድ እመቤታችን እጅግ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን፡፡ ከምድራዊ ሕይወት በላይ ለዘለዓለማዊ ሕይወታችንም ተግተን እንድንሠራ ታማልድልን፡፡ አሜን፡፡

10 February 2021, 13:43