ፈልግ

ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በማቅረብ ላይ ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በማቅረብ ላይ 

የ“ካቶሊክ አክሽን” እንቅስቃሴ አባላት መልካም ዜናን ለማሰራጨት መዘጋጀታቸውን አስታወቁ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 23/2013 ዓ. ም. በእኩለ ቀን ላይ ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ከሰላም መልዕክተኛ ሕጻናት ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ሕጻናቱ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያላቸውን ፍቅር ከገለጹላቸው በኋላ ከቅዱስነታቸው ጋር ያላቸውን አንድነት በማደስ ድጋፋቸውን ገልጸውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሕጻናቱ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ድጋፋቸውን የገለጹት እንዳለፉት ዓመታት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል መሆኑ ታውቋል። ከሮም ሀገረ ስብከት፣ ማኅበራዊ መገናኛ መምሪያ በኩል ድጋፍ ሲደረግለት የቆየው የ “ካቶሊክ አክሽን” እንቅስቃሴ የሰላም መልዕክተኞች ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያላቸውን ፍቅር እና ድጋፍ የገለጹት የሰላም ወር ተብሎ ሲከበር በቆየው በጥር ወር ማለቂያ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቫቲካን በመገኘት አብረዋቸው የነበሩ የሰላም መልዕክተኛ ሕጻናትን በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ከምዕመናን ጋር ካስተዋወቁ በኋላ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም የሚከተለውን የማበረታቻ መልዕክታቸውን አስተላልፈውላቸዋል፥

"ሌሎች ሕጻናትም በየቁምስናቸው ሆነው በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ከሰላም መልዕክተኞች ጋር ያላቸውን አንድነት በመግለጽ ላይ ናቸው። ዘንድሮ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቢኖርም፣ በወላጆቻቸው፣ በመምህራኖቻቸው እና በመሪ ካህናት በመታገዝ የሰላም ምስክርነት መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። ይህን መልካም ተግባራችሁን እየገለጻችሁ በድፍረት ወደ ፊት መጓዝ አለባችሁ፤ ጎበዞች!" በማለት ቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።      

ወደ ኢየሱስ ይበልጥ መቅረብ

የሰላም መልዕክተኛ ሕጻናቱ ዘንድሮ ያከናወኑት ተግባር ከሌላው ዓመት የተለየ መሆኑን ለቅዱስነታቸው በጻፉት መልዕክት የገለጹላቸው ሲሆን፣ የዘንድሮ የሰላም መልዕክታቸውን በወረቅት እና በጨርቅ ላይ በመጻፍ በሮም ከተማ ውስጥ ያሰራጩ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸውም ሕጻናቱ የጻፏቸውን መልዕክቶች በንባብ እንዲያሰሙ ዕድል የሰጧቸው ሲሆን በተጨማሪም ሥራዎቻቸው በሌሎች ሰዎች ዘንድ እንዲታወቅላቸው ማድረጋቸው ታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሕጻናቱን የዘንድሮ እቅዶች ያወከ ቢሆንም ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበው እንዲጸልዩ ምቹ አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል።

ሰላም፣ መልካም ዜና ነው

ሕጻናቱ በጽሑፍ መልዕክታቸው፣ የዘንድሮ ዝግጅት እያንዳንዱ ሕጻን ችሎታውን በመጠቀም የጋዜጠኛነት ጥበብ የታየበት፣ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑበት፣ በፎቶ ሪፖርተርነት እና በአዘጋጅነት ተሳትፎአቸውን የገለጹበት መሆኑን ተናግረዋል። ቃለ መጠይቆችን በማድረግ እና ዘገባዎችን በመሰብሰብ መልካም ዜና የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተላለን ብለዋል። እርስ በእርስ በመተሳሰብ፣ ሰላምን በመፍጠር፣ ለፍጥረት እና ለእያንዳንዱ ወንድም አስፈላጊውን ጥበቃ እና እንክብካቤ እናደርግለታለን ብለዋል። ለፍጥረት ጥበቃን እና እንክብካቤ ማድረግ በሁለት ድርጅቶች የሚመራ መሆኑን የገለጹት ሕጻናቱ የመጀመሪያ “የሰዎች ምድር” በተሰኘ ዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎት ድርጅት እና ባለፈው ዓመት የተቋቋመው “ኢየሱስ መለኮታዊ ሠራተኛ” ፈንድ መሆኑን ገልጸዋል። ለዘንድሮ ዝግጅት የተመረጠ መሪ ቃል “ሰላም፣ መልካም ዜና ነው!” የሚል መሆኑን የገለጹት ሕጻናቱ አክለውም በዚህ መሪ ቃል በመታገዝ ዛሬ የምንገኝበትን እውነታ ማየት የምንችለው በከተማችን በችግር ውስጥ የሚገኙን በመመልከት፣ እንዲሁም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዓለማች የሚገኝበትን ሁኔታ ሳንዘነጋ በመመልከት ነው ብለዋል። የሰላም መልዕክተኛ ሕጻናቱ በመጨረሻም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ በዚህ ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና በመከተል፣ የተስፋ እና የሰላም ፍሬን ለዓለም ሕዝብ በማድረስ ለሚያበረክቱት የሐዋርያዊ መሪነት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። 

01 February 2021, 10:16