ፈልግ

በማላዊ ከሚገኙ አልቢኖዎች መካከል አንዱ፤ በማላዊ ከሚገኙ አልቢኖዎች መካከል አንዱ፤ 

የማላዊ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ አልቢኖዎችን በማገዝ ላይ መሆኗ ተገለጸ።

በማላዊ ውስጥ የቆዳ መንጣት በሽታ ያለባቸው እና አልቢኖዎች በመባል በሚታወቁ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎችን የሚቀጣ ሕግ ቢኖርም፣ አልቢኖዎቹ ከማኅበረሰቡ የተገለሉ እና በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት መከራ የሚደርስባቸው መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማላዊ የዞምባ ሀገረ ስብከት የፍትህ እና ሰላም ምክር ቤት በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አልቢኖዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው የሚደርስባቸውን ችግሮች ለማስወገድ፣ ከጥቃት እና ከአመጽ ተከላክሎ  ሰብዓዊ መብታቸውን ለማስከበር ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ጥቃትን ለመከላከል አብሮ መሥራት

በማላዊ፣ የዞምባ ሀገረ ስብከት የፍትህ እና የሰላም ምክር ቤት፣ አልቢኖዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ በብስክሌት ፈጥኖ በመድረስ ማኅበራዊ ችግራቸውን የሚፈታ እና ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚያስጠብቅ ፈጥኖ ደራሽ ግብረ ሃይል ማሰማራቱ ታውቋል። ግብረ ሃይሉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ መሪዎች ጋር በመተባበር የአልቢኖዎችን ሰላማዊ ሕይወት መኖር መብታቸውን በዘላቂነት ለማስከበር የሚሰሩ መሆኑ ታውቋል። ለግብረ ሃይሉ ብስክሌቶችን በመመደብ፣ አልቢኖዎች ወደሚኖሩበት የዞምባ ሀገረ ስብከት ውስጥ በፍጥነት በመድረስ ከሚደርስባቸው ጥቃት እንዲከላከሉ የሚያስችል የሁለት ዓመት እቅድ፣ በማላዊ የዞምባ ሀገረ ስብከት የፍትህ እና የሰላም ምክር ቤት መወጠኑ ታውቋል።

መገለልን በመቃወም

የዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአልቢኖዎች ላይ መገለል ከሚታይባቸው አገራት መካከል ማላዊ አንዷ መሆኗ ታውቋል። ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የወንጀል ሕግ ላይ ማሻሻያ ተደርጎ እርምጃን በመውሰድ ከበድ ያለ ቅጣቶች የሚጣሉ ቢሆንም አልቢኖዎችን ከማኅበረሰቡ መካከል ማግለል፣ ማፈን፣ መግደል እና አካላቸውን በሽያጭ ለጥንቆላ ተግባር ማቅረቡ የቀጠለ መሆኑ ታውቋል። 

01 February 2021, 10:26