ፈልግ

በቫቲካን የአትክልት ስፍራ የሚገኝ የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ሐውልት በቫቲካን የአትክልት ስፍራ የሚገኝ የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ሐውልት 

በቫቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ በዓል ተከብሮ ዋለ

በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ቅዳሜ የካቲት 20/2013 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ በዓል ተክብሮ መዋሉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክብረ በዓሉን በጋራ ያዘጋጁት በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ሕብረት ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና በቫቲካን የአርሜኒያ ሪፓብሊክ ኤምባሲ ሲሆኑ፣ ሦስቱ በጋራ ሆነው ያዘጋጁት የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ክብረ በዓል በላቲን የአምልኮ ስርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ መከበሩን ለማስታወስ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ከቤተክርስቲያ አበው በካከል አንዱ እና ሊቅ በመባል፣ በጠቅላላው የላቲን ስርዓት የቀን አቆጣጠር መሠረት፣ የካቲት 20 ቀን እንዲከበር በማለት መወሰናቸው ታውቋል።

ዓርብ የካቲት 19/2013 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና የክርስቲያኖችን ሕብረት ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ መሠረት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ በ4:30 የተጀመረውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የመሩት መሆናቸው ታውቋል። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ሥነ-ሥርዓት ከብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ጋር የመሩት፣ በእስታንቡል የአርሜኒያ ካቶሊካዊ ምዕመናን ተጠሪ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሌቮን ዜኪያን እና በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ሕብረት አስተባባሪ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ብራያን ፋሬል መሆናቸው ታውቋል።

ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ቀጥሎ በቫቲካን ውስጥ እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም. ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ባርከው ይፋ ባደረጉት የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ሐውልት ፊት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መካሄዱ ታውቋል። በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ የተገኙበትን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የመሩት በሮም የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ካያጅ ባርሳሚያን መሆናቸው ታውቋል።

የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ

በአሥረኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአርሜኒያ መናኒ የነበረው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገጣሚ፣ መንፈሳዊ ጸሐፊ እና የዜማ ደራሲ የነበረ ሲሆን በጽሑፍ አዘጋጅቶ ካቀረባቸው የጸሎት መጻሕፍት መካከል አንዱ እና ታዋቂው “ሰቆቃው መጽሐፍ” የሚል ሲሆን ይህ የጸሎት መጽሐፍ በአርሜኒያ ሥነ-ጽሑፍ ድንቅ የተባለለት መሆኑ ታውቋል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ራሱ ያበረከተውን የጸሎት መጽሐፍ፣ ለአገሩ ሕዝብ በሙሉ የተበረከተ የጸሎት “ኢንሳይክሎፔዲያ” ከማለቱ በተጨማሪ፣ በሁሉም የሕይወት መስክ ለሚገኝ ሰው የጸሎት መመሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተስፋ ያደረገበት መሆኑ ታውቋል። የናሬክው ቅዱስ ጎርጎርዮስ፣ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በተለየ ሁኔታ እንዲከበር ዕውቅና የተሰጠው መሆኑ ታውቋል።

27 February 2021, 18:00