ፈልግ

በሆንዱራስ ውስጥ ከሕገ ወጥ ታጣቂዎች የተገኙ የወንጀል መሣሪያዎች  በሆንዱራስ ውስጥ ከሕገ ወጥ ታጣቂዎች የተገኙ የወንጀል መሣሪያዎች  

ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነፃ የሚያደርግ ስምምነት፣ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑ ተገለጸ።

ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጋር ቃለ ምልልስ ያደርጉት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በዓለም ንግድ ድርጅት እና ዋና መቀመጫቸውን ጀኔቭ ያደረጉት ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቋሚ ታዛቢ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ሲልቫኖ ማርያ ቶማሲ፣ ዓለማችንን ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነፃ በማደርግ ዕቅድ የአብያተ ክርስቲያናት ሚና አስፈላጊነትን በማስመልከት አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሲልቫኖ ማርያ ቶማሲ፣ ዓለማችንን ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነጻ የሚያደርግ ስምምነት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ሕግ እና በሕዝብ አስተያየት እየጎላ መምጣቱን ገልጸዋል። ካርዲናል ቶማሲ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ዓለምን ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነጻ ወደሚያደርግ ስምምነት የተደረሰው እ.አ.አ ሐምሌ 7/2017 ዓ. ም. ሲሆን፣ ተግባራዊነቱ የተረጋገጠው እ.አ.አ ጥር 22/2021 ዓ. ም. መሆኑን ተናግረዋል። ስምምነቱ አባል አገራትን ኒውክሌር የጦር መሣሪያዎችን ከማሳደግ፣ ከመለማምድ፣ ከማምረት ፣ ማከማቸት፣ ከቦታ ቦታ ከማዘዋወር የሚያግድ ሲሆን በተጨማሪም የስምምነት ውሎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያግዝ መሆኑ ታውቋል። ለኒውክሌር የጦር መሣሪያ አምራች አገራት የጊዜ ገደብን በማስቀመጥ፣ የድርድር ጊዜን በመመደብ፣ ተመልሰው ወደ ምርት እንዳይገቡ እና ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ምርት እቅዳቸውን እንዲያቋርጡ የሚያስገድድ መሆኑ ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ቶማሲ አክለውም፣ የሞራል ግዴታዎች ብቻ ወደ ትጥቅ መፍታት የሚመሩ መሆኑን ገልጸው፣ አዲስ የወጡት ደንቦች፣ ዓለማችንን ከኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ነጻ ለማድረግ የሚያግዙ የተወሳሰቡ ድርድሮች መልካም ውጤቶችን እንዲያመጡ የሚያግዙ እና የኒውክሌር መሣሪያዎች ተጠቃሚ ያልሆኑ መንግስታትም በጉዳዩ ላይ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ የሚያሳስብ መሆኑን አስረድተዋል።

ሲቪል ማኅበረሰብ፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ሐይማኖታዊ ማኅበረሰብ በጋራ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ፣ ተመሳሳይነት ያላቸውን ሞራላዊ መልዕክቶችን ለሚያምኑ እና ለማያምኑ ሰዎች በማስተላለፍ፣ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ምርትን መቃወም የሚችሉ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ተናግረዋል። በየአገራቱ የሚገኙ አንዳንድ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ቶማሲ፣ እነዚህ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ከተወካዮቻቸው ጋር እና በአውታረ-መረብ በመገናኘት ድምጻቸው እንዲሰማ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል።

“የኒውክሌር መሣሪያዎች መኖር ብቻውን የማያቋርጥ አደጋ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቶማሲ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለማችን የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በአገሮች መካከል ያለውን አለመመጣጠን ጉልህ ማድረጉን ገልጸው፣ ከዚህ በፊት ለጦርነት ማስኬጃ ይውሉ የነበረውን ገንዘብ ለማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ እድገት ማዋል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ተግባራት የትኞቹ እንደሆኑ ከማሳየቱ በተጨማሪ፣ እንደ ቤተሰብ ፍታሃዊ ስርዓቶችን ለመገንባት እና ለሕዝቦች አስፈላጊውን አገልግሎት በማቅረብ ዓለማችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል በማለት ማበረታታቸውን አስታውሰዋል። እነዚህን መልካም ተግባራት ማከናወን ጠቃሚ ግብ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊ እሴት መሆኑንም ብጹዕ ካርዲናል ቶማሲ አክለው አስረተዋል። መዋዕለ ነዋይን በጦር መሣሪያ ላይ ማፍሰስ የሚጀምረው ስጋት ሲኖር ነው ያሉት ካርዲናል ቶማሲ፣ ነገር ግን ኅብረተሰቡ አስፈላጊው ፍላጎቶች ካልተሟሉለት በጭራሽ ተረጋግቶ ሊኖር የማይችል መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ካርዲናል ቶማሲ ገለጻ መሠረት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ ብዙ አገሮች የተመኙትን የኤኮኖሚ ዕድገት የሚገታ በመሆኑ ፣ ሃያላን መንግሥታትን ጨምሮ በበርካታ አገራት ኤኮኖሚያቸውን ለማነቃቃት የገንዘብ ድጋፍን ማድረግ መቻል በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለጦር መሣሪያ ግዥ ሊያወጡ ያሰቡትን የገነዘብ መጠን ለኤኮኖሚያዊ ዕድገት ቢያውሉት፣ በዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥ ያላቸውን የበላይነት ለመጠበቅ ለሚፈልጉ መንግሥታት ስትራቴጂካዊ ምርጫ መሆኑን ካርዲናል ቶማሲ ገልጸው፣ ከችግሩ ለማገገም ያላቸው ኃይል እና ተጽዕኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊታይ ይችላል በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።         

24 February 2021, 15:30