ፈልግ

ካርዲናል አዩሶ፣ የሰላም እና የአንድነት ባሕልን ለማሳደግ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ሊከበር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን መርዳት እና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ እ.አ.አ ለ2021 ዓ. ም. የተጋጀው የዛይድ ሽልማት ለ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ዓለም አቀፍ ማኅበር መዘጋጀቱ በተለያዩ እምነቶች መካከል የተፈጠረው የመተጋገዝ ምልክት ፍሬ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍን በማግኘት ጥር 27/2013 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን የሚከበር ሲሆን ይህም በተባበሩት አረብ ኤምረቶች አቡዳቢ ከተማ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በታላቁ የአል-አዛር ኢማም በሆኑት በአህመድ አል-ታይብ መካከል የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ከተፈረመ ከሁለት ዓመት በኋላ መሆኑ ታውቋል። በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ እንደገለጹት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን የሰላም ባሕልን ለማሳደግ በጋራ የመስራትን ፍላጎት ማሳደጉን አስረድተዋል። ካርዲናል ሚገል አንገል በማከልም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ ሲጠናቀቅ ወንድማማችነትን እና አንድነትን ማሳደግ የሚቻልበት የመልሶ ማቋቋም ተግባር ለማከናወን ተጠርተናል ብለዋል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ በአዲሱ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ሃላፊነቶችን በግል እና በጋራ እንድንወስድ የሚያነሳሳ እጅ ግጠቃሚ ሰነድ መሆኑንም ካርዲናል ሚገል አንገል አስረድተዋል። 

እ.አ.አ ታኅሳስ 21/2020 ዓ. ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 75ኛ ጠቅላላ ስብሰባን ባካሄደበት ወቅት ጥር 27 ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ተብሎ በየዓመቱ እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነቱን ያጸናው አባል አገራቱ በሃይማኖቶች እና በባህሎች መከከል የሚደረገውን ውይይት ማሳደግ እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑ ይታወሳል። ስምምነቱ ከዚህም በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ቀውስ በአንድነት ላይ በተመሠረተ ዓለም አቀፍ ሃላፊነት፣ አንድነት እና ሁለገብ ትብብር መቋቋም እንዲቻል ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። ስለ ወረርሽኙ ባለን የግል ግንዛቤ ብቻ ራስን ከችግር ማዳን እንደማይቻል የስምምነት ሰነዱ አስታውቆ፣ በሃይማኖቶች እና በባህሎች መከከል የሚደረገውን ውይይት ለማሳደግ፣ በተባበሩት አረብ ኤምረቶች በአቡዳቢ ከተማ እ.አ.አ በ2019 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በታላቁ የአል-አዛር ኢማም በሆኑት በአህመድ አል-ታይብ መካከል የተፈረመው የሰላም፣ የአንድነት እና የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ መፈረሙን ስምምነቱ አስታውሷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ጥር 27 ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን እንዲከበር የወሰነው በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መካከል የተደረሰውን ስምምነት ለማስታወስ መሆኑ ታውቋል። ጥር 27 ቀን የሰው ልጆች ካላቸው መልካም አመለካከት አንጻር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት በአሰቃቂው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜያት የሰላም፣ የመቻቻል፣ የአንድነት እና የመግባባት ባሕልን ለማሳደግ ፍላጎታቸውን ለማነቃቃት ተስፋ የተደረገበት መሆኑ ታውቋል።

ሐይማኖቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ በሐይማኖት ተቋማት መካከል ያለው ወዳጅነት እና መከባበር እጅግ ገስፈላጊ እንደሆነ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን መሪነት ስልጣን ከተቀበሉበት ጊዜ አንስቶ መናገራቸውን አስታውሰዋል። የተለያዩ እምነት ተከታዮች በኅብረት እየተጓዙ የጋራ ውይይቶችን በማካሄድ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ጠቅላላ ወንድማማችነት ለማሳደግ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ ገልጸው፣ የተለያዩ ሐይማኖት ተከታዮች እሴቶቻቸውን በመጠቀም ፍትሃዊ እና ጤናማ ማኅበረሰብን ለመገንባት የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። ጽድቅ፣ ታማኝነት፣ የጋራ ፍቅር፣ ለሌሎች መጨነቅ፣ በተለይም ለችግረኞች ቸርነትን መግለጽ እና ምህረት ማድረግ ለተለያዩ ሐይማኖቶች መንፈሳዊ መሣሪያቸው እንደሆነ፣ ይህም ተጨባጭ እርምጃዎችን መልካም ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ጋር በኅብረት መውሰድን የሚጠይቅ መሆኑን ካርዲናል ሚገል አንገል ተናግረው፣ ሁላችንም የሰላም እና የአንድነት መልእክተኞች ለመሆን የተጠራን፣ ግጭቶችን እና መከፋፈልን ከሚያበረታቱ ሰዎች በተቃራኒ ወንድማማችነትን ማወጅ ያለብን ጊዜ አሁን መሆኑን አስረድተዋል።

የሁሉ ፈጣሪ እና አባት እግዚአብሔር በመሆኑ ራሳችንን የአንድ ቤተሰብ አባላት አድረገን መመልከት እንደሚያስፈልግ፣ ይህም የእምነታችን መሠረታዊ ውጤት፣ ከጥላቻ ወጥተን በወንድማማችነት አብሮ ወደ መኖር፣ በመካከላችን የሚታየው ልዩነት የአመጽ ምክንያት እንዳይሆን በመጠንቀቅ፣ በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ፍቅር አብሮ ለመኖር የሚያስችል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

“ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ የሚያምኑትን ሆነ የማያምኑትን፣ ወንዶች እና ሴቶች ማኅበራዊ ወዳጅነትን እንዲያሳድጉ የሚጋብዝ መሆኑን፣ ይህን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማንበብ በዓለማችን ውስጥ የግልም ሆነ የጋራ ሃላፊነት ሊሰማን እንደሚያስፈልግ፣ በቅርቡ የምናከብረው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀንም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይፋ ካደረጉት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ፍሬ እና ውጤት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ተናግረዋል። በሰብዓዊ ወንድማማችነት እና የተባበሩት መንግሥታት የሚያስተባብረው ዓለም አቀፍ ቀን፣ ሁለቱም የወንድማማችነትን መልዕክት ለማስተላለፍ የታለሙ መሆኑ ታውቋል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል አርዕስት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ በኅብረተሰባችን ውስጥ ውይይትን በማካሄድ የብቸኝነት ስሜትን ለማስወገድ፣

ሰብዓዊ ወንድማማችነት፣ ማንም ሰው ተከብሮ የመኖር መብቱን ሊያጣው እንደማይችል አፅንዖት የሚሰጥ እና ሰው ሁሉ የሚቻለውን ሁሉ እንዲያበርከት የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። ሰብዓዊ መብት በድንበር የሚከለል ባለመሆኑ፣ የተወለደበትን አካባቢ መሠረት በማድረግ ማንም ሰው እንዳይገለል የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቃለ ምዕዳን በግልጽ ያሳስባል። የልዩነት እና የራስ ወዳድነት ባሕል ያጠቃው ዓለማችን አዲስ እና ጠቅላላ አንድነት በማምጣት በጋራ መኖር የሚችለው ሰብዓዊ ወንድማማችነትን በማሳደግ በመሆኑ፣ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ወንድሞች እና እህቶች ተገናኝተው አንድነታቸውን መግለጽ አስፈላጊ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ ተናግረዋል።

ለዓለም ሰላም እና አብሮ ለመኖር የሚያስችል የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድን በተግባር መተርጎም እንዲቻል እ.አ.አ በነሐሴ ወር 2019 ዓ. ም. የተቋቋመውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ኮሚቴን በሰብሳቢነት ለመራት የመጀመሪያ ዕድል ማግኘታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ፣ ከፍተኛ ኮሚቴው ባሁኑ ጊዜ ከዓለም ዙሪያ ከተመረጡ የሐይማኖት መሪዎች እና ምሑራን፣ ከክርስቲያን፣ ከአይሁድ እና ከእስልምና ሐይማኖቶች ተወጣጥተው በሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ዓላማ በመመራት ሰላምን እና እርስ በእርስ መከባበርን በሚያሳድጉ የባሕል አዋቂዎች የተዋቀረ መሆኑን አስረድተዋል። የከፍተኛ ኮሚቴ አባላት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና ከታላቁ የአል-አዛር ኢማም ከሆኑት ከአህመድ አል-ታይብ የተላከውን መልዕክት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለሆኑት ለክቡር ዶ/ር አንቶኒዮ ጉተሬዝ ለማድረስ እ.አ.አ ታኅሳስ 4/2019 ዓ. ም. በኒውዮርክ ከተማ መገናኘታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል አዩሶ፣ በወቅቱ ጥር 27 ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰናቸውን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ ኮሚቴ አስተባባሪነት በኮቪ-19 ወረርሽኝ የተጠቁትን ለማስታወስ፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮች እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች እ.አ.አ ግንቦት 14/2020 ዓ. ም. በጸሎት እና በጾም መተባበራቸውን አስታውሰዋል።

እ.አ.አ 2019 ዓ. ም. ለተመሰረተው ለ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የተዘጋጀው የዛይድ ሽልማት የአረብ ኤምሬቶች መስራች የሆኑትን ሸክ ዛይድ ቢን ሱልጣን ኣል ናያንን ለማስታወስ ሲሆን የመጀመሪያው የክብር ሽልማት እ.አ.አ 2019 ዓ. ም. ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የታላቁ አል-አዛር ኢማም ለሆኑት ለአህመድ አል-ታይብ የተሰጠ መሆኑ ይታወሳል። ቀጥሎም ሽልማቱ የዓለማችንን ሕዝቦች ለማቀራረብ እና ሰላማዊ አንድነትን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረትን ለሚያደርጉ ግለ ሰቦች እና ድርጅቶች የሚዘጋጅ መሆኑ ታውቋል። ሽልማቱ በሕዝቦች መካከል ድልድይ በመገንባት ሰብዓዊ ግንኙነቶችን የሚያሳድግ፣ በአገሮች መካከል ኅብረት እና መግባባት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑ የታመነበት ሲሆን፣ የዚህ ሽልማት መዘጋጀት፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ባሉ ወንዶችና ሴቶች መካከል ፍሬያማ የትብብር ምልክትን ለማሳየት ተስፋ የተጣለበት መሆኑን በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ አስታውቀዋል።                

02 February 2021, 10:38