ፈልግ

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጨረሻ እራት፤ "እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ" የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጨረሻ እራት፤ "እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ" 

ለክርስቲያኖች አንድነት የተመደበ የጸሎት ሳምንት 3ኛ ቀን።

“የእኔ ትእዛዝ፣ እኔ እንደወደድኋችሁ እናንተም እርስ በእርስ እንድትዋደዱ ነው” (ዮሐ. 15:12)

“ርኅራኄን ልበሱ” (ቆላ. 3:12-17) ፣ “እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ (ዮሐ. 13:1-15 ፤ 34-35)።

የመጽሐፍ ቅዱስ አስተንትኖ፥ “አንድ አካል ስለ መሆን”

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ አንድ ቀን አስቀድሞ የሐዋርያቱን እግር ለማጠብ ተንበረከከ። በኅብረት አብሮ መኖር አስቸጋሪ እንደሆነ እና እርስ በእርስ በመተጋገዝ ይቅርታን መደራረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ለጴጥሮስ፥ “እኔ እግርህን ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር አንድነት አይኖርህም” አለው። ጴጥሮስም እግሩን ለኢየሱስ አቀረበለት፤ እግሩን ከታጠበ በኋላ በኢየሱስ ትህትና እና ገርነት ልቡ ስለ ተነካ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በጥንታዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ክርስቲያኖችን ማገልገል ጀመረ።

በወይኑ ግንድ በኩል፣ ለወይኑ ልምላሜ የሚያግዙ ጠቃሚ ምግቦች እንደሚመላለሱ ሁሉ፣ ፍቅር እና ሕይወት በእኛ ውስጥ በመመላለስ፣ ክርስቲያኖች በሙሉ አንድ አካል እንዲሆኑ ኢየሱስ ይፈልጋል። ዛሬም ቢሆን እንደ ጥንቱ በኅብረት አብሮ መኖር ቀላል አይደለም።

የራሳችን ውስንነትም አለብን። አንዳንድ ጊዜ በማኅበረሰብ ፣ በቁምስና ወይም በቤተሰብ ውስጥ ለእኛ ቅርብ የሆኑትን ሰዎች እንኳ መውደድ ያቅተናል። ከእነርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ የሚቋረጥበት ጊዜ አለ። ቢሆንም ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማድረግ ርኅራሄን እንድንለብስ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋብዞናል። እግዚአብሔር እንደወደደን በማወቃችን፣ በጥንካሬአችን ሆነ በድክመታችን ጊዜ ሁሉ እርስ በእርስ በእንግድነት እንድንቀባበል የእግዚአብሔር ፍቅር ይገፋፋናል። ያኔ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን እንደሚገኝ እናውቃለን።

ከባዶ እጅ ተነስተን የኢየሱስ ክርስቶስ በሆነች እና እርሱ በመሠረታት ቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኝ የፍቅር አንድነት መካከል እርቅን ማምጣት ትችላላችሁ ወይ? በጋራ ጥረት ተደግፋችሁ ስለቆማችሁ ደስ ይበላችሁ! ካሁኑ በኋላ ከወንድሞቻችሁ እና ከእህቶቻችሁ ጋር በኅብረት በምታከናውኑት ተግባር ሁሉ ብቻችሁን አይደላችሁም። አብራችሁ በመሆን ለምትኖሩበት ማኅበረሰብ ምሳሌ ለመሆን ተጠርታችኋልና።        ከቴዜ ጸሎት፣ ገጽ 48-49 (እ.አ.አ 2000 ዓ. ም.)        

ጸሎት

እግዚአብሔር አባት ሆይ! ፍቅርህን በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በወንድሞቻችን፣ በእህቶቻችን በኩል ገልጠህልናል። በልዩነታችን ጊዜ ቢሆን ይቅርታን በማድረግ መኖር እንድንችል ልባችንን ክፈትልን። አንድ አካል ሆነን እንድንኖር እና በዚህ ጸጋ በመታገዝ እያንዳንዳችን ወደ ብርሃን እንድንቀርብ እርዳን። ሁላችንም የሕያው ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌዎች እንድንሆን አድርገን። አሜን።

ይህ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ሦስተኛ ቀን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተንትኖ የተዘጋጀው፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ውስጥ የእምነት ደንብ ኮሚሽን ነው።

21 January 2021, 15:51