ለክርስቲያኖች አንድነት የተመደበ የጸሎት ሳምንት 2ኛ ቀን።
“በእኔ ኑሩ ፤ እኔም በእናንተ እኖራልሁ” (ዮሐ. 15:14) ፣
“ክርስቶስ በእምነት በልባችሁ እንዲኖር” (ኤፌ. 3:14-21)፣
“ማርያም ሁሉን ነገር በልብዋ ትይዘው ነበር” (ሉቃ. 2:41-52)
የመጽሐፍ ቅዱስ አስተንትኖ፥ “ውስጣዊ እድገትን ማምጣት”
ኢየሱስ ክርስቶስን በሕይወታችን ውስጥ መቀበል፣ ከእርሱ ጋር ለመኖር ያለንን ፍላጎት በማሳደግ ፍሬን እንድናፈራ ያግዘናል። ሙሉ ሰው መሆን እንደ ኢየሱስ በጥበብ ማደግን ያመለክታል።
ኢየሱስ የአይሁድ እምነት ልማዶችን መሠረት በማድረግ ቀላል ሕይወት ኖረ። በናዝሬት ከተማ በቆየባቸው ዓመታትም በሕይወቱ ውስጥ ልዩ እና አስደናቂ ነገር ባይከሰትም፣ በእግዚአብሔር አብ እርዳታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጣ።
ማርያም ይህን እየተመለከተች ፣ እግዚአብሔር በእርሷ እና በልጇ ሕይወት ውስጥ የሚያደርጋቸውን ድንቅ ሥራዎች በልቧ ታሰላስለው ነበር። ቀስ በቀስም የልጇን ምስጢራዊ ሥራዎች በሕይወቷ ለመቀበል ቻለች።
እኛም የኢየሱስ ጥልቅ ፍቅር በእኛ ውስጥ እንዲገባ፣ እርሱ በእኛ ውስጥ እንዲኖር እና እኛም በእርሱ ውስጥ እንድንኖር ያስፈልጋል። እኛ በማናውቀው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ በልባችን ውስጥ እንዲቀመጥ መንፈስ ቅዱስ ቦታን ያዘጋጅለታል። ይህ የሚሆነው በጸሎት ኃይል፣ ቃሉን አድምጠን ለሌሎች ስናካፍል፣ የተረዳነውን በተግባር ስናውል ውስጣዊ ሰውነታችን ኃይልን ሊያገኝ ይችላል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ እንዲወርድ ስንፈቅድለት፣ ወደ አእምሮአችን እና ልባችን፣ ወደ ሰውነታችን ሁሉ ዘልቆ እንዲገባ እናደርጋለን። ይህን ካደረግን እኛም አንድ ቀን የምሕረቱን ጥልቀት እና ስፋት መረዳት እንችላለን”። ከቴዜ ጸሎት፣ ገጽ 134 (እ.አ.አ 2000 ዓ. ም.)
ጸሎት
መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ኢየሱስ ክርስቶስን በልባችን ውስጥ ተቀብለን እንደ ምስጢራዊ ፍቅር አድርገው እንድንከባብ እርዳን። ጸሎታችንን ተቀበልልን፤ ለቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት ብርሃን ሁንልን። የስጦታዎችህ ፍሬዎች በእኛ ውስጥ በትዕግሥት እንዲያድጉ፣ ሥራህም በእኛ በኩል ይገለጥ። አሜን።
ይህ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ሁለተኛ ቀን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተንትኖ የተዘጋጀው፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት እና በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ውስጥ የእምነት ደንብ ኮሚሽን ነው።