ፈልግ

ዛሬ መድኃኒት ተወልዶላችኋል ዛሬ መድኃኒት ተወልዶላችኋል 

ዛሬ መድኃኒት ተወልዶላችኋል

በዚያን ጊዜ ሮማዊው ንጉሥ ቄሣር በግዛቱ በነበረው የሕዝብ ቁጥጥር እንዲደረግ በአዋጅ አዘዘ፡፡ ይህን ትዕዛዝ ሲሰማ ሰው ሁሉ ወደ የትውልድ ሀገሩ ሊጻፍ ሄደ፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ (ከዳዊት ዘር ስለ ነበር) ይቀመጥባት ከነበረችው ናዝሬት ከተማ ነፍሰ ጡር ከነበረችው እጮኛው ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጋር ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተልሔም ሄዱ፡፡ በዚያን ሳሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም የመውለጃዋ ቀን ደርሶ የበኩር ልጅዋን ኢየሱስ ክርስቶስ ወለደች፡፡ በእንግዳ ማደሪያ ሥፍራ ስላልተገኘ በከብቶች በረት ወልዳ በጨርቅ ጠቅላላ በግርግም ውስጥ አስተኛችው፡፡ በዚያ ሥፍራ ሌሊት መንጋቸውን እየጠበቁ በሜዳው የሚያድሩ እረኞች ነበሩ፡፡ እነርሱም የሚያንጸባርቅ ግርማውን ካዩ በኋላ በጣም ፈሩ፡፡ መልአኩ ግን ወዲያው “አይዞአችሁ አትፍሩ፣ አትደንግጡ፣ ለሁሉ ሕዝብ የሚሆን ታላቅ ዜና የምስራች ይዤላችሁ መጥቼአለሁ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ተወልዷል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ምልክቱ በጨርቅ የተጠቀለለ አንድ ሕፃን በግርግም ተኝቶ ታገኙታላችሁ” አላቸው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ከዚህ በኋላ መላእክት ከሰማይ መጥተው ከመላአኩ ጋር በመሆን “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፡፡ በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰላም ይሁን$ እያሉ በምስጋና ዘመሩ፡፡ መላእክት ተሰውረው ከሄዱ በኋላ እረኞቹ “እግዚአብሔር የገለጠልን ድንቅ ነገር ለማየት ወደ ቤተልሔም እንሂድ” (ሉቃ. 2፣1-20) ብለው ጉዞ ጀመሩ፡፡ እዚያ ከደረሱ በኋላ ቅዱስ ዮሴፍንና እመቤታችን ማርያምን በከብቶች በረት በግርግም ውስጥ ተኝቶ ከነበረው ሕፃን ጋር አገኙአቸው፡፡ ሕፃኑንም ግርማ ሞገሱ መልአኩ እንደነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ካዩት በኋላ ተደስተው ወደ መንጋቸው ተመለሱ፡፡

በጨለማ ይኖር የነበረ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፡፡ ሰው የአምላክን ትዕዛዝ አፍርሶ ከተከለከለው ፍሬ ቀንጥሶ ከበላ በኋላ መዓት ወደረበት፤ ለመከራ ተጋለጠ፤ በአምላክ ጥላቻና እርግማን ወደቀ፡፡ ኑሮው ደኀነት፣ ትግል፣ ስቃይ ብቻ ሆነ፡፡ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ከበበው፡፡ በቀን የፀሐይን ብርሃን እንደማያይ ዓይነ ሥውር ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ምንም እንኳን ያን ጊዜ እጅግ አዝኖና ተቆጥቶ ሰውን ከፊቱ በመከራና በድኀነት እንዲሰቃይ ቢተወውም መሐሪ ስለሆነ መከራውንና መጥፎ ሁኔታውን ተመልክቶ አሳዛኝ ኑሮውን አይቶ ራራለት፡፡

አስቀድሞ በደግነቱ ከኢምንት እንደፈጠረው እንዲሁም ደግሞ ፊቱን መልሶ በምሕረቱ በጣም ከሚያሳዝን የኃጢአትና የባርነት ከባድ ኑሮው ነጻ ሊያወጣውና ከወደቀበት ጉድጓድ አውጥቶ ከፍ ሊያደርገው ወሰነ፡፡ እንደገና በልጅ አድርጐ የዘለዓለማዊ ደስታው ተካፋይ እንዲሆን ጠራው፡፡ ሰው ለዚህ ከአምላክ በተሰጠው ተስፋ ተጽናንቶ በጨለማ ኑሮ ሲጋደል ሳለ የደኀንነት ብርሃን ጮራ ፈነጠቀለት፡፡ “በጨለማና በሞት ጥላ ይኖር የነበረ ሕዝብ ትልቅ ብርሃን አየ” (ኢሳ. 9፣3) ይላል ነቢዮ ኢሳይያስ፡፡ እግዚአብሔር ከረጅም ዘመናት በፊት ለሰው አሰምቶት የነበረውን አዳኝ ከሰማይ ላከለት፡፡ “ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር እነዚያን ከሕግ በታች የነበሩትን ለመዋጅት ከሴት የሚወለድ ሕግንም የሚከተል ልጁን ላከልን” (. ገላ. 4፣4) እያለ ቅዱስ ጳውሎስ ይናገራል፡፡

መልአኩ ለእረኞች “ታላቅ የምሥራች ዛሬ መድኃኒት ተወልዶላችኋል፤ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች አመጣሁላችሁ፡፡ በዳዊት ከተማ መድኃኒት ተወልዶላችኋል$ አላቸው፡፡ የክርስቶስ ልደት ፍጹም ደስ የሚያሰኝ ታላቅ የምሥራች ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ ዓለምን ሁሉ ሊያድን ነው የመጣው “ሕፃን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፡፡$ እያለ ነቢዩ ኢሳይያስ ከፍ ያለ ደስታውን አድናቆቱን ይገልጣል፡፡ (ኢሳ. 9፣7) “ቃል ሥጋ ኮነ ወኃደረ ላዕሌነ ቃል ሥጋ ለብሶ ሰው በመሆን በእኛ አደረ$ ይላል ቅዱስ ዮሐንስ፡፡

ከላይ በተገለጠው ሁኔታ ክርስቶስ የአዳምን ልጆች ከኃጢአት ኑሮና ከሰይጣን ባርነት ነጻ ሊያወጣቸው ከውድቀት ሊያነሣቸው ከስንት ዘመናት ጥላቻ በኋላ ከአምላካቸው ሊያስታርቃቸው በድንግል ማኀጸን በማደር የሰው ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር ወረደ፡፡ ሕፃን ሆኖ ከእነርሱ ጋር አንድ በመሆን ከሰው ልጆች እስከ ዕለተ ሞቱ በመስቀል ላይ የሕይወቱን ዘመን እንደማንኛውም ተራ ሠራተኛ ለመኖር ሥራ እየሠራ አሳለፍ፡፡ ለወንድሞቹ ለአዳም ልጆች የጨለማን የውድቀት ጊዜ አስወግዶ የብርሃን ተስፋ ከፈተላቸው፤ የስቃይና የኃዘን ዘመን ደምስሶ የደስታና የምቾት ዘመን እንዲያመጣላቸው ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ በዚህ የምሕረት ተግባር የመድኃኒታችንና የአምላካችን ደግነት ተገለጠ፡፡ “ባደረግነው የጽድቅ ፍሬና የግል ጥረት ሳይሆን በደግነቱና በምሕረቱ አዳነን” (ገላ. 3፣4 ) እያለ ቅዱስ ጳውሎስ ይናገራል፡፡

በትዕቢት የተኰነነው ሰው በአምላክ ልጅ ትሕትና ከወደቀበት ገደልና አዘቅት ወጥቶ ተነሣ፡፡ ምስኪን በዲያብሎስ ተታሎ በሞኝነት እከብራለሁ ብሎ ለውርደት የተዳረገው ሰው በአምላክ ልጅ ውርደት በበደሉ ያጠፋውን ክብር እንደገና አገኘ፡፡

ከመጀመሪያ ይበልጥ ከፍ አለ፤ በልዑላዊ ወንበር ከመላእክት ጐን ሊቀመጥ ቻለ፡፡ “ወልድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲያደርገን ሰው ሆነ” ይላል ቅዱስ ልዮነ፡፡ በኢየሱስ ልደት አምላክና ሰው ታርቀው ሰላም ያደረጉበት የተባረከና የተቀደሰ ቀን ነው፡፡ ኢየሱስ ተወልዶ ወደ ዓለም ሲመጣ በሰማይም በምድርም ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ “ለእግዚአብሔር በሰማይ ክብር ይሁን በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን$ እያሉ መላአክት ዘመሩ፡፡

በኢየሱስ ልደት እግዚአብሔር ከበረ ተመሰገነ፡፡ የፈለገው ካሣ እንደ መስዋዕት ቀረበለት፡፡ ሰው ደግሞ ከሰይጣንም ባርነት ነጻ ወጥቶ ሰላምን አገኘ፡፡ ዛሬ በቤተክርስቲያን በክርስቶስ ልደት ምክንያት ተደስተን እንገኛለን፡፡ የልደት በዓል ስናከብር፣

1ኛ. ሰላማችንና ደኀንነታችን የሆነው ሕፃን ማመስገን አለብን፣

2ኛ. ልደቱ የነፍሳችን ልደት የነፍሳችን መታደስ ሊሆን ያስፈልጋል፣

ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ የጨለማን ሥራ ትተን የብርሃን ጦር እንልበስ፡፡ እንድንለብሰው ክርስቶስ ያመጣልን ሰማያዊ መንፈስ መልበስ አለብን፡፡ ሕፃኑን ኢየሱስ ለምመስል መንገዱን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ “ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ መድኃኒነ ተወለደ ነዋ ይኤዜኒ ለሰላም ንትልዋ፡- አሁን አዳኛችን ተወልዶልናልና ሰላምን እንከተላት$ በዚህ በመለኮታዊ ሕፃን አማካይነት ሰላምና የአምላክ ደኀንነት መጣልን፡፡ የተገኘውን ሰማያዊ ሀብት በጥንቃቄ እንድንጠብቅ ግዴታ አለብን፣ ያስፈልጋልም፡፡ ምክንያቱም ዋጋው አለመጠን ውድ ነው፡፡ ይህን እንወቀው ለዚህ ዋስትና የሚሆን ይህን ሰማያዊ ሰላም እንድናጠፋ ከዚህ ከተባረከ መለኮታዊ ሕፃን አንራቅ ጠበቅ አድርገን እንከተለው፡፡

07 January 2021, 12:44