ፈልግ

የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክብረ በዓል በሮም ተከበረ የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክብረ በዓል በሮም ተከበረ 

የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክብረ በዓል በሮም ተከበረ

የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክብረ በዓል በጥር 09/2013 ዓ.ም በቅድስት መንበር በሚገኘው ጳጳሳዊ የኢትዮጲያ ኮሌጅ በደማቅ ስነ ሥርዓት ተከሮ ማለፉ ተገለጸ። በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በሥርዐተ ዋዜማ፣ በሥርዐተ ማኅሌት እና በመሥዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ውሏል። የዘንድሮው የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክብረ በዓል በቅድስት መንበር የሚገኘው ጳጳሳዊ የኢትዮጵያ ኮሌጅ 100ኛ ዓመት መዝጊያ ሆኖ በድርብ በዓል ተከብሯል። በወቅቱ የኮቪድ19 ወረርሺኝ ምክንያት ዘንድሮ እንደወትሮው በሮም የሚገኙ ገዳማት መነኮሳንና ካህናት እንዲሁም ምዕመናን መገኘት ባይችሉም በሮም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቆሞስ ክቡር አባ ተሻለ ንማኒ ቁምስናውንና ምዕመናንን በመወከል ከኮሌጁ ካህናት ጋር በመሆን መሥዋዕተ ቅዳሴውን አሳርገዋል። በመሥዋዕተ ቅዳሴው ላይ የዕለቱን ቃለ ምዕዳን ያሰሙት ክቡር አባ ቶማስ ቅዱስ እስጢፋኖስ ዘአቢሲኒያ ገዳም  ከ500 ዓመት ያላነሰ ዕድሜ እንዳለው አስታውሰው ነጋድያን ከሀገራችን ወደ ቅድስት ሀገር ያደርጉት የነበረ ሕያው የእምነት ምስክር ውጤት ነው ብለዋል።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት ማን ነው?

የዚህ ዕለት ስንክሳር (ስንክሳር መስከ 15) የቅዱስ እስጢፋኖስን ክብረ በዓል ያስታውሰናል፡፡ ቤተክርስቲያን ቅዱስ እስጢፋኖስን ከትላልቅ ቅዱሳን አንዱ አድርጋ ትቆጥረዋለች፡፡ ለታላላቅ ቅዱሳን የሚሰጠውንና የሚገባውን ክብር ትሰጠዋለች፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ የሰማዕታት ሁሉ በኩር ከሁሉም በፊት ስለ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ቅዱስና ቀዳሜ ሰማዕት ምን ተጋድሎ እንዳደረገ የሐዋርያትን ሥራ (.የሐዋ. 7፣ 57- 59) እናንብብ፡፡ በኢየሩሳሌም የምእመናን ቁጥር እየበዛ በሄደ መጠን ችግርና አለመግባባት ደግሞ እየተስፋፋ ይሄድ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ግን ክርስቲያኖች ሁሉም አንድ መንፈስና አንድ ልብ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ ምግባቸው፣ ልብሳቸው፣ ሁሉም በኀብረትና በጋራ ነበር፡፡

የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ከሌሎች ቦታዎች ከመጡ ክርስቲያኖች በቁጥር ይበዙ ስለነበር፡፡ በምጽዋት እደላ ጊዜ ምግብ አንሶ ሚስቶቻቸው ተሰልፈው ሲጠብቁ ኋላ የቀሩት ያጉረመርሙ ጀመር፡፡ ሐዋርያት ይህንን አውቀው ክርስቲያኖችን በሙሉ ሰብስበው «የእግዚአብሔርን ቃል ትተን በምግብ እደላ ብቻ መጠመድ አይገባንም፡፡ ስለዚህ የምግቡን እደላ አደራ የምንሰጣቸው መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሞላባቸው ሰባት ሰዎች ከእናንተ መካከል ምረጡ (የሐዋ. 6፣8) አሏቸው፡፡ ክርስቲያኖቹም የሐዋርያት ሐሳብና ንግግር መልካም ሆኖ ስለታያቸው ሃይማኖትና መንፈስ ቅዱስ የሞላበትን «እስጢፋኖስ የተባለውን ሰውና ሌሎችንም መረጡ (የሐዋ. 6፣5)፡፡

እኛስ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሃይማኖትና ጸጋ የሞላብን ሰዎች ነን ወይ; በጥምቀት የተቀበልነው ሃይማኖት በምን ላይ ይገኛል; እስቲ አስተውለን እንመርምር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእኛ እንዴት ሆኖ ይኖራል? በእኛ ተደስቷል ወይ?

ቅዱስ እስጢፋኖስ ኃላፊነት ከተሸከመ በኋላ በአረማመዱና በተቀደሰ ሕይወቱ ለሁሉም ድንቅ ምልክቶችን ያደርግና ያሳይ ነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱ አንዳንድ ቅናተኞች አይሁዳውያን ሊቃወሙት ተነሱ፡፡ ነገር ግን በጥበብና መንፈስ ቅዱስ በተሞላበት ንግግሩ ተሸነፉ፣ ከተሸነፉም በኋላ ወደ ውሸት፣ አመጽና ኃይልን ወደመጠቀም ተሯሯጡ፡፡ በኃይልና በጉልበት ይዘውት ወስደው በፍርድ ሸንጐ ፊት አቆሙት፣ «በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተናል፤ የሚሉ ሰዎችን አስነሱበት(የሐዋ. 6፣11) ከመሬት ተነስተው በሐሰት ከሰሱት፡፡ በዚህም ላይ «ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም (የሐዋ. 6፣13) የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙበት፡፡ ሊቀ ካህናቱም «ይህ ነገር እውነት ነውን፣ (ዋ. 7፣1) ሲል ጠየቀው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስም ረጋ ባለ መንፈስ «ወንድሞቾና እህቶቼ ሆይ! ስሙ፣ የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ታየው … (የሐዋ. 7፣2-50) እያለ የአባቶቻቸውን ረጅም ታሪክ አስረዳቸው፡፡

እንዲሁም አንዳንዶች ያደረጉአቸውን እኩይ ተግባሮችን ዘረዘረላቸውና እነርሱም ይከተሉት እንደነበር ገለጠላቸው፡፡ እንደ አባቶቻቸው እግዚአብሔርን ብዙ ጊዜ እንደከዱት፣ ነቢያትንም በክፉ አቀባበል አሳደው እንደገደሉአቸው አስታወሳቸው፡፡ «እናነት አንገተ ደንዳኖች፣ ልባችሁና ጆሮአችሁ በክፋት የተሞላ በመሆኑ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፣ … ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ; (የሐዋ. 51፣58) እያለ ገሰጻቸው፡፡

አይሁዳውያኑ ይህንን በሰሙ ጊዜ በጣም ተቆጡና ጥርሳቸውንም አፋጩበት፣ እኛም ልክ እንደዚሁ ለጥቅማችን ብሎ ስህተታችንን፣ ጥፋታችንን የሚገልጽልንን እንድንታረምበት የሚመክረንን ሰው እንጠላዋለን፣ እናዋርደዋለን፡፡ ይህም ክፋታችንና ጥፋታችን እንዲገለጥ እንደማንፈልግ ማስረጃ ነው፡፡ ከእኩይ ሥራችን እንድንላቀቅ አንፈልግም፣ የከፋና የባሰ ኃጢአት ደግሞ ይህ ነው፡፡

ቅዱስ እስጢፋኖስ በፍርድ ፊት ቆሞ ሳለ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ከተመለከተ በኋላ የእግዚአብሔርን ክብር አየ፣ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ አየው፡፡ «እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” (የሐዋ. 7፣56) አለ፡፡ ይህን ከተናገረ በኋላ አይሁዳውያን በታላቅ ድምጽ ጮኸው ወደ እርሱ ሮጡ፤ እጅግ ተቆጥተውም አደጋ ጣሉበት፤ ከከተማ ወደ ውጭ አውጥው በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡

ቅዱስ እስጢፋናስ ከመሞቱ በፊት «ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት፣ …. ይህን ኃጢያት አትቁጠርባቸው (የሐዋ. 7፣ 50-60) እያለ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፣ ይህንንም ብሎ በሰማዕትነት ደሙን አፍስሶ ሞተ፡፡ ሕይወቱን ሰጠ፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለ ሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ (ማቴ. 5፣ 44-45) ያለውን በተግባር የተረጐመና የፈጸመ ቅዱስ ነው፡፡ ጌታውንና ባልንጀራውን አፍቅሮ ትዕዛዙን ፈጽሞ አረፈ፡፡

እኛ ደግሞ «ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ ጠላትህና ጥላ የሚለውን የዓለም ትምህርትና አስተሳሰብ ትተን እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ የማይወዱንንና የሚያሰቃዩንን፣ የሚያዋርዱንን ሰዎች በጥሩ አመለካከት እንቅረባቸው ቂምና ጥላቻን አስወግደን በሥራችን ፍቅራችንን እንግለጽላቸው፡፡

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከሁሉ አስቀድሞ ለክርስቶስ የላቀ የፍቅር ምልክት ገለጸለት፡፡ ስለ እርሱ ብሎ ደሙን አፈሰሰ፡፡ እኛ ግን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን እያልን ስለ እሱ ደማችንን ማፍሰስ ይቅርና ፈተናና ሥቃይ መቀበልን እምቢ እንላለን፡፡ እርሱን መከተል መከራን ሲያመጣብን አስወግደን እንሸሻለን፡፡ ይህን የድክመት መንፈሳችንን ትተት የቅዱስ እስጢፋኖስን ጽኑ እምነትና የመንፈስ ቅዱስን ብርታት የተሞላበትን መንፈስ እንልበስ።

17 January 2021, 13:45