ፈልግ

ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ  

የኢየሱስ ጥምቀት

ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ አይሁዳውያንን ሲያጠምቅ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተራ ሰው መስሎ መጣ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ገርሞት “እኔ ነኝ በአንተ ልጠመቅ የሚገባኝ እንጂ አንተ እንዴት ወደ እኔ ትመጣለህ” (ማቴ. 3፣14-15) በማለት ማጥመቁን እምቢ አለ፡፡ ኢየሱስ ግን “አሁንስ ተው አትከልክለኝ የምጠይቅህን ጥምቀት ስጠኝ፡፡ ምክንያቱም ሕግን ሁሉ መፈጸም ተገቢ ነው”። ሲለው የጥምቀት ውኃ በራሱ አፈሰሰበት፡፡ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው በራሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ ሰማይም ተከፈተ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” (ማቴ. 3፣17) የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ኢየሱስ የተጠመቀው ግዳጅ ስለነበረበት አይደለም፡፡ ሕግን ሁሉ መፈጸም እንዳለበት በተለይ ደግሞ ምስጢረ ጥምቀት ለደኀንነታችን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ሊያስተምር ፈልጐ ነው፡፡ ሊየሱስ ለኒቆዲሞስ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደገና ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም፣ ሲል ተናገረው (ዮሐ. 3፣5) እንዲሁም “ወደ ዓለም ሙሉ ሄዳችሁ ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ ስበኩ፣ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁቸው፡፡ ያመነና የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል” (ማር. 16፣16) እያለ ደቀ መዛሙርቱን ላካቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከዮርዳኖስ ወንዝ ሳይወጣ እዚያው ቆሞ እያለ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ “በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” እያለ እግዚአብሔር አብ ተናገረ፡፡ ይህ ጥምቀት በሚቀበል በእያንዳንዱ ሰው ይደገማል፡፡ እኛ ጥምቀትን ስንቀበል መንፈስ ቅዱስ በማይታይ ሁኔታ በእኛ ላይ ይወርዳል፡፡ እግዚአብሔር ያን ጊዜ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” እያለ ተደስቶ ይቀበለናል፣ የላቀና የጠለቀ ደስታውን ይገልጣል፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያደርገናል፣ በጥምቀት ጸጋ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከባርነት ወደ ነጻነትና ጽድቅ እንሻገራለን፣ የቅድስት ሥላሴ ማደሪያና ምድራዊ መኖሪያ እንሆናለን፡፡ ጥምቀት ስንት መንፈሳዊ ሀብትና ጸጋ እንዲሁም ከፍ ያለ የእግዚአብሔር ልጆች ክብር ይሰጠናል።

ነገር ግን ምድራዊ ሀብት ጠንቀቅ ብለን ካልጠበቅነው ሊጠፋና ሳንጠቀምነበት ሊቀር እንደሚችል እንዲሁም የጥምቀት መንፈሳዊ ሀብት ተግተንና ነቅተን ካልሰራንበት ጥቅም ሳይሰጠን ባክኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ጥምቀት ስለተቀበልን ድነናል ብቁዎችን ሆነናል መንግሥተ ሰማያትን ወርሰናል ማለት አይደለንም፡፡ ደኀንነታችን ፍጹም እንዲሆን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ በበኩላችን ደካማ አቅማችን በሚፈቅደው ያለሰለሰ ጥረትና ትግል ማድረግ አለብን፣ የደኀንነታችን መሠረት ልንቀጥለውና መልካም ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ ልናሳድገው እንዲሁም ግራና ቀኝ ሳንል በደኀንነት ጐዳና እንድንጓዝ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ ጥምቀት ተቀብለናል፣ ተጠምቀናል፣ ይበቃናል፣ አሁንስ ለዘለዓለም ድነናል ብለን ከመንፈሳዊ ጥረት ውጊያ ተግባር ማረፍና ማቋረጥ አይገባንም፡፡ በጥምቀት ጸጋ ተመርተን እንድንሄድና ኑሮአችን የሕይወታችን አረማመድ ከመንፈስ ጥምቀት እንዲስማማ ማድረግ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “እምነት ያለሥራ የሞተ ነው” (ያዕ. 2፣26) አያለ ያስጠነቅቀናል።

ቤተክርስቲያን ስንጠመቅ “በዘለዓለም ሕይወት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ ከፈለግህ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ጠብቅ፣ እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ ውደድ፣ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ፤ ሰይጣንና ሥራውን ሁሉ ካድ በኢየሱስ እመን$ እያለች ታስጠነቅቀናለች፡፡ እኛም ደግሞ እክዳለሁ … አምናለሁ …$እያልን እንመልስላታለን፡፡ እንግዲህ ቃላችንን እንጠብቅ፣ መሐላችንንና እምነታችንን ፍሬ አፍርተን በተግባር እናሳይ፡፡ በየዓመቱ የኢየሱስን የጥምቀት ቀን በማስታወስ መንፈሳችንን እናድስ፡፡ ያን የጥምቀት ጸጋ በበለጠ ጥረት ኰትኩተን እናዳብረው፡፡

18 January 2021, 13:34