ፈልግ

በኦሽዊትዝ የሚገኝ ማጎሪያ ካምፕ በኦሽዊትዝ የሚገኝ ማጎሪያ ካምፕ 

ልዩነትን በማስወገድ የመቀራረብ ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ቀረበ

በርካታ አይሁዳዊያን በግፍ የተጨፈጨፉበት ቀን በሚታወስበት ጥር 19 ቀን በጣሊያን የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት እና የአገሪቱ ዜጎች በሙሉ እየተስፋፋ ያለውን አመጽ የታከለበት የፀረ-ሴማዊነት እና የዘረኝነት መንፈስን አጥብቀው እንዲቃወሙት፣ ዋና ጽሕፈት ቤቱ በሮም የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ አሳሰበ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ፣ ጣሊያንን ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የአመጽ፣ የልዩነት፣ የብሔረተኝነት፣ የበላይነት እና የተወለዱበትን አገር መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ስሜቶች እያደጉ መምጣታቸውን አስታውቋል። በማከልም በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በነበሩ አይሁዳዊያን ላይ የደረሰውን የጭፍጨፋ ተግባር ከመላው ዓለም ጋር በሐዘን በማስታወስ የተሰማውንም ፍርሃት እና ጭንቀት ገልጿል። ማኅበሩ ጥር 19/2013 ዓ. ም. በጻፈው መልዕክቱ በሕዝባዊ ውይይቶች መካከል ታሪክን እና ባሕላዊ እሴቶችን የሚገልጹ ጥናታዊ ምርምሮች ይፋ እንዲሆኑ አሳስቦ፣ ዛሬ ስለደረሱበት ማኅበራዊ ሕይወት ማወቅ የሚቻለው ያለፈውን ታሪክ በጥልቀት ስናውቅ ነው በማለት አስረድቷል።  

በአይሁዳዊያን ላይ የደረሰውን የጥፋት መጠን ማስታወሱ እርስ በእርስ በመረዳዳት ለመኖር፣ በእንግድነት ለመቀባበል እና ለማኅበራዊ ሕይወት ዝግጁዎች ለመሆን እንደሚረዳ ማኅበሩ አስረድቷል። እያሳሰበ የመጣውን እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት የሚገለጸውን የጥላቻ መልዕክቶችን እና ስሜቶችን በመቃወም እና በማውገዝ፣ ወጣቶችም ከቀድሞ አባቶች ለወረሷቸው መልካም እሴቶች ምስክርነትን በመስጠት በአዲሱ ትውልድ መካከል መልካም ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ በተለያዩ ደረጃዎች ለሚገኝ ወጣት ማኅበረሰብ ከሰላም ማስተማር ተግባር ጀምሮ የእርስ በእርስ ግንኙነት እና የትውውቅ ባሕል እንዲያድግ በማድረግ፣ ወጣቶች በመካከላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካም ተግባራትን በመፈጸም ማንኛውንም ዓይነት የፀረ-ሴማዊነት እና የዘረኝነት መንፈስን አጥብቀው እንዲቃወሙት ማድረግ መሆኑን አስታውቋል።    

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን አሳዛኝ ሁኔታ በማስመልከት ባስተላለፈው መልዕክቱ፣ ወረርሽኙ ከዚህ በፊትም ሆነ ዛሬ በሕዝቦች መካከል ፍርሃት እና ልዩነት እንዲኖር ካደረጉት ከሀገር፣ ከጎሳ እና ከሃይማኖት ልዩነቶች ባሻገር የሰው ልጅ የጋራ ዕጣ ፈንታ ያለው መሆኑን አስታውሶናል ብሏል። በመሆኑም የአውሽዊትዝ የጥፋት ካምፖች ጥልቅ ትዝታ፣ ያለፈውን ታሪክ ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነ አስረድቷል። የናዚዎችን የጥፋት እና የስቃይ ወቅትን መቋቋም የቻለች፣ ኤዲት ብሩክ በጽሑፏ እንዳስገነዘበችው “ፀረ-ሴማዊንት ዛሬም ቢሆን በአውሮፓ ውስጥ የሚገኝ አዲስ ጥቁር አሻራ ነው” ማለቷ ታውቋል። ባለፈውን የፀረ-ሴማዊነት እና የዘረኝነት ታሪክ ላይ ማስተንተኑ፣ በከፍተኛ ለውጥ ሂደት ውስጥ በሚገኝ ዓለማችን የሚታዩ የዛሬ ችግሮች ነገ በምናያቸው መልካም ገጽታዎች የሚተኩ መሆናቸውን ማኅበሩ አስረድቶ፣ ከሁሉም በላይ ሰብዓዊ ቤተሰብን፣ ምኞቱን እና ክብሩን ማስቀደም እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

28 January 2021, 11:52