ፈልግ

በኢራቅ፣ ሞሱል ከተማ አንድ ክርስቲያን አባት ከሕጻን ልጁ ጋር በኢራቅ፣ ሞሱል ከተማ አንድ ክርስቲያን አባት ከሕጻን ልጁ ጋር  

የኢራቅ ምዕመናን፣ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሳካት እንዲጸልዩ ጥሪ ቀረበ

ምሥራቃዊ ስርዓተ አምልኮን የምትከተል የባቢሎን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሳካ እንዲሆን በመላው አገሪቱ የሚገኙ ምዕመናን ከጥር 9/2013 ዓ. ም. ጀምረው ጸሎት እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የጋራ ውይይትን እና ሰላምን የሚያወርድ ፍሬያማ ጉብኝት እንዲሆን መላው የአገሪቱ ሕዝብ የሚተባበር መሆኑ ታውቋል። የመካከልኛው ምሥራቅ አገር የሆነችው ኢራቅ ባሁኑ ጊዜ ጎረቤት አገር ከሆነች ሶርያ ጋር በድንበር አካባቢ ግጭት መኖሩ የሚስተዋል ሲሆን፣ እስላማዊ መንግሥት በሚቆጣጠረው የሞሱል ግዛት ከ2014-2017 ዓ. ም. (እ.አ.አ) ድረስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው እና የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸው መጠነ ሰፊ አመጽ ሲካሄድ መቆየቱን ያመለክታል ተብሏል።

“ከዓመታት ጀምሮ የመከራን ሕይወት ኖረናል” ያሉት ብጹዕ ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ባወቁ ጊዜ እንደተናገሩት፣ ቅዱስነታቸው አገሪቱ ዳግም በመወለድ “አዲስ ብርሃነ ልደቱን” እንድታከብር ለማድረግ አደራ የተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል። ይህን ሃሳብ መሠረት በማድረግ፣ በባቢሎን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ፣ በኢራቅ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ከጥር 9/2013 ዓ. ም. ጀምሮ በየእሑዱ በሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚደገም የሚከተለውን ጸሎት በማዘጋጀት ምዕመናኑ እንዲጸልዩ ጠይቀዋል።

"ጌታ አምላካችን ሆይ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጤና በመስጠት በኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በፍሬያማነት እንዲፈጽሙ እርዳቸው። በኢራቅ ውስጥ የጋራ ውይይት እንዲኖር እና ወንድማዊ እርቅ እንዲገኝ፣ በሕዝቡ መካከል መተማመን እንዲመጣ፣ በተለይ በኢራቅ ሕዝብ መካከል የሰላም እሴቶች እና ሰብዓዊ ክብር እንዲጠናከር፣ የአሳዛኝ ክስተቶች ምስክሮች እንድንሆን ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረቶች በሙሉ አንተ ባርካቸው"።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት አደራን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመስጠትም፥

"ፈጥሪያችን ሆይ! በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር ማየት እንድንችል የልባችንን ብርሃን አብራልን። ለዜጎቻችን እና ለአገራችን የተሻለ ዘመን እንዲመጣ፣ በአገራችን ውስጥ ሙሉ አንድነት እንዲመጣ፣ ወንድማዊ መረዳዳት እንዲኖር ጸጋህን አብራልን"።

በጎርጎሮሳዊያኑ ታኅሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ለኢራቅ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማስተናገድ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን “ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሌላ ሳይሆን በአስቸጋሪ እና እርግጠኞች ባልሆንንበት በዚህ ጊዜ መጽናናትን የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጉብኝት ነው” ማለታቸው ይታወሳል። አክለውም “የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝትን በታላቅ እምነት የምንቀበለው፣ በእኛ ውስጥ ያለው እምነት እና ተስፋ በተግባር እንዲታይ የምናደርግበት አጋጣሚ ነው” ማለታቸው ይታወሳ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እንዲያደርጉ ከአገሪቱ ባለስልጣናት እና ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል ግብዣ መቅረቡ ይፋ የሆነው ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ ታኅሳስ ወር ቢሆንም፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቅዱስነታቸው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለአሥራ አምስት ወራት ያህል አቋርጠው መቆየታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ ውስጥ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ባግዳድን፣ ኡርን፣ ኤርቢልን እና በነነዌ ክፍለ ሀገር የሚገኘውን ቃራቆሽ ከተማን የሚጎበኙ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ኢራቅን ለመጎብኘት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ምኞት እንደነበራቸው ሲታወቅ፣ እ.አ.አ ከ 2019 ጀምሮ በሚያስተላልፉት መልዕክታቸውም፣ በአገሪቱ ውስጥ ለጋራ ጥቅም ቅድሚያን የሚሰጥ ጠንካራ ማህበራዊ መሠረትን እንደገና እንዲገነባ በተደጋጋሚ መልዕክት ሲያስተላልፉ መቆየታቸው ይታወሳል።

16 January 2021, 16:01