ፈልግ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ 2020 ዓ.ም ተጠናቆ 2021 ዓ.ም ዛሬ በታኅሳስ 23/2013 ዓ.ም መጀምሩ ይታወሳል። በእዚህ እለት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ አባላት ዘንድ አዲስ አመት እየተከበረ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ይህንን የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት” ዓመታዊ በዓል እየተከበረ ይገኛል። 

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

እመቤታችን እጅግ ቅድስት  ድንግል ማርያም  “የአምላክ እናት ናት” የተባለው  የእምነት  እውነት  ካቶሊካዊት  ቤተክርስቲያን  ስለ እመቤታችን  እጅግ  ቅድስት  ድንግል  ማርያም  ማንነት በይፋ  ያወጀችው  የመጀመሪያው  የእምነት  እውነት  ነው። "ማርያም፡ የአምላክ  እናት" በመባል  ለመጀመሪያ  ጊዜ  የተጠራችው  እ.አ.አ. በ250 ዓ.ም. አከባቢ  ሲሆን፣ "በጥበቃሽ ሥር እንጠለላለን" በሚለው  ጸሎት አማካይነት  ነበር እምነቱ የተገለጸው። እመቤታችን  እጅግ  ቅድስት  ድንግል  ማርያም  የአምላክ  እናት  ናት" የተባለውን  የእምነት  እውነት  እናታችን  ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን  ስለ እመቤታችን  እጅግ  ቅድስት  ድንግል  ማርያም  በይፋ ያወጀችው  የመጀመሪያው  የእምነት  እውነት  ሲሆን  ይህም  የታወጀው  በኤፌሶን  ጉባኤ እ.አ.አ. በ431.ዓ.ም. ነበር።

ኔስቶርዮስ (እ.አ.አ. ከ381-451 የኖረ) እ.አ.አ. ከ428.ዓ.ም. ጀምሮ የኮንስታንትኖፕል ፓትሪያርክ ነበር። እርሱም ማርያም የአምላክ እናት ተብላ መጠራት በጭራሽ አትችልም እያለ ያስተምር ነበር። በርሱ አመለካከት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የወለደችው ሰው የሆነውን ኢየሱስ ብቻ ስለሆነ፣ "የክርስቶስ እናት" ተብላ መጠራት ብቻ ነው የምትችለው ይል ነበር። በዚህ ዐይነት በግብፃዊው ቅዱስ ቄርሎስና  (እ.አ.አ. ከ385-444 የኖረ) በኔስቶርዮስ መካከል ከፍተኛ የአመለካከት ግጭት ተፈጠረ።

ስለሆነም ቄርሎስ ኔስቶርዮስን በጽሑፉ በኃይል አወገዘው። ጉዳዩንም ለግብፅ ጳጳሳትና መነኮሳት በፋሲካ በዓል እ.አ.አ. በ429 ዓ.ም. በይፋ አመለከተ። የርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ሰሌስቲኖስ ቀዳማዊን (422-432) ሙሉ ድጋፍ ስላገኘ ቅዱስ ቄርሎስ 12 ውግዘቶችን በመጻፍ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስም ለነስቶሪዮስ በመላክ ከስሕተቱ እንዲታረም በጥብቅ አሳሰበው። ኔስቶሪዮስ በበኩሉ ደግሞ 12 ተቃዋሚ ውግዘቶችን በመጻፍ የምሥራቅ ንጉሠ ነገሥት የነበረው የዳግማዊ ቴኦዶሲዮስን (እ.አ.አ. ከ 408 እስከ 450 ዓ.ም. የነገሠ) ድጋፍ ከማግኘቱም በላይ  በርሱም  አማካይነት የምዕራብ  ንጉሥ  ነገሥት የነበረውን ቫሌንቲኒያን ዳግማዊን (እ.አ.አ. ከ425 ዓ.ም. እስከ 455 ዓ. ም. የነገሠ) በማስተባበር ስለ ጉዳዩ የቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጉባኤ እንዲጠራ አደረገ። የካቶሊክ ቤተክርቲያን ጠቅላይ ጉባኤዎች 3ኛው የነበረው የኤፌሶን ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው እ.አ.አ. በሰኔ 22 ቀን በ431 ዓ.ም. በበዓለ ኀምሳ በዓል አጋጣሚ ነበር። በዕለቱም ፓትሪያርክ ኔስቶርዮስና ተከታዮቹ አልተገኙም ነበር። በጉባኤው በነበሩት በ198 ጳጳሳት ፊት ኔስቶሪዮስን በመቃወም ቅዱስ ቄርሎስ የጻፈው የውግዘት ሰነድ ተነበበ። ጳጳሳቱም በሙሉ ድምፅ ሰነዱን አጸደቁ። የነስቶሪዮስንም ውግዘት ያለ ምንም ተቃውሞ ተቀበሉ።

በዚህ ዐይነት በኤፌሶን ጉባኤ እመቤታችን  እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም "የአምላክ እናት ናት" የተባለው የእምነት እውነት በይፋ ታወጀ። የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን መለኮታዊ እናትነት የሚደግፈው የመጀመሪያው የወንጌል ጥቅስ የተወሰደው ከወንጌላዊው ዮሐንስ ሲሆን እንዲህ ይላል፣ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ” (ዮሐ. 1፡14 ተመልከት)። ወንጌላዊው ሉቃስ በበኩሉ ደግሞ ጉዳዩን በተመለከተ እንዲህ ይላል፣ "መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የልዑልም ኃይል በጥላው ይጋርድሻል ስለዚህ ደግሞ ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል”(ሉቃ.1፡35 ተመልከት)።

የአሕዛብ ብርሃን የሚባለው ትልቁ የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ሰነድ በበኩሉ ደግሞ በ8ኛው ምዕራፉ ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መለኮታዊ እናትነት እንደሚከተለው ይገልጻል፣ “ድንግል ማርያም በመልአኩ ብሥራት የእግዚአብሔርን ቃል በልቡዋና በሰውነቷ በመቀበል ለዓለም ሕይወት ስጥታለች፤ በእርግጥም የአምላክ እናትና የመድኃኔዓለም እናት መሆንዋ ተቀባይነት አለው፤ ክብርም ይገባታል።” ይህም የእምነት እውነት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት መካከል ስላለው ጥብቅ ግንኙነት ከታወጀው የእምነት እውነት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።

01 January 2021, 14:14