ፈልግ

ብጹዕ ፓትሪያርክ ቤካራ ራይ፤ ብጹዕ ፓትሪያርክ ቤካራ ራይ፤ 

የሊባኖስ ፖለቲከኞች ወደ ጋራ መግባባት ደርሰው አገሪቱን ከውድቀት እንዲታደጓት ጥሪ ቀረበ

የምስራቅ ስርዓት በምትከተል የሊባኖስ ማሮናይት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤካራ ራይ ለአገራቸው የፖለቲካ መሪዎች ባቀረቡት ጥሪ፣ የፓርቲ ፍላጎቶችን ወደ ጎን በማለት ብሔራዊ ፍላጎትን እውነተኛ መንግሥት እንዲመሰርቱ እና አገሪቱን ከጠቅላላ ውድቀት እንዲታደጓት አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ፓትሪያርክ ቤካራ ራይ ጥሪያቸውን ያቀረቡት በሊባኖስ የሚታየው የፖለቲካ ልዩነት አዲስ ለሚመሠረተው መንግሥት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን በመረዳት መሆኑ ታውቋል። መንግሥትን ለውድቀት በመዳረግ ኃላፊነትን መሸሽ አይረዳም ያሉት ፓትሪያርክ ራይ፣ መፍትሄው አገሪቱን ያጋጠማት አደጋ በጋራ ክንድ መመከት እንደሆነ ከቤይሩት በ22 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ በብኬርኬ የማሮናይት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

ቤሩት ከውድቀት መታደግ

የአገሪቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሚሼል ኦውን እና አገሪቱን ለሦስት ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ክቡር አቶ ሳድ ሐሪሪ፣ በመካከላቸው የሚታየውን የፖለቲካ ልዩነት እና ውጥረት አስወግደው ወደ ስምምነት መድረስ እንደሚቻል የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ቤካራ፣ ሁለቱ ከፍተኛ መሪዎች የግል ፖለቲካ ፍላጎት ከማራመድ ይልቅ የሊባኖስን ሕዝብ ፍላጎት ማስቀደም እንዳለባቸው አሳስበዋል። ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በአገሪቱ ሊካሄድ የታቀደው የመንግሥት ምስረታ መዘግየቱ እንዳሳዘናቸውም ገልጸዋል።

ስድስት ሚሊዮን ዜጎች ያሏት እና ባሁኑ ጊዜ ጠንካራ መንግሥት የሌላት ሊባኖስ፣ እ.አ.አ. ነሐሴ 4/2020 ባጋጠማት የቤይሩት ከተማ ባሕር ዳርቻ ፍንዳታ ምክንያት ወደ 200 በሚጠጉ ሰዎች ላይ የሞት አደጋ መድረሱ፣ በ5000 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱ እና በመዲናይቱ ትላልቅ ክፍሎች ውድመት መድረሱ የሚታወስ ነው።

የገንዘብ ቀውስ እና ድህነት

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስቀድሞም ቢሆን ሊባኖስ ረጅም ዓመታትን በዘለቀ የኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ የአሁኑ ግን አገሪቱ እ.አ.አ. ከ1975-1990 ከገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት ጊዜ ቀውስ እጅግ የከፋ ነው ተብሏል። ለሊባኖስ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ዋና ምክንያቱ በአገሪቱ የተስፋፋው ሙስና በአስራ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለድህነት መዳረጉ እና በዚህ ምክንያት ትላልቅ ጸረ-መንግሥት ሰልፎች ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል። የአገሪቱ የገንዘብ ምንዛሪ መቀነሱ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ ታውቋል። የሊባኖስ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሚሼል ኦውን፣ አገሪቱን ለሦስት ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉትን ክቡር አቶ ሳድ ሐሪሪን የካቢኔያቸው አባል ቢያደርጉም ነገር ግን በፓርቲዎቹ መካከል አሁንም አለመግባባት መኖሩ በአዲሱ የጎርጎሮሳዊያኑ ዓመት 2021 ዓ. ም. ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ለከፍተኛ ድህነት እንደሚጋያልጥ እና የማዕከላዊ ባንክ ክምችትም እንደሚቀንስ የዓለም ባንክ አስጠንቅቋል።

"ሊባኖስ ወደ ጠቅላላ ውድቀት እና ኪሳራ"

ብጹዕ ፓትሪያርክ ቤካራ ራይ በጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለፖለቲካ መሪዎች ባቀረቡት የወቀሳ መልዕክታቸው “አገሪቱ መንግሥት ሳትመሠርት አዲስ ዓመት መጀመሩ አሳፋሪ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። ፓትሪያርክ ቤካራ ራይ በመልዕክታቸው፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ፖለቲካ ሂደት ውስጥ የሃያላን መንግሥታት እጅ ጣልቃ መግባቱን ገልጸው፣ ማንም ቢሆን መንግሥት ከመመስረት ሊያግድ፣ የአገሪቱን የቅርብ እና የሩቅ ጊዜ ፍላጎትን እና ዕድልን መወሰን ሊከለክል አይችልም ብለዋል። አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሪሪ ከሁለት ወራት በፊት አዲስ መንግሥት እንዲመሰርቱ ሃላፊነት ቢሰጣቸውም ተግባራዊ አለማድረጋቸውን ገልጸው፣ በዚህም ምክንያት ሊባኖስ በፍጥነት ወደ ጠቅላላ ውድቀት እና ኪሳራ በማምራት ላይ መሆኗን አስታውቀዋል።   

05 January 2021, 14:02