ፈልግ

በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የተከበረው የጥምቀት በዓል ሥነ-ሥርዓት በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የተከበረው የጥምቀት በዓል ሥነ-ሥርዓት  

በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የመጀመሪያው መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ

ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥመቁ ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፣ የብርሃነ ጥምቀቱ በዓል በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት መፈጸሙን ከሥፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል። ከመጥመቁ ቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ቤት በጥቂት ሜትሮች ርቀት በሚገኝ ሥፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩት፣ በቅድስት አገር የሚገኝ ፍራንችስካዊያን ማኅበር አለቃ የሆኑት ክቡር አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ እና በዮርዳኖስ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኝ ይህ ሥፍራ እ.አ.አ በ1967 ዓ. ም. በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የማዕድን ማውጫ እና ወታደራዊ ቀጠና በመሆኑ ከጥቅም ውጭ ሆኖ መቆየቱ ታውቋል። በአካባቢው የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ያላቸው አብያት ክርስቲያናት ስምንት ሲሆኑ እነዚህም በቅድስት አገር የሚገኙ መንፈሳዊ ሥፍራዎችን የምትንክባከብ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የአርመን፣ የኮፕት፣ የኢትዮጵያ፣ የሮማኒያ፣ የሶርያ እና የሩሲያ አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸው ታውቋል።

አካባቢው እድሳት ተደርጎለታል

“ቃስር ኣል ያሁድ” ተብሎ የሚጠራው ይህ ሥፍራ፣ የአይሁድ ቤተመንግሥት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን እስራኤላዊያን ወደ ቃል ኪዳን ምድር በደረሱ ጊዜ የተሻገሩት የዮርዳኖስ ወንዝ የሚገኝበት ሥፍራ መሆኑ ታውቋል (ኢያሱ 3:14-17)። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 2000 ዓ. ም. ወደ ቅድስት አገር ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በእስራኤል ባለስልጣናት ፈቃድ መሠረት መጠነኛ እድሳት የተደረገለት ሲሆን እ.አ.አ 2011 ዓ. ም. ለመንፈሳዊ ተጓዦች ለአጭር ጊዜ ክፍት ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል። እ.አ.አ 2018 ዓ. ም “ሃሎ ትረስት” የተባለ አንድ የእንግሊዝ ድርጅት፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እ.አ.አ በ1935 ዓ. ም. የገነባችው የመጥመቁ ቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ቤት አካባቢን ከፈንጂ ነጻ ማድረጉ ይታወሳል። አካባቢው ተገቢ እድሳት ከተደረገለት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፣ እሑድ ጥር 2/2013 ዓ. ም. የብርሃነ ጥምቀቱ ክብረ በዓል መከበሩ ታውቋል።

አዲስ ምዕራፍ ነው

ሥፍራውን በማስመልከት በዕለቱ ስብከታቸው ያሰሙት፣ በቅድስት አገር የሚገኝ ፍራንችስካዊያን ማኅበር አለቃ የሆኑት ክቡር አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን፣ እ.አ.አ ጥር 7/1967 ዓ. ም. ሁለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህናት ለመጨረሻ ጊዜ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መፈጸማቸውን እ.አ.አ በነሐሴ 9/2018 ዓ. ም. ወደ ጸሎት ቤቱ ያመሩት ክቡር አባ ሰርጌይ ከመዝገብ ውስጥ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ክቡር አባ ፍራንችስኮስ በስብከታቸው ወቅት እንደተናገሩት “ከ54 ዓመታት እና ሦስት ቀናት በኋላ፣ የጦርነት ቀጣና እና በፈንጂ የታጠረ አደገኛ ሥፍራ የነበረው ወደ ሰላማዊ የጸሎት ሥፍራ መለወጡን በጸሎት ቤቱ መዝገብ ውስጥ አዲስ ገጽ ላይ ጽፈን እናስቀምጣለን” ብለዋል።

የተስፋ መልዕክት ነው

ኃጢአት ያልነካው ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ በስብዕናችን፣ በድክመቶቻችን እና በችግራችን ውስጥ በመግባት እንደ እግዚአብሔር ልጆች መኖር እንዳንችል የሚያደርገን ኃጢአታችንን መሸከሙን ክቡር አባ ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። አክለውም ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን በይፋ በጀመረበት ጊዜ የእኛ ድነትም መጀመሩን የገለጹት ክቡር አባ ፍራንችስኮስ፣ ወደዚህ ሥፍራ ተመልሰን የምንመጣው ብርሃነ ጥምቀቱን ለማስታወስ ብቻ ሳይሆን የእርሱን የእርቅ መስዋዕትነት ለማስታወስም ጭምር ነው ብለዋል። ከ50 ዓመታት በፊት በተደረገው ጦርነት ምክንያት የተፈጠሩት ቁስሎች፣ የአካባብው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የሰው ልጅ ከጥላቻ ወጥቶ ሰላምን እና እርቅን የሚያገኝበት የለውጥ ምልክት እንደሚሆን፣ የሰው ልጅ በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰጠው አዲስ ጥምቀት ወደ እርቅ እንደሚደርስ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ አስቀድሞ መናገሩን አስታውሰዋል።

በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ መግባት

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ የሚገኙት ምዕመናን ቁጥር ሃምሳ ብቻ እንዲሆን ከእስራኤል መንግሥት ትዕዛዝ መድረሱ ታውቋል። ክቡር አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን በንግግራቸው፣ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሬቨን ሪቭሊን፣ ቅዱስ ሥፍራዎች ለቤተክርስቲያን እንዲመለሱ ከልብ በመመኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ክቡር ፕሬዝዳንት አቶ ሬቨን ሪቭሊን፣ እ.አ.አ 2015 እና 2018 ዓ. ም. በቫቲካን ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ጊዜ የውይይታቸው ቀዳሚ ርዕስም፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን ቦታ የተመለከተ እንደነበር ያስታወሱስት ክቡር አባ ፍራንችስኮስ፣ በወቅቱ ከተደረገው ታሪካዊ ስምምነት ጀምሮ በቅድስት አገር የሚኖሩ የፍራንችስካዊያን ማኅበር አባላት በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በተለያዩ ወቅት የኡደት እና የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።         

ጥንታዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት

በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የኢየሱስን የጥምቀት መታሰቢያ ክብረ በዓል መከበር የተጀመረው ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መሆኑ ሲታወቅ፣ በቅድስት አገር የሚኖሩ ፍራንችስካዊያን ወንድሞች እ.አ.አ ከ1641 ዓ. ም. ጀምሮ በየዓመቱ ወደ ሥፍራው መንፈሳዊ ጉዞን ሲያካሂዱ መቆየታቸው ይታውቃል። በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው በተከሰተው አለመረጋጋት ወደ ሥፍራው ሲደረግ የነበረው መንፈሳዊ ጉብኝት ተቋርጦ ቢቆይም እ.አ.አ 2011 ዓ. ም. በቃስር አል ያሁድ በተደረገው መጠነኛ እድሳት፣ አካባቢው ለመንፈሳዊ ጉዞ ክፍት መደረጉ ታውቋል። በቅድስት አገር የሚኖሩ ፍራንችስካዊ ወንድሞች በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ለተወሰኑ ዓመታት የብርሃነ ጥምቀቱን በዓል፣ የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎትን እና ለሕጻናት ምስጢረ ጥምቀትን ሲሰጡ መቆየታቸው ታውቋል። ሥፍራው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከመዘጋቱ አስቀድሞ በየዓመቱ ወደ ሥፍራው የሚመጡ ጎብኝዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር እ.አ.አ 2018 ዓ. ም. ወደ 720,000 መድረሱ ታውቋል።

የወደፊት ልማቱ

የእስራኤል መንግሥት አካባቢውን ለማልማት በወጠነው እቅድ መሠረት፣ ከፍተኛ ወጪን በመመደብ ባለፉት ዓመታት የቃሲር አል ያሁድ አካባቢዎችን ከፈንጂ ነጻ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ታውቋል። በቀጣይ ጊዜያትም በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተጠመቀበት ሥፍራ የሚያደርስ መንገድ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ተደርጎ እንደሚገነባ፣ ለንግደት የሚመጡ ምዕመናን የሚያርፉበት የጸሎት ሥፍራን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች የሚገነቡ ሲሆን የወንዙ ውሃ ንጽሕናም የሚሻሻል መሆኑ ታውቋል።    

13 January 2021, 16:40