ፈልግ

በኢራቅ ምዕመናን ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ማርያም ዘንድ ሲያቀርቡ በኢራቅ ምዕመናን ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ማርያም ዘንድ ሲያቀርቡ  

ካርዲናል ሩፋኤል፣ በኢራቅ ሰላምን ለማውረድ ምዕመናን በጾም እና በጸሎት እንዲተባበሩ ጠየቁ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመጪው መጋቢት 26-29/2013 ዓ. ም. በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆም እና ሁኔታዎች መመቻቸት የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ በኢራቅ ምዕመናን ዘንድ የሦስት ቀናት የጾም እና የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንዲፈጸም በማለት የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል የባቢሎን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ለአገሩ ምዕመናን ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ በመልዕክታቸው እንደገለጹት የጾም ሥነ-ሥርዓቱ እስከ እኩለ ቀን እና ከዚያም በላይ ሊራዘም እንደሚችል ገልጸው፣ አብዛኛው የኢራቅ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በየዕለቱ በሚካሄዱ የጸሎት እና የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓቶችን በመሳተፍ “የነነዌ ትንሳኤ” የሚል ርዕስ በተሰጠው በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዝግጅት እንዲያደርግ አደራ ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ አክለውም ከጥር 17/2013 ዓ. ም. ጀምሮ የሚካሄደው የጾም እና የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ወደ ፊት ለሚጠብቃቸ የጾም ወር መልካም ዝግጅት ይሆናል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ “የነነዌ ትንሳኤ” ለሚለው ርዕስ በሰጡት ማብራሪያ፣ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰ መሆኑን ገልጸው፣ እግዚአብሔር ነብዩ ዮናስን ለሕዝቡ እንዲሰብክ ወደ ነነዌ ከተማ በላከው ጊዜ፣ ከተማዋ የአይሁዳዊያን ከተማ ባለመሆኗ ምክንያት ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን አስታውሰዋል። ነብዩ ዮናስ በባሕር አውሎ ነፋስ በመመታት በአሳ ነባሪ እንደተዋጠ እና በፍርሃት እና በንስሃ ፣ የእግዚአብሔርን ይቅርታ በመለመን ሕይወቱን ከሞት ማዳኑን አስታውሰዋል። ይህ ክፍል ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል እንዳመለከቱት፣ “እግዚአብሔር መሐሪ ነው፤ እርሱ ለፈጠራቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሁሉ እንክብካቤውን የማያጓድል ፣ ደኅንነታቸውንም የሚመኝ ርኅሩኅ አባት ነው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚያስታውስ መሆኑን አስረድተዋል።

ከስቃይ ወጥቶ ለጸጋ እና ለመልካምነት መብቃት

የነነዌ ከተማ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሜሶፖታሚያ ላይ በደረሰው አስገራሚ መቅሰፍት የወደቀች መሆኑን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ፣ ዛሬ በተመሳሳይ መልኩ በአገራቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሰውን ሕይወት በአደጋ ላይ መጣሉን ገልጸው፣ አደጋው በመላው ዓለም ላይ በመድረሱ አሉታዊ ፋይዳው በጤና፣ በማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉን አስረድተው “ነገር ግን ያለፈው መቅሰፍት እንደተሸነፈ ሁሉ እኛም “ይህንን አሳዛኝ የወረርሽኙን ተሞክሮ በመንፈሳዊ እና ማህበራዊ አጋርነት ወደ ፀጋ እና ቸርነት እድል መለወጥ እንችላለን” ብለዋል።

ካርዲናል ሩፋኤል በመልዕክታቸው “ከኃጢአታችን እንመለስ፣ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመዳን እንጸልይ ፣ ህሊናችንን እንመርምር፣ በወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ ያለብንን ሃላፊነት በትክክል እንወጣ፣ ለታመሙት፣ ሥራቸውን እና ኑሯቸውን ላጡት በሙሉ የእርዳታ እጃችንን እንዘርጋ በማለት ምክራቸውን አስተላለፈዋል።

ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጸሎት ይደረግላቸዋል

የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል የባቢሎን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ለአገሩ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት ኢራቅ የብዙዎችን ሕይወት ከቀጠፉ በርካታ ጦርነቶች በኋላ ደህንነቷ የተጠበቀ እና ሰላም የሰፈነባት አገር እንድትሆን መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ባግዳድን፣ ኡርን፣ ኤርቢልን እና በነነዌ ክፍለ ሀገር የሚገኘውን ቃራቆሽ ከተማን የሚጎበኙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መሳካት በአገሪቱ የሚገኙ ቁምስናዎች ከጥር 17/2013 ዓ. ም. ጀምሮ በጸሎት እንዲተባበር አደራ ብለዋል። የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመልክተው የኢራቅ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በዋና ከተማዋ ባግዳድ፣ ኣል ማንሱር የፓትሪያርኩ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ሰብሳቢነት ጥር 11/2013 ዓ. ም. ስብሰባ ማድረጋቸው ታውቋል።

26 January 2021, 14:14