ፈልግ

የጥር 9/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘናዝሬት ዕለተ ስንበት አስተንትኖ የጥር 9/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘናዝሬት ዕለተ ስንበት አስተንትኖ 

የጥር 9/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘናዝሬት ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ሮሜ. 15፡1-13

2.   1ዮሐ. 4፡14-2

3.   ሐዋ.ሥ. 13፡32-43

4.   ማቴ.2፡19-23

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ከግብፅ ወደ ናዝሬት

ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው። ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ (ማቴ.2፡19-23)

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘናዝሬት የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን ፡፡ በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ለእያንዳንዳችን የሚሆን የሕይወት ስንቅ ይሰጠናል የሕይወት ምግብ ይመግበናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ወትሮው ዛሬም ወደ እያንዳንዳችን ይሠርፃል፣ እኛም ወደ እኛ የመጣውን ቃል ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን በተግባር እንድናውለው ያስፈልጋል፡፡

እርሱም እንደሚለን በምድር ላይ በምኖርበት ጊዜ ስለራሳችን ብቻ ሣይሆን ስለሌሎችም ማሠብ መጨነቅ እንደሚያስፈልግ ይነግረናል፡፡ “ብርቱ የሆኑ ሰዎች የደካሞችን ወድቀት መሸከም አንዳለባቸው ያሳስባል፡፡”

ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ሰው ቶሎ የሚቆጣ ከሆነ፣ በመስከር ቤተሰቡንና ጐረቤቱን የሚበጠብጥ ከሆነ፣ ሰውን ሁሉ የሚሳደብና የሚያስቀይም ከሆነ በቃ ይህ ሰው ፀባዮ ነውና ተውት እንዳሻው ያድርግ ማለት ሣይሆን ያንን ሠው ከዚህ  ሥራው እና ባህሪ እንዲመለስ በተደጋጋሚ በፍቅርና በትሕትና መርዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ነው የደካሞችን ሸክም መሸከም ማለት ካለበት አስከፊ ሁኔታ ወይንም ባሕሪ እንዲላቀቅ ማገዝ መርዳት ማለት ነው።

ይህም በጥምቀት የተቀበልነውን እምነታችንን መኖርና መመስከር ከምንችልባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ሲሆን መንፈሳዊ ሕይወታቸው በተለያዩ ሐሳቦች እና ልማዶች ወጥመድ ውስጥ ገብተው ያሉትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲላቀቁ  ማገዝ ነው። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ  በኤፌ 4፡2 “ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፣ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ተዕግሥተኞች ሁኑ” በማለት ይመክረናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሌላው መልዕክቱ 1ቆሮ 10፡33 ላይ የራሳችንን ደስታና ፍላጎት ብቻ በማዳመጥ ሕይወት ውስጥ ማንነታችን ለሌሎች ደስታ ምክንያት ሳንሆን እንዳንቀር ክርስቶስን በምሳሌነት በመጥቀስ በቃሉ ይናገራል።

ሮሜ 15፡2 ላይ በዕለታዊ ሕይወታችን ዘወትር የምናደርጋቸው ነገሮች ለሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሰናከያ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንድናደርግ ያሳስበናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከነ ውድቀታችን፣ ከነደካማነታችን ተቀብሎናል በኃላ ደግሞ ከውድቀታችን አነሣን ተመልሰን  እንዳንወድቅም በምን አቅጣጫ መጓዝ እንዳለብን መንገዱን በፍቅርና በትሕትና አስተማረን፡፡

ይህም ሆኖ በድካማችን ብዛት ብንወድቅም የምንመለስበትን መንገድ ምሥጢረ ንሰሀን አዘጋጀልን፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚሁ መልዕክቱ በመቀጠል ክርስቲያኖች አንድ ልብ አንድ ሐሳብ ሆነው እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑ ይመክራል።

ምክንያቱም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በኖረበት ዘመን አይሁዳውያን እኛ ከመጀመሪያው ጀምሮ እግዚአብሔርን እናውቃለን በማለት አረማውያንንና ከአረማውያን ወገን የሆኑትን ክርስቲያኖችን ሁሉ ይንቁ ነበር፡፡

በዚህ በተከፋፈለ ልብ ግን እግዚአብሔርን ማመስገን እንደማይቻል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ አበክሮ ይናገራል ለዚህ ነው  ክርስቲያኖች በአንድ ልብ በአንድ ሐሳብ እግዚአብሔርን ያመስግኑ የሚለው፡፡  በክርስቲያን ማኀበረሰብ ውስጥ መከፋፈልና መለያየት ካለ ይህ መንፈስ ከእግዚአብሔር የመጣ መንፈስ አይደለም ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ ሁሌም የአንድነት፣ የመተባበር፣ የመረዳዳትና የመከባበር መንፈስ ነው ፡፡

ዛሬም ምንአልባት ይህ ክስተት በኛ በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር ይችላል፡፡ ሀብታሞችና ባለጸጎች፣ድሆችን፣ የተማሩት ያልተማሩትን፣ ጤነኞች በሽተኞችን ለመቀበል የሚቸገሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡

ይህ ግን የክርስቶስ ወዳጅ እና የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ከሚል  ሰው ሊንፀባረቅ አይገባም፡፡  ምክንያቱም ዓላማችን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ሐሳብ በፍጹም ኃይል መውደድና ባልእንጀራችንን እንደራሳችን አድርገን መውደድ ነውና፡፡ (ማር 12፡30) “አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኅይልህ ውደድ” (ማር 12፡31 ፣ ገላ 5፡14) “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላልና።

ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስን መልዕክት ስለ ምስክርነት በመግለጽ ሃሳቡን ያጠናክረዋል ይህም 1ዩሐ 4፡15-16 “ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆን አምኖ በሚመሰክር ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፣ በፍቅሩም እናምናለን።” ይለናል።

በዚሁ በቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ መልዕት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል ስለዚህ ይህን ፍቅር የሆነን አምላክ የምናፈቅረው በፍርሃት ሳይሆን ፍቅር በተሞላበት መንፈስ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

እግዘአብሔር ይቀጣናል ወደ ገሃነም ይከተናል በሚል ሐሳብ የምንቀርበው እና የምናመልከው ከሆነ ይህ ስሕተት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሌም ፍቅር የሆነ ፍቅርን የሚሰጥ ፍቅርን የሚያበረታታና ስለ ልጆቹ ፍቅር ብሎ ሕይወቱን በመስቀል ላይ አላልፎ በመስጠት ያዳነን አምላክ ነው።

በዚሁ በዮሐንስ መልዕክት 4፡18 ላይ “በፍቅር ፍርሃት የለም ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፣ ፍርሃት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና፡፡ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም” ይላል፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር እንጂ በፍርሃት መንፈስ ልናፈቅረው አይገባም፡፡ ባለ እንጀራችንንም እንዲሁ ንጹህ በሆነ ፍቅር እንጂ ብድር ስለሚመልስ መሆን የለበትም፡፡ ሉቃስ 14፡13 እንዲህ ይላል ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድሆችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዓይነስውሮችን ጥራ ትባረካለህም እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ በጻድቃን ትንሣኤ እግዚአብሔር ራሱ ብድራትህን ይመልስልሃል ይላል፡፡

የማቴዎስ ወንጌል 2፡19-23 ላይም እግዚአብሔርን የሚወድና በእርሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሰው እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ እንደሚረዳው፣ እንደሚመራውና እንደሚያግዘው ያስተምረናል፡፡

የፃድቁ የቅዱስ ዬሴፍ ሕይወት የሚያመላክተን ይህንኑ ነው ገና ከጅምሩ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከፀነሰችበት ጊዜ አንስቶ እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንዳለበት ይነግረው ነበር በሕልሙ ይገልፅለት ነበር፡፡  እርሱም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመላለስ ነበር፡፡

ወደ ግብፅ እናቱንና ሕፃኑን ይዞ እንዲሄድ እንደነገረው አሁን ደግሞ ከግብፅ ወደ እስራኤል እንዲመለስ ነገረው፡፡ በዚህም በትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፈ 11፡1 ላይ ያለው የትንቢት ቃል ተፈፀመ ልጄን ከግብፅ እነዲወጣ ጠራሁት ይላል።

እኛም  በሕይወታችን ለእግዚአብሔር ታማኞችና ታዛዦች ከሆንን እርሱን ከልባችን በማፍቀር በእርሱ እቅድ የምንመላለስ ከሆንን እሱ ሁሌም ከእኛ ጋር ይሆናል በለመለመው መስክም ይመራናል፡፡ መዝሙር 34፡7 ጀምሮ እንዲህ ይላል እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል ያድናቸዋልም  እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው እናንተ ቅዱሳን እግዚአብሔርን ፍሩት እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና አንበሶች ሊያጡ ሊራቡም ይችላሉ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጎድልባቸውም የላል፡፡ እንግዲህ እኛም ሁል ጊዜ ከእርሱ ጋር ድምፁን በመስማት የምንጓዝ ከሆንን የእርሱ በረከት ከእኛ ጋር ይሆናል። ለዚህም ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የብዙኃን እናት የሆነች ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ይህን የማያልቀውን ፀጋና በረከትን ታማልደን፡፡

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

16 January 2021, 12:21